“ጨረቃ ብትደምቅ አትሞቅ።”
በዚህ ዓለም ላይ ድሀውና ታማሚው ዘመድ ይክደዋል ፣ የተሳካለትን ደግሞ ሁሉም ሐረግ ሠርቶ የእኔ ዘመድ ነው ይለዋል ። በልጅነታቸው የእኛ ዘር አይደሉም ተብለው የተካዱ አድገው ባለጠጋና ዝነኛ ሲሆኑ መልሰው ያምኑአቸዋል ። ባለጠጋ ዘመድ የሌለው ድሀ የለም ፣ ሁሉም ባለጠጋ የራሱን ድሀ ቢሸከም የዓለም ችግር ይቀንስ ነበር ። ድሀ ሁሉ ድሀ የሆነው ባለጠጋ ዘመድ ስለሌለው አይደለም ። የባለጠጋ ዘመድ ቀብር አሳማሪ እንጂ ኑሮ አሳማሪ አይደለም ። የቀብሩ ሥነ ሥርዓትም ከእውነትነት ይልቅ የአንድ ቀን ድራማ ነው ። ለስማቸው ፣ አነርሱን ብሎ ለሚመጣ እኩያ የሚደረግ እንጂ የሟችን ቤተሰብ ቀና የሚያደርግ ፣ ረሀቡን የሚያስታግሥ አይደለም ። በእኛ አገር ርቦት ለሞተው ሰው ቀብሩ ላይ በሬ ይታረዳል ። ታርዞ ለኖረው ብዙ ድንኳን ይጣላል ። ብቸኝነት እንዳላጠቃው ሺህዎች ሊቀብሩት ይመጣሉ ።
ዋናው መሞትህ ነው ። ከሞትህ ማንም አያማህም ፣ “ሙት መውቀስ ድንጋይ መንከስ” ይባልልሃል ። ከሞትህ እንደ ገና አያዩህምና ፎቶህን በትልቁ አሠርተው “ለእኔ ልዩ ነህ” እያሉ ያዜሙልሃል ። ከዚህ በኋላ መጥተህ ቁመት አትለካካቸውምና ወደ ታች ይቀብሩሃል ። ሽቱአቸውን አትጋፋምና አፈር ይበትኑብሃል ። አይተህ ደስ አይልህምና ኮርማ የሚያህል አበባ ያመጡልሃል ። እንዳትወጣ ሰግተው ባዞላ ያነጥፉብሃል ፣ ቀዳዳውን በሲሚንቶ ይደፍኑታል ። ግማሽ ቀን ርእስ ነህ ፣ ከዚያ በኋላ ለዘላለም ይረሱሃል ። ስምህን ሲያጠለሹት ከርመው ፣ መድረሻ እንዳላሳጡህ ቅድስና የሞላበት የሕይወትህን ታሪክ ያነቡልሃል ። ሰላምታ እንዳልናፈቀህ አሥር ገጽ የመልካምነትህ ወሬ ቀብርህ ላይ ይነበብልሃል ። አንድ ካህን ያልመጣልህ ፣ አንድ ቃል ያልነገረህ ብትሆንም አሁን አህያ ልትሸከመው የማትችለውን መጽሐፍ ዘርግተው ያነቡልሃል ። በቁምህ ቁረብ ሳይሉህ አሁን ከበሮ ይዘው ይደርሱልሃል ። ሳለህ እግዚአብሔር ይፍታህ ሳይሉህ የሰባት ደብር ቄስ ሊፈቱህ ይመጣሉ ። ብቻ ሙትላቸው ፣ በጣም ይወዱሃል ። አገሬ እንዲህ ናት ። ያወቁ ሳይሆን ያወቁ የሚመስሉ የሚከበሩባት ፣ ከቁምነገር ይልቅ ፌዝ ካባ የሚለብሳባት ይህች ናት አገሬ ። ከሰውነት ይልቅ ጨርቅን የሚያከብር ፣ ኖር ለልብሱ የሚል ይህ ነው ወገኔ !
ጨረቃ ብትወጣም ብርዱን ስለማትከላከል ብዙ ልብስ ታወጣለህ ። ጨረቃ ብትደምቅ አትሞቅም ። እርሱ ብዙ ማድረግ እየቻለ አላደረገልኝም ብለህ በደማቁ ዘመድህ አትበሳጭ ። በዚህ ዓለም ላይ የሚጠቅሙህ የማይገመቱ ሰዎች ናቸው ። እውቅ ሰዎችን ለመተዋወቅ እንሻለን ። ከትልልቆች ጋር ፎቶ ለማስቀረት እንጋደላለን ። ከትልልቆች ጋር የተነሣነውን ፎቶ እንለጥፋለን ፣ ማስፈራሪያ መሆኑ ነው ። የተማመናቸው አንዳቸው አይጠቅሙንም ። ትልቅ ሁኖ የሚጠቅም አንድ ብቻ ነው ። እርሱም ስሙ እግዚአብሔር ይባላል ።
ከእነ እገሌ ጋር የጋብቻ ዝምድና ቢኖር ደስ ይላል ። እነ እገሌን ማወቅ ኃጢአት አይደለም ። ነገር ግን ትልልቆች ቢዋቡ ፣ ቢታዩ ፣ አያሞቁም ። ፀሐይ ትሞቃለች ፤ ነገር ግን ማንም አያያትም ። የሚያጽናኑን የሚያበረቱን ጋ ምንም ፎቶ የለንም ። አናያቸውም ፣ ብናያቸው እንደ ፀሐይ እንባችን ይመጣል ። የሚጠቅሙን አዋቂ እንጂ ታዋቂ አይደሉም ።
እንደ ጨረቃ በውበታቸው ፣ በአለባበሳቸው ፣ የሰውን አንገት ደፋ በሚያደርግ ግርማ ሞገሳቸው የተደነቁ ይኖራሉ ። በጦርነት ውስጥ የውበት ውድድር እንደሌለ ዓለም በተጨነቀችበት ጊዜ ይህ ውበት አይጠቅምም ። ከዚህ ሞገስ ውስጥ የሚያጽናና ቃል ፣ ከዚህ ዝነኝነት ውስጥ መንገድ የሚያሳይ ምክር የሰው ልጅ ይፈልጋል ። ጨረቃ ብትደምቅ አትሞቅ ! ብዙ ደማቆች አብረዋቸው ለሚኖሩት ብርድ ናቸው ! “የባል ደግነቱ ባትናገር ሚስቱ” እንዲሉ በየቤቱ ብዙ ፍርሃት አለ ።
ጨረቃ ሦስት መልክ አላት ። አንድዋ ጨረቃ ሙሉ ፣ ከፊል ፣ ጠፊ ትሆናለች ። እንደ ጨረቃ ሙሉ ናቸው ብለን መንገድና ሥራ ስንጀምር ከፊል ይሆኑብናል ። ግማሽ ሲሆኑብን መጠራጠር እንጀምራለን ። ሲጠፉብን ባለንበት ቆመን እንቀራለን ። ጨረቃ የጊዜ መቍጠሪያ ናት ። ሰውም ዘመን ነው ፣ ዘመንም ሰው ነው ። ሰውን እያየን ዘመኑን መገመት እንችላለን ። ብዙ አገልጋይ እንደ ጨረቃ የደመቁ ሰዎችን ይዟል ። ነገር ግን በረሀብና በጥማት ይቀጣል ። እንደ ጨረቃ የደመቁት ሰዎች አጫዋች ፈላጊ ፣ ለጨዋታችን ስፖንሰር ናቸው ። አንዳች ጥቅም የላቸውም ። የማያሞቅ ከሆነ ድምቀትን መፈለግ ጥቅም የለውም ። ጥቅም የማይሰጥ ትልቅነትን መጸየፍ ያስፈልጋል ። በሬሳ መካከል ቆንጆ መኪና ቢነዱ ደስ እንደማይል ለወገኔ የማልጠቅም ከሆነ እንዴት እየኖርሁ ነው ብዬ ራሴን መገምገም አለብኝ ። ሚሊየኖች እያጣጣሩ ያንተ ውበትና ከፍታ ሞገስ የለውም ።
ደምቃ እንደማታሞቅ ጨረቃ ከመሆን ፣ ሳትታይ እንደ ፀሐይ ብታሞቅ ይሻልሃል ፣ ምረጥ !
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሰኔ 10 ቀን 2017 ዓ.ም.