24. የውሸት ኑሮ አቁም
የብዙ ሰው ሕይወት በውሸት የተሞላ ነው ። የውሸት ይስቃል ፣ የውሸት ያለቅሳል ። የውሸት ይፎክራል ፣ የውሸት ይዘምራል ። የውሸት እንባውን ያፈስሳል ፣ የውሸት እልል ያሰኛል ። ያደረግነውን ነገር ያደረግነው ከልባችን ነው ወይስ ለማስመሰል ነው ብለን ራሳችንን መጠየቅ አለብን ። ከሰው ጋር የመኖር ትልቅ ምሥጢር ከራስ ጋር መኖር መቻል ነው ። ከራሳችን ጋር የምንኖረው በእውነት ብቻ ነው ። ሥልጣናችን ፣ ሀብታችን ፣ ትዳራችን ፣ ዝናችን የእውነት ካልሆነ በውስጣችን ታላላቅ ፍንዳታዎች በየሰከንዱ ይሰማሉ ። ሰው ራሱን አስሮ የሚያሰቃይበት እስር ቤት ካለ ውሸት ነው ። ለባለጠጎች በማያስቀው እየሳቁ ፣ እርስዎ ልክ ነዎት እያሉ ዕድሜአቸውን የሚገፉ አያሌ ናቸው ። ፓትርያርክ ፣ ጳጳስ ሲያዩ መወድስ የሚደረድሩ ዞር ሲሉላቸው መውቀስ የሚያበዙ ቍጥር የላቸውም ። አስመሳይነት የዲያብሎስ የበኵር ልጅ መሆን ነው ። ነገ ላይ ከሰው ላለመለየት ፣ ነገ ላይ ጨረታ ላለማጣት ፣ ነገ ላይ የሀብታሞችን ጥላቻ ላለማትረፍ የማያምኑበትን መጠጥ የሚጠጡ ፣ ቤታቸውን ርቀው በደጅ የሚያድሩ ብዙ ናቸው ። ይህን የውሸት ኑሮ ትዳራቸውም አምኖላቸዋል ። ከባለጠጋ ጋር ሲያመሹ ትዳሩም እሰየው ይላል ፣ ከድሀ ጋር ሲያመሹ ቤቱን አያከብርም ተብሎ ሽማግሌ ይጠራል ። ልጆቻቸውን ሳይቀር ለጥጋበኞች ጨረታ የሚያቀርቡ ወላጆች ባለፉት ሠላሳ ዓመታት አትርፈናል ።
ባለጠጎች ድሀን የፈጠሩት ይመስላቸዋል ። በምድር ላይ ባለጠጎችና ነገሥታት ትዳር ሲፈጽሙ ድሀ መጨነቅ ይጀምራል ። ገንዘብ ሐሰተኛ ወዳጅና እውነተኛ ጠላት የሚገዛ ነው ። በአገራችን ልቅሶ ብድር ነው ። እንባውን ለእኛ ልቅሶ ላፈሰሰ የእርሱም ሲሞትበት ሄደን እናለቅሳለን ። ሰውዬው ስለ ሞተ ሄደን አንቀብርም ፣ ተመልካች ዘመድ ካለ ግን እስከ ዐርባው አንለይም ። ልቅሶ በፖሊስ የምናለቅስበት አገር ይመስላል ። ጾማችን እንኳ በጾም ትራፊኮች ቁጥጥር ካልሆነ ላንጾመው እንችላለን ። በደርግ ዘመን ሽፍንፍን የሚባል ምግብ መጥቶ ነበር ። ጥብሱ ሥጋ አንድ እንጀራ ሙሉ ይለብሳል ። ከላይ ሲታይ የጾም ነው ፣ በቀዳዳው እጁን እየላከ የሚበላው ግን ሥጋ ነው ። በሁዳዴ ሽፍንፍን ተጀመረ ። የጾም ዋጋ ከፋይ እግዚአብሔር ነው ። ጾም በሁለት ነገር ይረክሳል ። የመጀመሪው የሌላውን አለመጾም ሲያሳየን ሲሆን ሁለተኛው የተውነውን ምግብ ለድሀ ባለመስጠታችን ነው ። ጸሎት ያለ ምጽዋት አይሆንም ። ምክንያቱም የእኔ ጸሎት እንዲሰማ የድሀን ጩኸት መስማት አለብኝና ። ጾምም ኢኮኖሚ ሳይሆን የተውነውን ምግብ በምጽዋት ለድሆች መስጠት ነው ።
ያዙኝ ልቀቁኝ እያለ የሚፎክረው ደፍሮ ሳይሆን ፈርቶ ሊሆን ይችላል ። አቅሙን የሚያውቅ ውሻ አይጮህም ። አድብቶ ይይዛል ። ፉከራ ባለበት ፍርሃት ይነግሣል ። ደጅ ላይ በጣም ሽቁጥቁጥ የሆኑ ሰዎች ገና የቤታቸውን በር ሲያንኳኩ ቤተሰቡ መሯሯጥ ይጀምራል ። የደጅ ፈሪ የቤት ጀግና ነው ። ሰካራሙ ጭላጭ እየተደፋበትና እየተሰደበ ጠጥቶ እቤቱ ሲገባ አምባገነን ሁኖ እንቅልፍ ይነሣል ። የውሸት የሚፎክር ብዙ ነው ። ፉከራ ጸሎትን ያስረሳልና እንደ ጴጥሮስ ለክህደት ይዳርጋል ። እግዚአብሔር ከረዳኝ ያንን ወይም ይህንን አደርጋለሁ ማለት ይሻላል እንጂ ፉከራ ከንቱ ነው ። በኃይለ እግዚአብሔር ስንል መላእክት ይዋጉልናል ፣ በእኔ ጉልበት ስንል አጋንንት ይዋጉናል ። የውሸት የሚዘምር ብዙ ነው ። እንደ ሰማነው ስዘምር አለቅስ የነበረው አስለቃሽ ቅባት ተቀብቼ ነበር እየተባለ ነው ። እግዚአብሔር የደበቀላቸውን ነውር መደበቅ ያልቻሉ ብዙ ናቸው ። ግልጽነቱ መጠን ከሌለው እብደት ነው ። “እብድና ብርድ በግድ ያስቅ” ይባላል ። ብርድም እትትት.. ሲያሰኝ ፈገግታ አለው ። እብድም ፣ የጠባይ ነሆለልም በግድ ያስቃል ። አምልኮተ እግዚአብሔር ለብዙዎች ተውኔት ነው ። ምስኪኑን ሕዝብ የሚያስለቅሱበት እነርሱ ግን የሚስቁበት ነው ። በዓለም ያልጨረሰውን ጭፈራ በኢየሱስ ስም ለመጨረስ የተሰለፈው ቍጥር የለውም ። እንደዚህ ካለ ዓለማዊ ዝማሬ መሳይ ጋር መተባበር ስህተት ነው ።
አንዳንድ ተናጋሪ ሰዎች እንባቸውን ፈሰስ ሲያደርጉት ብዙ ሕዝብ ይከተላቸዋል ። እንባቸው የንግድ ፈቃዳቸው ነው ። አንደኛው በኢየሱስ ስም ፣ ሌላኛው በእመቤታችን ስም ሲያታልል ቀኑ ይመሻል ። አንድ ወጣት አንድ ሰው እያሳየኝ ያ ተናጋሪ የሚያለቅስበትን ደቂቃ አውቆታልና አሁን ሊያለቅስ ነው አለኝና ተናጋሪ ወዲያው አለቀሰ ። የሚያለቅሱበት ደቂቃ እንኳ የተለካ ሰዎች አሉ ። እንባ ግድ ካልሆነ በአደባባይ ባይደረግ መልካም ነው ። እነዚህ ሰዎች በድብቅ ያልቅሱ እንዳይባል በድብቅ አይጸልዩም ፣ አያለቅሱም ፤ ላይሰንሳቸውን ለማደስ በአደባባይ ያለቅሳሉ ። አማኝን ሳይሆን ገጸ ባሕርይ የተላበሱ ምእመናንን ያተረፍነው በዚህ ይመስላል ።
ብዙ ሰዎች በጌታ ሰላም አለኝ ፣ ደስተኛ ነኝ እያሉ ሲለፈልፉ ይውላሉ ። እውነቱ ግን እነዚህ ሰዎች ሰላምም ደስታም የላቸውም ። የያዙት ነገር አይወራም ። ራሱ ይናገራል እንጂ ። አዎ እንደ ተባለው፡- “የውሸት ኖረን የእውነት እንሞታለን ።”
ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሐምሌ 16 ቀን 2016 ዓ.ም.