ቍጣን ለማብረድ
ከልኩ አያልፍም
ያለነው በልክ ዓለም ላይ ነው ። ውቅያኖስ ከየብስ ቢሰፋም ልኩን አያልፍም ። ሺህ ቤት የገነባ የሚያድረው በአንድ ቤት ያውም በጠባብ ክፍል ነው ። አመጋገቡን ፣ ስፖርቱን ፣ የኑሮ ዘይቤውን ቢጠነቀቅም ሰው ከሞት አያመልጥም ። ሞት የሰው ልጆች የመጨረሻው ልክ ነው ። ብዙ ጫማዎች ቢገዙ የሚያደርጉት አንዱን ጥንድ ነው ። ጎተራ እህል ቢያስገቡ የሚበሉት በሰሐን ነው ። ብዙ መድኃኒት ቢታዘዝም የሚወስዱት አንዱን ፍሬ ነው ። በብርታት ቢውሉ ምሽት ላይ እንደ ሞተ ሰው መተኛት የሰው ገንዘቡ ነው ። ምንም ስመ ጥር ኃያል ቢሆኑ እርጅና ያደክማል ። የትኛውም ከፍታ ላይ ቢዘሉ ወደ መሬት መውረድ አይቀርም ። ሰፊ ምድርን ቢገዙ ፣ አውራጃዎችን ሲጎበኙ ቢውሉ በጠባብ ቤት ማረፍ ግድ ነው ። ሺህ ወዳጅ ቢኖር የልብን የሚነግሩት ለአንዱ ነው ። ብዙ እውቀት ቢኖር እንጀራ የሚበሉት በተወሰነው በአንዱ ሙያ ነው ። እልፍ ፍርሃት ቢኖር የሚሆነው ከመሆኑ የማይቀር ነው ። ገዳዮች ተነሥተው እንግደል ቢሉ በሥጋ እንጂ በነፍስ ማጥፋት አይችሉም ። እስረኞችን ያሰረ ተቋም ሲሞቱ ይፈታል ። አሳዳጁ ድንበር ሲሻሩበት ይመለሳል ። አልበላም ብሎ የሚግደረደር ምሳ ቢያልፍ እራት አምጡ ይላል ። ልበ ደንዳናው በትንሽ ልጁ እጅ ይሰጣል ። ሁሉም ሰው የሚረታበት ደካማ ጎን አለው ። ያሳደደም ተሳዳጅ ይሆናል ፣ በሰው ልጅ የሳቀም ጉድ ይወልዳል ። ጊዜው የእኔ ነው ያለም ጊዜ ይከዳዋል ። አፈቀርኩ ብሎ ያበደም ጥላቻ ይፈታተነዋል ። እገሌ ካልመጣ አልበላም የሚለው አታሳዩኝ ብሎ ይመረራል ። በጭንቅ የተያዘም በሞት ያርፋል ። መኖሪያ ያጣም መቃብር ያገኛል ። መኖሪያ የነበራቸውም መቃብር ይነፈጋሉ ። ክረምት በበጋ ፣ በጋም በክረምት ይገደባሉ ። ሌሊት ሲመጣ ቀኑ ይሸሻል ፣ ጮራው ሲፈነጥቅ ጨለማው ይበናል ። ሰጪው ተቀባይ ይሆናል ፣ መቀበል የሰለቸውም የሚሰጠው ይሰጠዋል ። ሁሉም ነገር ከልኩ አያልፍምና አብርደን መያዝ የሰውነት ወጉ ነው ።
ከዶፍ በኋላ ካፊያ ይሆናል ፣ ከካፊያም በኋላ መሬት ይጠግጋል ። ከቤት አላስወጣ ያለው ስድብም ያባራል ። አማርኛ የተለማመዱብንም ዱዳ ይሆናሉ ። የአሸናፊዎች ቡድን ተሸንፎ በሌላ ቡድን ይተካል ። ሕፃኑም ያድጋል ፣ ያደገውም ይጃጃል ። ንቁ ይፈዛል ፣ ሞኝም ጠቢብ ይሆናል ። የደፈረሰው ይጠራል ፣ ከወላጅ ጀርባ የማይወርደውም ፣ ቁርጡን ሲያውቅ ራሱን ችሎ ይቆማል ። ሊቃውንት በመርሳት በሽታ ይጠቃሉ ። የጌታ ልጆች ከርታታ ይሆናሉ ፣ የድሀ ልጆች እንጀራ ይጠግባሉ ። ጠዋቱ የጠረረባቸው ማታው ይዋብላቸዋል ፣ በጠዋት የበሉ ማታ ይቸገራሉ ። ያረፈደው ዓለም አይውልም ፣ የዋለው ሳቅም አያመሽም ። ከሥራ ብለው ከቤት ይወጣሉ ፣ በአደጋ ሰማይ ይደርሳሉ ። ለአጭር አቅደው ሩቅ ይደርሳሉ ። አህያ ፍለጋ ወጥተው እነ ሳኦል ንጉሥ ይሆናሉ ። አልጋ ወራሾች እነ ዮናታን በዱር ይሞታሉ ። በረኸኛው ዳዊት ይመለሳል ፣ የናቁት ከተማው ይከዳቸዋል ። ነገሥታት እስረኞች ይሆናሉ ፣ ሠራተኞች ይደክማሉ ። ቡቡዎች ጠንካራ ይሆናሉ ፣ ሰው ይጠሉ የነበሩ በሰው አገር በናፍቆት ይቃጠላሉ ። ነገረኛ ሆነው የሚላኮሱ በእስር ቤት ሆነው ጠላቴ ናፈቀኝ ይላሉ ።
አገልጋዩ ጌታ ይሆናል ፣ ጌታው ቀን ጎድሎበት ቁራሽ ይለምናል ። አገር የነሡ አገር አጥተው ይሰደዳሉ ። በአየር የበረሩ ጥርኝ አፈር ይሆናሉ ። የሠሩ ይጠላሉ ፣ ያወሩ ይከበራሉ ። በቁሙ ርኵስ የተባለ ሲሞት ቅዱስ ይሆናል ። ቅጣትም ያልቃል ፣ እስር ቤትም በር አለው ። አንድ ቀንም መቃብር በር ይኖረዋል ። እግዚአብሔር የእኔ ጌታ ልክ የለውም ፣ ፍጥረትን ግን ልክ ሰጥቶታል ። መሐሉ ቢያታግልም የመጨረሻው ግን እርሱ ነው ። ወዳጅ ቢንጣለል ከሞት ወዲያ አብሮ የሚጓዝ ወዳጅ እግዚአብሔር ብቻ ነው ። ይመጣል ያልነው ይቀራል ፣ ይቀራል ያልነው መጥቶ ውኃ ያቀብለናል ። ሞቴ ይጎዳዋል ያልነው እንደውም ይስማማዋል ፣ ያልጠበቅነው ሲያስበን ይኖራል ። ዘመዱ ጠላት ለመሆን ሲሰማራ ፣ ባዕዱ ወገን ይሆናል ። ዘመን ዱዳ ሲያደርገን አፍ የሚሆኑን ይነሣሉ ። እኛ ዝም ስንል እግዚአብሔር ይናገራል ፣ የገለጥነውን ገመና አማኑኤል ጌታ ይሸፍነዋል ። ገጽታም ይጠቁራል ፣ ውበትም ይረግፋል ፣ የገዛ መልክም ይጠፋል ፣ እዩኝ ያለ ገላም መደበቂያ ያጣል ። እንደ ደመቀ የሚኖር የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ብቻ ነው።
ከልኩ አያፍምና ሰዎችን አትፍራ ። በማስፈራሪያቸው አትገብርላቸው ። የጦርነት አዋጅም ጉዳይ ገጥሞት ይረሳል ፣ የሞት ፍርድም ጊዜ መጥቶ ይሻራል ። ጥላሸት የተቀባው ስምህም መቃብር ፈንቅሎ ይወጣል ። ሁሉም የሚወዱህ ጥግ ይዘው ነው ፣ አውላላ ሜዳ ላይ ቆመህ ቶሎ ዒላማ የምትሆነው አንተ ብቻ ነህ ። ሰዎች ለምን እንደ መጡና እንደሚሄዱ ያውቁታል ፣ ዘላለምን ጠብቀህ ዛሬ ስትከዳ የሚቆጭህ አንተ ብቻ ነህ ። ካለህ ኃጢአትህ እንደ ጽድቅ ይወራል ፣ ከሌለህ ጽድቅህ እንደ ኃጢአት ፣ እምነትህ እንደ ክህደት ይታያል ። አዳዲስ መሣሪያዎች ሲመጡ ይሞክሩብሃል ። የቀን ጎርፍ ይዞህ እንዳይሄድ ጥግህን ያዝ ። ከልኩ አያልፍም ። ገዳይም ሟች ነው ። የተለቀቀ ምላስም ይታሰራል ። ራስህን የምትጎዳው ማን ያዝንልኛል ብለህ ነው ? ያሉህ ነገሮች የሚጠቅሙት አንተ ካለህ ብቻ ነው ። የወደቅህ ቀን እኛን ሲደግፍ ወደቀ ብለው የቅርቦችህ አያዝኑልህም ። ገንዘብህ ያለቀ ቀን ወዳጆችህም አብረው ያልቃሉ ። እኮ ለማን ብለህ ነው አቅልህን እስክትስት የምትቆጣው ? ሊያቆስልህ ለመጣው ዓለም ደድረህ ጠብቀው ። ታመህ ካልጠበቅኸው የሚያሳምምህ የለም ። ደግሞ ጎበዝ ነህ እኮ እጅ አትስጥ ። እንዳንቺ ያለ ንቁ ሴት ማንም የለም ፣ እንባ ቀለብሽ የሚሆንበት ቀን ዛሬ ያበቃል ። ሁሉንም ነገር ወደ ሳቅ ፣ ወደ ፈገግታ ፣ ወደ ትምህርት ከለወጡት የሚጎዳ ነገር በዓለም ላይ የለም ።
ተፈጸመ
መጋቢት 24 ቀን 2018 ዓ.ም.