የትምህርቱ ርዕስ | ቍጣ -7

የቍጣ ውጤቶች

እርዳታ አያገኝም

ቍጠኛ ሰው ቢታመም ፣ ቢጎዳ ቀርቦ ለማገዝ የገዛ ቍጣው መሰናክል ይሆናል ። ልጅን እንኳ ስናሳድግ ሰውን እንዲቀርብ አድርገን ካሳደግን እረፍት እናገኛለን ። እኛ ብቻ የምንሸከመው ኃይለኛ ልጅ ከሆነ እየተጎዳን ፣ እየሰለቸንና እየሰጋን እንመጣለን ። ልጅን ማኅበራዊነትን አላብሰን በፍቅር ማሳደግ የእኛን ጫና እየቀነሰ ይመጣል ። ደግሞም ልጅ ሁልጊዜ ከእኛ ጋር አይኖርምና ትሑት ሁኖ ማደግ ይገባዋል ። “የሰው አገሩ ምግባሩ” እንዲሉ የትም ለመኖር ጠባይ አስፈላጊ ነው ። ቍጠኛ ሰው ሁሉም ሰው እንደ ተሳሳተ እርሱ ግን ብቸኛ ልክ እንደሆነ እያሰበ ይመጣልና ራሱን ማራቅ ይጀምራል ፣ ሰዎችም እየራቁት ይመጣሉ ። በጣም ለስላሳ በጣምም ሸከራ መሆን ተገቢ አይደለም ፤ ለዘብተኛ ሰው መሆን ግን አስፈላጊ ነው ። ቍጠኛ ሰው ሕመም ሲገጥመው የበለጠ ቍጠኛ ይሆናል ። አንዳንዴ ካልሞተ በቀር የቅርብ ሰዎቹ ላይመጡ ይችላሉ ። መረታት ሲመጣ በድንገት እጅ ይሰጣል ፣ ተለማማጭና ፈሪ መሆን ይጀምራል ። በደግ ቀን ያላስቀመጡት በክፉ ቀን አይገኝምና ሰዎችን በአግባቡ መያዝ ይገባል ። ሁልጊዜ ጉብዝና የለም ፣ የመድከም ቀን አለና ።

ልጆች ድብቅ እንዲሆኑ ያደርጋል

በምድር ላይ ልጅን መክሰር ትልቅ ጉዳት ነው ። ምክንያቱም አንበሳም ለልጅዋ አዛኝ ናት ። ልጅ እንኳን ሰውን አውሬን የሚያሸንፍ ተፈጥሮአዊ ፍቅር አለው ። ለልጆች ወላጅ ብቻ ሳይሆን ጓደኛም መሆን ያስፈልጋል ። ልጆች ይህን ዓለም የሚጎበኙት በእኛ መሪነት ነውና ሁሉን ማሳወቅ አለብን ። ሰው ከመውለዱ በፊት የሕይወት እውቀትን መጨበጥ አለበት ። ወላጅ ለልጁ የሥጋው ብቻ ሳይሆን የነፍሱም ወላጅ ነውና ለሥጋው እንጀራ እንደሰጡ ለነፍሱም እውቀትን ፈሪሀ እግዚአብሔርን ማስጨበጥ ይገባል ። ልጆች ምንም ቢያጠፉ እኛን መደበቅ የለባቸውም ። የሚረዳቸው ግልጽ ሲሆኑ ብቻ ነው ። እንደ ትንሽነታቸው ብዙ ስህተት ውስጥ ሊወድቁ ይችላሉ ። ቍጠኛ ከሆንን ድብቅ እየሆኑ ስለሚመጡ የምናውቀው ሁሉም ነገር ካበቃ በኋላ ነው ። ልጆች ሰው በመሆናቸው ደካማ እንደሆኑ መቀበል አለብን ። ግንኙነታቸውም ከእኛ ጋር ብቻ ሳይሆን ከመላው ዓለም ጋር ነውና ሌላ ትምህርት ሊማሩ እንደሚችሉ መረዳት አለብን ። ልጆች ሁሉንም ነገር ሲነግሩን እንደ ወላጅ ሳይሆን እንደ አማካሪ ራሳችንን ማዘጋጀት አለብን ። የሚነግሩን መንገድ ፈልገው ሊሆን ይችላልና ቍጣን ማራቅ አለብን ። ቍጠኛ ሰው ልጁን ይከስራል ። በቍጣ ምክንያት ደንባራ ፣ ሰውን የሚፈሩ ከሆኑ አንድ ቀን ለዚህ የበቃሁት በእናንተ መጥፎ አስተዳደግ ነው ብለው ይወቅሱናል ። ያን ጊዜ ለፍቶ መናነት ይሰማናል ።

ጯኺነት

ቍጣ ጩኸትን ይወልዳል ። በመጮህ ውስጥ ራሳችንን በብርቱ እንጎዳለን ፣ የማናውቃቸውን ውስጣዊ ዕቃዎች እንሰብራለን ። ሌሎችንም የመቆም አቅም እናሳጣለን ። ነገሮችን በየጊዜው ማረም ፣ እርምጃዎች መውሰድ ፣ በመጨረሻ መወሰን መልካም ነው ። ሰዎችን እንደ እኔ ሁኑ ማለት አይቻልም ። ምርጫቸው እንደዚያ ከሆነ ከእኔ ጋር መኖር አልቻልንም ምናልባት ይህ ጠባይ ሊስማማው የሚችል ሌላ ይኖራልና ሂዱ ብሎ መሸኘት ይገባል ። ምክንያቱም ጩኸት ያለበት ኑሮ ሁሉንም ከማወክ በቀር አንዳች ጥቅም የለውምና ። ደግሞም ጩኸት የመጨረሻ ውጤት በመሆኑ ቀድሞ ያለውን እኛ እናውቀዋለን ፣ ሰዎች ግን የአሁኑን ጩኸት ብቻ በመስማት ይገምቱናል ። የምንጮህባቸውም ቲያትር በመሥራት ጭምት መስለው ይታያሉ ። ይህችን አንድ ሕይወት በማይረቡ ነገሮች ማጨናነቅ አይገባንም ። አንዳንድ የሚጎዱን ሰዎች እነርሱ መሄድ ፈልገው እኛ በእልህ የያዝናቸው ይሆናሉ ። ሊሄድ የፈለገን መያዝ ብርቱ ጉዳት ያመጣል ። ቍጣ ጩኸትን ስለሚያመጣ ሰብአዊ ክብርን እንድንጥል ያደርገናል ።

ይቀጥላል
የካቲት 21 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ