የቍጣ ውጤቶች
ስድብ
ስድብ ከማኅበረሰቡ የምንወርሰው ነው ። ስድብ ከበቀል መሣሪያዎች አንዱ ነው ። ዱላ አካልን ሲጎዳ ፣ ስድብ ግን ለሕሊና ስብራት የሚተኮስ ጥይት ነው ። ስድብ ሕፃናት ገና በለጋነታቸው የሚፈልጉት ነው ። ሕፃናት ከሁሉም ነገር ይልቅ ስድብን መያዝ ይችላሉ ። የሰሙትን ስድብ መርሳት ያቅታቸዋል ። ወላጆችም ይሸማቀቃሉ ። ሕፃናት የፈለጉትን ነገር ሲከለከሉ ወይም ሲቀጡ በስድብ ንዴታቸውን መግለጥ ይፈልጋሉ ። ስድብን ማስጣል ሲያቅተን ብርቱካን ብለህ ተሳደብ እንላለን ። ብርቱካን ብለው ቢሳደቡም ውስጡ ግን ስድብ እንዳለ ሰሚው ያውቀዋል ። የትዳር አጋራችንን ፣ ሠራተኞቻችንን ፣ ሌሎችንም የቤተሰብ አካላት ስንሳደብ የሰሙ ልጆች ስድብን የበቀል መሣሪያ ወይም የማናደጃ መንገድ አድርገው ይጠቀሙበታል ። አንድን ሕንፃ ቆመን ብንተቸው ሕንፃውን ሳይሆን ሠሪውን እየተቸን ነው ። እንዲሁም ሰውን ስንሰድብ ሕንፃ ሥላሴ ነውና ሠሪውን እየሰደብን ነው ። ስድብ ዓይን የለውምና ሰውዬውን ስለ ጠባዩ ብቻ ሳይሆን ስለ ተፈጥሮው ጉድለቱም ማሸማቀቅ ያለበት ነው ። ዓላማው ያ ሰው እንዳይነሣ ማድረግ ነው ። ከእግር ስብራት የሕሊና ስብራት ይበልጣልና ሕሊናውን የተጎዳ ሰው መራመድ ይቸገራል ። ሰው የመለወጥ ተስፋ ያለው ነውና በጉድለቱም መስደብ አይገባንም ። በተፈጥሮው ችግርም መስደብ ሠሪው ጌታ ላይ ጠላት ማነሣሣት ነው ። ፍጡርን በፈጣሪ ላይ ማሳመፅ ነው ። ምነው ጌታዬ እንዲህ አድርገህ ብትሠራኝ ስድብ አተረፍሁ ብሎ ፈጣሪውን ያማርራል ። ቍጣ በውስጡ የበቀል ጥማት አለውና ስድብን ይወልዳል ። ቡጢ ከሚሰነዝረው ይልቅ የሚቀበለው ላይ ክብደት አለው ። ስድብም እንዲሁ ነው ። ተሳዳቢነት በቆሻሻ የሰውን ልብስ መበከል ነው ።
ከሰው ጋር በሰፊው የሚያገኛኝ ሥራ ያላቸው ተሳዳቢ ይሆናሉ ። ከሰው ጋር በኖርን ቍጥር የምንወርሰው ብቻ ሳይሆን የምናወጣውም ጠባይ አለ ። ቅድስና የምንለው ነገር ለእግዚአብሔር ከሚገባው ያነሰውን ማቅረብ ፣ ለሰው ደግሞ ከሚገባው የሚተልቀውን መስጠት ነው ። ከሁሉ በላይ ለራስ ክብር ሲባል ስድብን ማራቅ ይገባል ። “ተንጋለው ቢተፉ ተመልሰው ካፉ” ይባላል ። ስድብ የመሸነፍ ውጤት ነው ። በዚህ ዘመን ትልልቆችን በመሳደብ ትልቅ የሚኮን የሚመስላቸው ሰዎች እየበዙ ነው ። ተሳዳቢነትም የሐቀኝነት ምልክት እየሆነ ነውና ሚዛን አልባ ዘመን ነው ።
መራርነት
ሁልጊዜ በሚነድ እሳት ፣ በሚቀጣጠል ወላፈን ፣ ባይጠፋ ፍም ውስጥ መኖር ቍጠኝነት የሚያመጣው ነው ። ቍጣ ወደ መራርነት ያደርሳል ። መራር ሰው ፊቱ አይፈታም ፣ ደግ አይናገርም ፣ ዓይኖቹ ይጋረፋሉ ። ሳይነኩት ለቅድመ መከላከል ብሎ ይተኩሳል ። በኃይለኛ ንግግሮች አፍ ያዘጋል ። በምንም ነገር የማይደሰት ፣ ለሌላው መልካም ለማድረግም አይገባቸውም ብሎ የሚያስብ ሲደረግለትም በደስታ የማይቀበል ነው ። ሁሉንም ነገር በጉድለት ጎኑ ይገመግመዋል ። ከክፉ ነገር ውስጥ መልካም ማውጣት የሰውነት ጥንካሬ ነው ። መራር ሰው ግን ከደጉ ነገር ውስጥ መልካም ማውጣት ያቅተዋል ። ራሱን ብቻ ያስባል ፣ እርሱ ብቻ በጉዳት እንዳለፈ ይቀበላል ። ሌሎች መልካም እንዲያደርጉ ስለዚያ ችግረኛ አስተዛዝኖ ይናገራል ፣ ራሱ ግን ማድረግ ይፈተናል ። የተጎዳውን አይረሳም ፣ የትላንት ታሪኩ ዘመኑን በሙሉ እንደ ጥላ ይከተለዋል ። ስለ ታመመ ስለ ሞተ ሰው ጉዳዩ አይደለም ። መርዶ የሚያመጣበትን ሰው በጣም ይጠላል ። ምን አገባኝ በሚል ስሜት ይኖራል ። ምክንያቱም ሰዎች ሁሉ ለእርሱ የቍጣው ምክንያት ናቸውና ። ቍጣ ከሚያመጣቸው አደገኛ ጠባያት አንዱ መራርነት ነው ።
የትክክለኛነት ስሜት
ከልክ ያለፈ ተሳስቻለሁ ማለትና ከልክ በላይ እኔ ቅዱስ ነኝ ብሎ ማሰብ ሁለቱም የአእምሮ መዛነፍ ናቸው ። ከአእምሮ ጉዳቶች አንዱ የትክክለኛነት ስሜት ነው ። የትክክለኛነት ስሜት ያላቸው ሰዎች እንኳን መሥራትን ማፍረስንም ከእኛ ወዲያ ለሐሳር የሚሉ ናቸው ። ሁልጊዜ ትክክል ስለሆኑ ሁሉንም ሰው አያውቅም ፣ ተሳስቷል ፣ ዋጋ የለውም ብለው ይፈርጃሉ ። ሰበበኛ ስለሚሆኑ ተጸጽተው ሰውን ይቅርታ መጠየቅ ፣ የአምላክንም ምሕረት በንስሐ መማጸን አይታይባቸውም ። የትክክለኛነት ስሜታቸው ሰውን ሁሉ የተሳሳተ አድርጎ ያሳያቸዋልና ከሳሽ ይሆናሉ ። ለእነርሱ ከፍተኛ ቦታ አለመድረስም የሰዎች መሰናክል እንዳለበት ያምናሉ ። እነዚህ ሰዎች በቍጣ ምክንያት የትክክለኛነት ስሜት እንዳዳበሩ ሁሉ በማያቋርጥ ቍጣም ይኖራሉ ። በሌሎች ጸጋ ፣ ሙያና ፍቅር ለመጠቀም ይህ አስተሳሰባቸው ያግዳቸዋል ። ብቻቸውን በረሃ ላይ ቆመው ይቀራሉ ። በመጨረሻ ሕይወትን እየጠሉ ይመጣሉ ። ሰው ራሱን እንደ መልአክ አልሳሳትም ብሎ ሲያስቀምጥ የእውቀት ችግር እንዳለበት እንረዳለን ። አእምሮ ከእውቀት ነጻ ሲሆን ያንን ለመካስ ሁሉም ሰው አያውቅም ወደሚል አስተሳሰብ ይገባል ። ከፍተኛ የሆነ የንቀት ስሜትም በሚበልጡት ላይ ሳይቀር ያዳብራል ። “ከእኛ በላይ ፉጨት አፍ ማሞጥሞጥ!”
ይቀጥላል
የካቲት 23 ቀን 2018 ዓ.ም.