የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የሕይወት ሥነ ሥርዓት (32)

17. ማኅበራዊ ኑሮ ይኑርህ

አንድነትን በሚመለከት አራት ዓይነት ኅብረቶች አሉ ። የመጀመሪያው ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ያለው አንድነት ነው ። ሁለተኛው ሰው ከራሱ ጋር ያለው አንድነት ነው ። ሦስተኛው ሰው ከሰው ጋር ያለው አንድነት ነው ። አራተኛው ሰው ከአማኝ ጋር ያለው አንድነት ነው ። ከእግዚአብሔር ጋር ያለን አንድነት እርሱን በማወቅ ፣ በማምለክና ትእዛዛቱን በመፈጸም ፣ በንስሐ በመታደስ ላይ የተመሠረተ እንዲሁም የሚቀጥል ነው ። ሰው ከራሱ ጋር ያለው አንድነት ከእግዚአብሔር ጋር ባለው አንድነት ላይ የሚመሠረት ነው ። ሰው ከራሱ ጋር መለያየት ካመጣ ፣ ውስጣዊ ግጭት ካለበት ሰላምና ደስታ እንዲሁም የመኖር ፍላጎት እየራቀው ይመጣል ። ሰው ከሰው ጋር ያለው አንድነት ከራሱ ጋር ባለው አንድነት መሠረት ላይ የሚቆም ነው ። ከራሱ ጋር አንድ ያልሆነ ከሌላው ጋር አንድ ሊሆን አይችልም ። ሰው በማመን እርሱን ከሚመስሉት ጋር አንድ የሚሆንበት ዘላቂ አንድነት አለ ። ይህን አንድነት ልዩ የሚያደርገው በሰማይም የሚቀጥል በመሆኑ ነው ።

አማኒ የሆነው ወንድማችን ዘመዳችን ፣ ጎረቤታችን ፣ የቅርብ አገልጋያችን ላይሆን ይችላል ። ያለን ግንኙነት መንፈሳዊ ነው ። ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም እንድንኖር መጽሐፍ ያዝዘናል (ሮሜ. 12፡18)። አንዳንዴ አዳጋች ይሆናልና ቢቻላችሁስ የሚል ሚዛን ያስቀምጧል ። ከተቻለን ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም መኖር መልካም ነው ። ሰዎች ግን የእኛ እምነትና ህልውና እየረበሻቸው ሊጣሉን ይችላሉ ። ክርስቲያን በምንም መንገድ ሌላውን የሚያውክ ሊሆን አይችልም ። እርስ በርሳቸው የዘረኝነት ችግር ቢኖርባቸውም ጌታችን ግን ከአይሁድ ወገን ተወልዶ የሳምራውያን ወዳጅ ነበረ ። ሰው ያገለላቸውን ቀራጮችና አመንዝሮች ከእርሱ ጋር አብረው እንዲበሉ ይጋብዛቸው ነበር ። ክርስቲያን ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር መስፈርት የሚያደርገው ሃይማኖቱን ወይም እንደ እኔ ካላመኑ የሚለውን አመለካከት አይደለም ። ክርስቲያን በመጽሐፍ እንጂ በሰይፍ የሚያሳምን አይደለምና ።

ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር መዋሸት አለብን ማለት አይደለም ። ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር የራሳችንን አመለካከትና ሃይማኖት እያከበርን የሌሎችንም ማክበር ነው ። የሃይማኖትህ መሪ የሆነው አባት ከቡዲስት ወይም ከአረሚ ጋር ሰላም ሲባባል ስታይ የምትበሳጭ ከሆነ ይህችን ዓለም ያንተ እምነት አባላት ብቻ እንዲኖሩባት እየፈለግህ ነው ። የራስን ይዞ የሌላውን ማክበር ይቻላል ። ሰዎች ያመኑበትን በጥላቻ ለማስጣል ስንሞክር የበለጠ እንዲያከሩ እናደርጋቸዋለን ። ምንም ውክልና የሌላቸው ለቤተ ክርስቲያን መልስ እንሰጥላታለን የሚሉ ወጣቶች በየጊዜው በሃይማኖት ስም ጥላቻን ሲዘሩ ይታያሉ ። እዚህ ያለውን አይሁድ ስትነካው ኢየሩሳሌም ያለው ክርስቲያን መኖሪያ ያጣል ። ሁሉም አገር አለውና ። እዚህ ያለውን ሙስሊም ስትነካው ግብጽ ያለው ክርስቲያን መሸበር ይጀምራል ። የዚህች ዓለም ሰላም የቆመው በሰው ልጆች ሁሉ ነጻነት ላይ ነው ። የራሱ እምነት ያሳረፈው ሰው የሌላውን በመንቀፍ ጊዜውን አይፈጅም ።

ማኅበራዊ ኑሮ በመከባበር ላይ የተመሠረተ ነው ። ማኅበራዊ ኑሮ በብዙ መንገዶች ሊጎዳ ይችላል ። የብቸኝነትና የጭንቀት መንፈስ ሲታገለን ማኅበራዊ ኑሮአችን እየተጎዳ ይመጣል ። መሸሽን ገለል ብሎ መቀመጥን እንወዳለን ። አንዳንድ ጊዜም ከትዳራችንና ከልጆቻችን መሸሽ ይታየናል ። የብዙ ትዳር ችግር ማንም ያላወቀው ጭንቀት ነው ። መነጫነጩ ፣ ስካሩ ውጤት ነው ። መነሻው ግን ጭንቀት ነው ። ሥሩን ካልፈወስን ቅርንጫፉ አይድንም ። ስለ ሰዎች ያለን ተገቢ ያልሆነ አመለካከት ይኖራል ። ይህ ከቤተሰብ ፣ ከአስተዳደግና ከደረሰብን ጉዳት የተነሣ የሚመጣ ነው ። በዚህ ምክንያት ከማኅበራዊ ኑሮ እንርቃለን ። ልጆች ሲያድጉ ከሰው ጋር እንዲቀላቀሉ ፣ ሰርግም ልቅሶም እንዲያዩ ተደርገው ሊሆን ይገባል ። ዛሬ ብንሸፍናቸው ነገ ብቻቸውን ይጋፈጡታል ። ልጆችን ተክቶ የሚኖር ወላጅ ሞቱን የረሳ ወላጅ ነው ። ዘመናዊነት ማኅበራዊነትን እየናደ ነው ። የትዳር ክፍተቶች ፣ የፍቺ መበራከቶች ማኅበራዊነትን ይጎዳሉ ። የሚሰሙና የሚታዩ ዘግናኝ ወንጀሎች ሰውን ፈሪ በማድረግ እንዲራራቅ ያደርጉታል ። ወንድ ልጃቸውን ለሴትም ለወንድም አደራ ብለው ለመሄድ የተቸገሩ ወላጆች አሉ ። የሚሰሙት ነገር ሕሊናቸውን አርክሶታል ፣ ልባቸውን ፈሪ አድርጎታል ። የገዛ ሴት ልጃቸውን ለአባት ትተው መሄድ የሚፈተኑ እናቶችን እናውቃለን ። ማኅበራዊነት በአባትና በልጅ መካከል ከፈረሰ ሌላ ቦታ መጠበቅ ከባድ ነው ።

ዘመናዊው ዓለም የግል የሆኑ ነገሮችን በማብዛት አንድነትን የማፍረስ ዘመቻ ላይ ነው ። በየጊዜው በላቦራቶሪ ተመርተው በሚለቀቁ በሽታዎች ሰው ሰውን እንዳይቀርብ ሰይጣናዊ ተልእኮአቸውን እየተወጡ ነው ። በዚህ ምክንያት የሰው ልጅ በብቸኝነት ዕድሜው እያጠረ ይመጣል ። ማኅበራዊነት ዕድሜን ይቀጥላል ፣ ደስታንም ይሰጣል ። አብረው ካልበሉ ፣ አብረው ካልተደሰቱ ፣ አብረው ካላለቀሱ የዚህ ዓለም ኑሮ ሊገፋ አይችልም ። ራስ ወዳድነትና ስስት ፣ ሁሉንም ነገር ስሌት ውስጥ ማስገባት የማኅበራዊነት ጠላት ነው ። ለሌሎች ስንኖር ሌሎች ለእኛ ይሞቱልናል ። የምናጭደው ከዘራነው በላይ ነውና ። ደግሞም ውጤቱን በማሰብ ሳይሆን በራሱ ትልቅ ደስታ በመሆኑ ማኅበራዊነት ሊጠነክር ይገባዋል ። አንተም ማኅበራዊነት አስፈላጊህ ነውና የሠራኸውን የግል ደሴት አፍርሰህ ከሰው ተቀላቀል ! ሞኝ አትሁን ከምትሰጣቸው የሚሰጡህ ይበልጣል ! ፌስ ቡክ ላይ ልቅሶ መድረስ ፣ ቲክ ቶክ ላይ ሙሾ ማውረድ ቁምነገር አይምሰልህ ፣ የቀኑ የወሬ ጥማትህ ማሟያ ወይም ምን ላውራ ለሚለው ጭንቀትህ ማረፊያ ነው ! ማኅበራዊነት አካላዊነት ነው ! መሄድ ፣ ጊዜ መስጠት ፣ አቅፎ ማጽናናት ፣ በጎደለው መሙላት ነው !

ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሰኔ 14 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ