ዕድገትን ሸፍኖ ማስቀረት አይቻልም ። ዕድገትን ማውራት አስፈላጊ አይደለም ፣ ራሱ ይናገራልና ። የሚናገር ተግባር ላይ ቃል መጨመር ዋጋውን ማሳነስ ነው ። ደግነት ደምፅ አልባው ድምፅ ነው ። ተቀባዩ ሲናገረው ክብር ነው ። ዕድገትን ማነቅ አይቻልም ፣ ዛፉ ሲያድግ የቤቱን መሠረት አልፎ ይሄዳል ፣ ግንቡን እየናደ ይመጣል ። ዕድገት ኃይል አለው ። ዕድገት የማያቋርጥ ሂደት ነው ። ቁመታችን ፣ ፀጉራችን ፣ ጥፍራችን ያድጋሉ ። በዚህም ሁለት ነገሮችን እንገነዘባለን፡- የመጀመሪያው ድምፅ አያሰሙም ፣ ሁለተኛው ያለ ማቋረጥ ያድጋሉ ። እኛ ተኝተንም ዕድገቱ ይቀጥላል ። ዕድገት ሁለት ዓይነት መገለጫዎች አሉት ። የመጀመሪያው ድምፅ አልባ ነው ። የሰው ልጅ ምንም ትልቅ ራእይ ቢኖረው በተናገረው ቍጥር የማድረግ አቅሙ ይቀንሳል ። ምክንያቱም ሲናገረው አእምሮ እንደ ተደረገ ይቀበለዋልና ተነሣሺነት አይኖረውም ። ብዙ ሰው ራእዩን በመናገር ብቻ ረክቶ ይቀራል ። ንግግሩ እንዳደረገው ያህል እንዲሰማው ያደርገዋልና ። ድምፅን አጥፍቶ ሥራን መሥራት ፣ በቃል ሳይሆን በተግባር መገለጥ ተገቢ ነው ። ብዙ የሚያወሩ ሰዎች የሠሩ ይመስላሉ እንጂ አልሠሩም ። ደግሞስ የማደርገውን ለማድረግ እኮ አይገባኝም የሚል ስሜት ካለ ንግግር ይበዛል ፣ ሰው ቁርሱን በልቶ እንዴት ያወራል ? ራእይን መከወን የዕለት ምግብ ነው ። ባለሙያ ሴት ድግሷን ስትደግስ ማንም አያያትም ፣ አይሰማትም ። የድግሱ ቀን ገበታው ሙሉ ሆኖ ይታያል ። ሰነፍ ግን ስታወራ ጊዜው ይደርስባታል ፣ በር ዘግታም ትጠፋለች ። ብዙ ከማሰብ ማድረግ ጭንቀትን ያርቃል ። የሚያስጨንቁን ነገሮች ሁሉ ቁጭ ብለን ስለምናያቸው ነው ። ጥቂት እንቅስቃሴ ትልቅ ተራራን መናድ ይጀምራል ። አንድ ርምጃ ወደ ከነዓን መጓዝ አንድ እርምጃ ከግብጽ መራቅ ነው ።
የሰሎሞን ቤተ መቅደስ እስካሁን ወደር ያልተገኘለት ድንቅ ኪነ ሕንፃ ነው ። ሦስተኛው መቅደስ ተብሎ የሚጠራውና የዓለም ፍጻሜ ምልክት የሆነው ቤተ ጸሎት በዚህ የሰሎሞን መቅደስ በተሠራበት ስፍራ የሚገነባ ነው ። ታዲያ የሰሎሞን መቅደስ ሲሠራ እንዲህ ተብሎ ተጽፎአል፡- “ቤቱም በተሠራ ጊዜ ፈጽመው በተወቀሩ ድንጋዮች ተሠራ በተሠራም ጊዜ መራጃና መጥረቢያ የብረትም ዕቃ ሁሉ በቤቱ ውስጥ አልተሰማም።” 1ነገሥ. 6 ፡ 7 ። ውድ ነገሮች ጩኸትና ማስታወቂያ ፣ ግርግር ፣ እዩልኝ ስሙልኝ የላቸውም ። ሰው እያደገ ሲመጣ ከታይታና ከማስታወቂያ እየወጣ ይመጣል ። ሥራው የሚናገረውን ያህል አፍ መናገር አይችልም ። ሥራው ከተናገረም አፍ ዝም ማለት አለበት ። ብዙ ሰው ራእዩን በጸሎትም በአሳብም ለማይደግፉት በመዝራት መንገድ ላይ ቆሟል ። ዕድገት የማያቋርጥም ነው ። ፀጉር በትንሽ መጠን በየዕለቱ ታድጋለች ። የማያቋርጥ ዕድገት እንደ አብዮት የሚፈነዳ ሳይሆን እንደ ጠል በትንሽ በትንሹ የሚሄድ ነው ። ጌታችን ሥጋ በለበሰ ጊዜ ዕለቱን የሠላሳ ዓመት ጎልማሳ መሆን ይችል ነበረ ። ቀስ በቀስ አደገ ተብሎለታል ። ቀስ በቀስ ነገር ግን ያለማቋረጥ ዕድገትን ማስቀጠል ተገቢ ነው ።
ዕድገትን ማፈንም እስከ ዘለቄታው መደበቅም አይቻልም ። ሙሴን ከገዳዮች ለማስመለጥ ለሦስት ወራት ወላጆቹ ሰወሩት ። ድምፁ እየጠነከረ ሲመጣ ግን ያንን ሕፃን መደበቅ አልቻሉም ። ዕድገት ጥንካሬ ስላለው የቃልም የጉልበትም ጽናት ስለሚያመጣ እስከ መጨረሻ መደበቅ አይቻልም ። ሰዎችና አገራት ስለማደጋቸው ብዙ ይናገራሉ ። ግን ሆድን በጎመን ቢደልሉት ጉልበት ዳገት ላይ ይከዳል የሚባለው ይደርሳል ። ማደግም አለማደግም ሊሰወር አይችልም ። የጎጃሙ ገዥ ደጃች ተድላ ጓሉ እየደገሱ በየሳምንቱ በሰንበት ካህናትንና ምእመናንን ያበሉ ነበር ። እኒህ ደግ በሞቱ ጊዜ እንዲህ ተብሎ ተለቀሰ፡-
አልሞተም ይሉናል ደጃዝማች ተድላን ፣
አሁን እሑድ ሲቀር የምናውቀውን ።
ዕድገትም ባይናገሩት ራሱ ይናገራል ። ሳያድጉ አድገናል ቢሉም ጉልበት ሲከዳ ራሱ ይናገራል ። አለን ብለው ቢፎክሩበት አለመኖር ያወራል ።
መንፈሳዊ ሕይወት በልደት የሚጀምር ፣ ሰማያዊ ዓለምን በማውረስ የሚጠናቀቅ ነው ። የልደት ጠባዩ ዓለም ማያ ነው ። በሥጋ ስንወለድ ይህን ግዙፍ ዓለም አየን ፣ በመንፈስ ስንወለድ ያንን ረቂቅ ዓለም እናያለን ። ልደት ዕድገት ይፈልጋል ። የሚያድገውም ያው ሲወለዱ የነበረው ትንሹ ነገር ከፍ እያለ ይመጣል እንጂ ሌላ አዲስ ነገር አይጨመርም ። በመንፈሳዊ ልደት ያገኘነው ጸጋ አለ ። እርሱ ቀስ በቀስ እያደገ ይመጣል ። የሰው ልጅ በማያቋርጥ ዕድገት ውስጥ ሲሆን ሞቶ እንኳ በመቃብር ውስጥ ፀጉሩና ጥፍሩ ያድጋሉ ። ሞተንም የሚያድግ ሥራ አለን ። የሰው ልጅ ሞት እንዲገታው ሁኖ ጥንቱንም አልተፈጠረም ። ከሞት በኋላም የሚያድገውን ተግባር ዛሬ መጀመር አለበት ። ሰዎች ስለ ሀብታቸው ፣ ስለ ጥረታቸው ፣ ስለ ስኬታቸው ብዙ መናገር ይወዱ ይሆናል ። ዕድገት ግን ራሱ ይናገራል ።
ይቀጥላል
መጋቢት 28 ቀን 2018 ዓ.ም.