“ውኃ ሲጠራ ተሻገር ፣ ዳኛ ሲገኝ ተናገር”
በኖኅ ዘመን እግዚአብሔር ምድርን ይቅር እንዳላት ምልክቱ የውኃው መጕደል ነበር ። ውኃ ሲጎድል መርከብ ማረፊያ ፣ እግርም መርገጫ አገኘ ። ላዳነው አምላክ ኖኅ መሥዋዕትን አሳረገ ። እንደ ውኃ ወዳጅ የለም ፣ ውኃ ጥፋት ሲሆን ግን መላሽ የለውም ። ደጎችን እንዳናከፋ መጠንቀቅ ይገባናል ። በምድር ላይ እጅግ ክፉ የሚሆኑት ደግነታቸውን ያስጣልናቸው ሰዎች ናቸው ። አረመኔ ነገሥታት ፣ ጨካኝ ሰዎች ሁሉ የቀደመ ጠባያቸው ብቻ ሳይሆን ጠባይ የሰጠናቸው ሊሆኑ ይችላሉ ። “ቸር ሲያጠቁት ቢስ ይሆናል” ይባላል ። ያጠቃናቸው ደጎች ፣ ለራስህም አስብ ያላልናቸው ቸሮች የከፉ ቀን የበላነውን ያስተፉናል ። የአፍቃሪ ሰው ቍጣ ከፍ የሚለው ለመውደድ የተጠቀመውን ኃይል ለጥላቻ ስለሚጠቀመው ነው ። አፍቃሪ ሁሉ አፍቃሪ ፣ ቸርም አዛኝ ይፈልጋሉ ። ይህ የተፈጥሮ ፍላጎት ነው ። እግዚአብሔርም ፍቅር ነውና የሚወዱትን ይፈልጋል ። ምላሽ የማይፈልግ ግዑዝ ብቻ ነው ። የውኃን ጥፋት ለማየት በዘመናችን ያየነው የሱናሚ አደጋ አስረጅ ነው ። በቅጽበት ስፍራዎች ተገለባብጠዋል ፣ ከአራት መቶ ሺህ በላይ ሰዎች ሞተዋል ። የብስ ላይ የነበሩ መኪናዎች ባሕር ገቡ ፣ ባሕር ላይ የነበሩ መርከቦች መሬት ላይ ረገጡ ። እሳት እንኳ ጊዜ ይሰጣል ፣ ውኃ ግን በቅጽበት ብዙ ጥፋት ያስከትላል ። ውኃ መንገደኛ ነው ። ተሰባስቦ ሲጓዝ በመንገዱ ፊት የሚቆመውን አይወድም ። ጠራርጎ ይወስደዋል ። የውኃ ዕድሜ አጭር ነው ። ትንሽ መታገሥ አለመቻል ግን ጥፋቱ ከፍ ያለ ነው ። የሰውም ቍጣ ለጊዜው ነው ፣ ትንሽ መታገሥ ፣ በመልካም ቃላት ማብረድ የሚቻል ነው ። ከዚያ በኋላ ተጸጽቶ ይክሰናል ፣ ከጥፋት አዳንከኝ ብሎ ያመሰግነናል ።
ውኃ ሲጎድል እየጠራ ይመጣል ። ውኃን መሻገር ጠርቶ ወለሉ ሲታይ ነው ። በልጅነታችን ወላጆቻችን እጆቻችንን ይዘው ይሄዳሉ ። ይበልጥ የሚይዙን የመኪና መንገድ መሻሪያ ላይ ነው ። ያን ጊዜ እጆቻችንን ልቅም አድርገው ይይዛሉ ። መያዝ ብቻ ሳይሆን አጥብቀው ይይዙናል ። በዓይኖቻቸውም ግራና ቀኙን ያዩልናል ። እኛ የሚረብሸን እጃችንን መያዛቸው ነው ። የእኛ ባልሆነ መንገድ ፣ በወንዙ መሐል እንዳለን አናውቅም ። አንዳንድ ጊዜ መኪናው እየተቃረበ ከመጣ ተሸክመው ያወጡናል ። የሚያሻግር አባት አለን ። እርሱም እግዚአብሔር ይባላል ። እጆቻችንን ይዞ ያሻግረናል ። ከዓይነ ሞት በዓይኖቹ ይከላከልልናል ። እጆቻችንን ስለያዘን ከፍቶን ይሆናል ። ይህ የሚገባን ስንበስል ፣ በሃይማኖት ስናድግ ነው ። እግዚአብሔር እንድንተርፍ አድርጎ ይዞናል ። ዛሬ ፍላጎቶቻችን ሁሉ ቢሟሉ እንሞት ነበር ። እግዚአብሔር በኖኅ ላይ በርን እንደ ዘጋበት ፣ እኛም በመክፈት እንደ ባረከን በመዝጋትም ይባርከናል ። ቀኖቹ ክፉ ቢሆኑ ፣ ከቁጥጥራችን ውጭ የሆኑ ችግሮችም ቢዘንቡ እግዚአብሔር ግን እጆቻችንን በእጆቹ ይዞ ያሻግረናል ። መያዛችን ላያስደስተን ይችላል ። ስለማናውቅ እግዚአብሔር በእውቀቱ ያድነናል ። ከአዲስ አበባ ተነሥቶ ጥቂት እንደ በረረ ደብረ ዘይት ላይ የተከሰከሰው አውሮፕላን ያመለጠው ተሳፋሪ እጅግ ተበሳጭቷል ። ጥቂት ቆይቶ ግን በዘመኑ ሁሉ የሚተርፍ የምስጋና ርእስ አግኝቷል ።
ውኃ ሲጎድል ፣ ውኃ ሲጠራ መሻገር መልካም ነው ። ጥቂት ትዕግሥት ማጣት ዘላቂውን ሕይወት ያበላሻል ። ለመናገር ደውለን ስልኩ ስላልሠራ ቆይተን እግዚአብሔርን አመስግነናል ። ንግግር እንጂ ዝምታ ብዙ ጊዜ አያጸጽትም ። እነዚህ ቀኖች አስቸጋሪ ናቸው ። በክፍለ ዘመን የማይሰሙ መዓቶች በወራት ውስጥ ይሰማሉ ። ሁሉም ሰው ነገር ገብቶታል ፣ ጉዳይ ተሰጥቶታል ። የምድር ገዥዎች የሰው ማረፍ እየረበሻቸው ዜጎቻቸውን በብዙ ማስጨነቅ ይዘዋል ። ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋ እስክንደናገር ፋታ አሳጥቶታል ። በዚህ ጊዜ ትዕግሥትን መለመን ሀብት ከመለመን በላይ ነው ። ከመጣውም ከሚመጣውም መዓት አሻግረኝ እያሉ መጸለይ የብልህ መገለጫ ነው ። በወፈፌ ዘመን ጠቢብ ሁኑ !
መናገርም ዳኛ ሲገኝ ነው ። አድር ባይ በበዛበት ፣ የዘመን ተለጣፊ በበረከተበት ፣ ተመሳስሎ መኖር ሥልጣኔ በመሰለበት ፣ ሰው ከሰውነቱ መንደሩን ባመለከበት ዘመን መናገር ጥቅም የለውም ። የምናገረው ውጤት ያመጣል ወይ ( ብለን ለክተን መናገር በጊዜ አቅም እንዳንጨርስ ያደርገናል ። ስናገር ይቀለኛል እያለን ይበልጥ እንቀጣጠላለን ። ባልበላ ሆዳችን ከበሉ ጋር መነጋገር ራስን ማድከም ነው ። “ይሁና ሰው ሲገኝ እናወራዋለና” ይሉ ነበር ወላጆቻችን ። መልስ አለኝ ምላሽ ግን አልሰጥም ብሏል ሰውዬው ። ዳኝነት ፣ የቅን ፍርድ እንኳን ከዓለም ከቤተ እግዚአብሔርም እየጠፋ ነው ። እንደ አራዊት በገዳይነት ያሸነፈ የበላይ የሚሆንበት መንገድ ላይ ነን። ሊቃውንት እውቀታቸውን ሽምጥጥ አድርገው ክደው ሰው የሚፈልገውን እያቀረቡ ነው ። እውነት እየተከሰሰች ውሸት በነጻ እየተለቀቀች ነው ። መሃይምነት ጊዜ አግኝታ ሰውን ሃይማኖተኛ እያሰኘች ነው ። ዳኛ የለም ። ለነፍሱ ፣ ለዘላለም መግቢያው ብሎ እውነትን እውነት የሚል እየጠፋ ነው ። የሃይማኖት ልብስ እንጂ የሃይማኖት ልብ የለንም ። መናገር ማባከን ነው ብለው አዋቂዎች ዱዳ ሆነዋል ።
ትዕግሥት ፣ ጊዜውን ያየ ዝምታ ያስፈልጋል ። ከሁሉ በላይ እግዚአብሔር እንደሚያሻግር ማመን ልብን ይደግፋል ። በሞት ጥላ መካከል በደኅንነት ልጆቹን የሚመራ ጌታ ዛሬም በሥራ ላይ ነው።
ያቺ መልካም እጁ ዛሬ ትዋሰን ! አሜን ።
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ግንቦት 29 ቀን 2017 ዓ.ም.