የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እንዳይደክመኝ

ክፋት ሲያድግ ፣ ደግነት ሲያንስ ፣ አጋጣሚዎች ማር ሳይሆን መርዝ ሲረጭባቸው ፣ ያውቃል የተባለው ካላወቀው በላይ ሲዋዥቅ ፣ ሙሉ ያሉት ጭላጭ ሲሆን ፣ የሚሰጠው መቀበል ሲሳነው ፣ ምግቡ ሲገኝ ጠኔ የያዘው ሰው ሞት ሲወስደው ፣ ይበልጣል ያሉት ከሁሉ ኋላ ሲሆን ፣ የመራ ከሰልፉ ወጥቶ ሲንከላወስ ፣ አመኔታ የተጣለበት ለማነስ ሲቸኩል እንዳይደክመኝ ያህዌ እባክህ አግዘኝ ። የምፈልገውን ሳገኝ እንደ ገና ሌላ ፍላጎት ሲያድርብኝ ፣ ፍለጋ አያልቅም ብዬ ስጨነቅ ፣ አተርፋለሁ ካልኩት ነገር ራሴን ስከስር ፣ ኑሮን ቀብቼ ሕይወትን ሳፈርስ ፣ ዘላለማዊውን በወቅታዊ ስለውጥ ፣ የመለኮትን ሙላት በፍጡር ጉድለት ስለካ እንዳይደክመኝ ኤልሻዳይ ሆይ እባክህ ለውጠኝ ። የሠዋሁት ሲነሣ ፣ ሞቻለሁ ብዬ መኖር ስጀምር ፣ መስቀሉን ኋላ ዓለምን ከፊት ሳደርግ ፣ እንግዳ ነኝ ብዬ ዘምሬ ተደላድዬ ስቀመጥ ፣ ብዙዎችን ቀብሬ እኔ እንደ ሐውልት ቆሜ የምቀር ሲመስለኝ ፣ የሚያብራራ የሚያበራ መሆኑን ዘንግቼ ታግሼ መስማት ሲያቅተኝ ፣ የአንድ ደቂቃ ቁም ነገርን ስፈልግ ፣ ቁርጥራጭ እውነትን ሳስስ ፣ በኪራይ ዓለም ላይ ተከራይ ብዬ ሌላውን ስናገር ፣ እኔነቴ አናቴ ላይ ወጥቶ ሲያሰክረኝ ፣ ራስን መሸጥ ዘመናዊ ንግድ ሲመስለኝ እንዳይደክመኝ እባክህ አዶናይ ሆይ ከዚህ ሕይወት አስመልጠኝ ።

የማለን ሳምን ፣ ለሚያለቅስ ብቻ ስፈርድ ፣ ሥጋዊ ቅንዓት ሃይማኖታዊ ቅንዓት ሲመስለኝ ፣ የሚመቸኝን አስተማሪ እየፈለግሁ የሚመክረኝን ስጠላ ፣ የሚመለከተኝን ትቼ የማይመለከተኝን ኳስ ስናደድበት ፣ በራ ስለው ሲጨልም ፣ ወጣሁ ስል ስዳክር ፣ ወሬኛን ወድጄ ሠራተኛን ስንቅ ፣ ሌባን አፍሬ ልፋተኛን ሳሳድድ ፣ ድህነትን ሳይሆን ድሀን ሳስወግድ ፣ ዘፈንን አድንቄ መዝሙር ላይ ሳኮርፍ እንዳይደክመኝ እባክህን በቀኝህ ደግፈኝ ።

ወጭና ወራጁ ልቤን ሲያዝለው ፣ ቆንጆው መልኩ ሲጠፋብኝ ፣ የትላንት ሰጪ እጁ ጉንድሽ ሲሆን ፣ አላማጁ ለማጅ ፣ ሁሉም እንግዳ ሲሆን ፣ ዓለምን ለመቀየር ተነሣሁ ያሉ ኑሮአቸውን በመቀየር ሲፈጽሙ ፣ የከፋው አትኩሮ የሚያየው ሲያጣ ፣ ለትላንት አጽናኝ እንባውን የሚጠርግለት ሲጠፋ ፣ የቃል ትምህርት ቤት በዝቶ የተግባር ትምህርት ሲጠፋ ፣ ነገረ እግዚአብሔር ቀሎ ነገረ ሰብእ ሲከብር ፣ የመጽሐፉ ትንቢት ተንቆ አዲስ ባለ ራእይ ሲታሰስ ፣ በመዘጋጃው ቀን ሰርግ ሲደገስ ፣ ምሕረትህ ሳይማርከኝ ወይ ፍርድህ ሳያስፈራኝ ስንኖር ፣ ማስተዋል ጠፍቶ ወድቆ ማሰብ ሲጀመር እንዳይደክመኝ ወልድ ሆይ በኪዳንህ አስበኝ ።

የተማሩ እንዳልተማረ ሲሆኑ ፣ ንጹሕ ምንጭ ተንቆ የጎርፍ ውኃ ለመጠጥ ሲውል ፣ ውስጡ ፈርሶ ሰው ላዩን ሲያሳምር ፣ ተራራ ስህተቱን ችላ ብሎ የሌሎችን ነቍጥ ሲቆጥር ፣ እንዴት ልመለስ ለሚለው ምስኪን የገደል መንገድ ሲያሳይ ፣ አደራ ተበልቶ መንጋው ላይ አውሬ ሲሰማራበት ፣ ሕሊናም ሕግም ሲተወን ፣ አብረን በልተን ስንጋደል ፣ አብረን ዘርተን አብረን ማጨድ ሲሳነን ፣ የጋራን ምድር የግሌ ስንል እንዳይደክመኝ እባክህ ለልቤ ልብ ስጠኝ ።

ሥራ ሰጥቶ የሚቆጣጠር ፣ አዝዞ የሚከታተል የበላይ ሲጠፋ ፣ ቁጭት መክኖ ስንፍና ሲበረታ ፣ ነገን ለመግደል ስንራወጥ ፣ ትልቅነትን ከትልቅ ሥራ መጠበቅ ስናቆም ፣ መልእክት ይዘን ስንረሳ ፣ ለሩቅ ተጠርተን ቅርብ ስናድር ፣ በሽታ አስተኝተን የመንገድ ጨዋታ ሲያስቀረን ፣ ወደ ላይ መላእክት እንዲስቡን ቀርቶ ወደ ታች አጋንንት እንዲጎትቱን ወደን ስንማረክ እንዳይደክመን እባክህ አግዘን ።

እየበላሁ ረሀብ ሲሰማኝ ፣ አግኝቼ እጦት ሲያሰቃየኝ ፣ የልመናዬ መልስ ምስጋና ቢስ ሲያደርገኝ ፣ አልቅስ አልቅስ እያለ ጠላቴ ሆድ ሲያስብሰኝ ፣ መዳኔ አንሶብኝ ምሬት ሲያነጋግረን ፣ የሌላቸውን እያጽናናሁ ፣ መቻልን እየነገርሁ እኔ ባለኝ ነገር ማመስገን ሲሳነኝ ፣ ትላንትን አልፌ ዛሬ ሲያስፈራኝ ፣ ማፍቀር ደክሞኝ መጣላት ሲቀለኝ ፣ መዝራት ተስኖኝ መንቀል ሥራ ሲሆንብኝ ፣ ዛሬን ሳልኖረው ነገ ሲያስፈራኝ እንዳይደክመኝ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ሆይ እባክህ አግዘኝ ።

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መስከረም 13 ቀን 2017 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ