የትምህርቱ ርዕስ | ዕድገት -8

ያደገ ሰው መገለጫ

አያለቃቅስም

ማልቀስ ፈውስ ከሚሰጡ መንገዶች አንዱ ነው ። ሰው በጥልቅ ደስታ ውስጥ ሲሆን ቃላት ያጥረዋል ፣ አፉ ይለጎማል ፣ ምን ማለት እንዳለበት ይጠፋዋል ፣ ድንገተኛ ስካር ፣ የሕልም ዓለም ይጋረጥበታል ። ይንገዳገዳል ፣ ይዞርበታል ። በዚህ ጊዜ ያለቅሳል ። የጠፋውን ልጁን ሲያገኝ ፣ የናፈቀው ወዳጁን ፊት ለፊቱ ቆሞ ሲያየው ፣ ተስፋ የቆረጠበት ያ ዘመዱ አሁን አካል ነሥቶ ስሙን ሲጠራው በእንባ ይጠመቃል ። የእግዚአብሔር ውለታ ፣ የመኖር ዋጋ ፣ የናፍቆት መልስ እንባን ይጠራል ። እንባ የጥልቅ ደስታ መግለጫ ነው ። በደስታ ሲያለቅሱ አታልቅሱ ማለት አይገባም ። ከቋንቋ በላይ ለሆነ ደስታ እንባ ቋንቋ ነው ። እንባ የጥልቅ ኀዘን መግለጫ ነው ። ሰው ጉዳት ሲደርስበት ፣ ስሜቱ ሲሰበር ፣ ወዳጁን በሞት ሲያጣ ያለቅሳል ። በኀዘን ማዘን ፣ አስተዛዛኝ ሳለ ማልቀስ ካልተቻለ ቆይቶ ሊጎዳ ይችላል ። የሰው ልጅ ያጣውን ትልቅ ነገር በእንባ ቋንቋ ይገልጣል ። ሁሉም ዓለም የሚሰማው ቋንቋ ፍቅርና እንባ ነው ። ቋንቋውን የማናውቅለት ሰው ሲያለቅስ አብረን እናለቅሳለን ። አልቃሽ ያስለቅሳል ። በእውነት የማዘን ስሜትና የእንባ ሀብት ከተለየን መጸለይ አለብን ። ይህ ከሰውነት ውጭ መሆን ነውና ። በርግጥ ብዙ ውሸታሞች እንባን እንደ ማሳመኛ አድርገው ተውኔት ይሠሩበታል ። ሕዝብን ለማባባት ፣ ወንጌለ ክርስቶስን ንግድ ለማድረግ የሚያስቡ አንዳንድ ሰዎች አልቃሻነት ይታይባቸዋል ። ይህ ትክክለኛ የስብከት መንገድ አይደለም ። ስለ ክርስቶስ ፍቅር ብቻችንን ማልቀስ ከቻልን በእውነትም ከልባችን ነው ። በውይይትና በንግግር መሐል ማልቀስ እውነቱን ለመሰወር የተደረገ ሊሆን ይችላልና እንባ እስኪቆም ውይይቱ መገታት አለበት ። ዋሾ እውነት እየቀረበችው መሆኑን ሲያውቅ ረዳቴ ብሎ የሚጠራት ልቅሶና እንባን ነው ።

ማልቀስ በቦታውና በጊዜው መልካም ማስተንፈሻ ነው ። እንባን ኑሮ ማድረግ ግን አእምሮን ማበላሸት ፣ ዓይንን ማጥፋት ፣ እግዚአብሔርን መካድ ነው ። “ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ” የሚል ትእዛዝ ተሰጥቶናል ። ሁልጊዜ ሲባል እግዚአብሔር ቢገድልም ቢያድንም ሥልጣን ያንተ ነው ፣ አንተ አትሳሳትም ፣ የእኔ የሆነ ነገር ኖሮ ለምን ወሰድከው ? የማለት ድፍረት የለኝም ብሎ ማመስገን ነው ። ደስ ያለው ይዘምር ስለ ተባለ በጌታ የተደሰተም ይዘምራል ። እግዚአብሔር ሥራህ ትክክል ነው ሲሉት ይወዳል ። ያን ጊዜ ከሄደው በላይ ይክሳል ። ማለቃቀስ የስሜት ሕመም መገለጫ ነው ። ሁልጊዜ አባብሉኝ የሚሉ የማባበል ጥገኛ የሆኑ ሕፃናት ያለቃቅሳሉ ፣ እየበሉም ጡት እየጠቡም ያለቃቅሳሉ ። እኔን ልጄ ፣ እኔ እያለሁ ፣ እናትህ ትደፋልህ የሚሉ ድምፆች የጆሮ ሐሺሽ ናቸው ። ይህን የለመደ ልጅ ሱሰኛ ይሆናል ። ብዙ አባቶች ይህን ማንቀራበጥ ስለማያውቁበት እንደ ጠላት እየታዩ ልጆቻቸው ይከዱአቸዋል ። በዚህ ዘመን የአባት ድርሻ የልጆች ስፖንሰር ሁኖ ማሳደግ ነው ፤ ልጆቹ ካደጉና የወር ደመወዛቸውን ከበሉ በኋላ አባቶች ከቤት ይባረራሉ ። አንዳንድ ጊዜ እናቶችም ባለማወቅ የእናት ፓርቲ በቤት ውስጥ መሥርተው አባትን ያገላሉ ። በስተርጅና ባሎቻቸውን ጥለው ፈረንጅ አገር የሄዱ ፣ አልመጣም ብለው የተቀመጡ እናቶች ብዙ ናቸው ። “ልጅ ደረሰ ቤት ፈረሰ” የሚባለው ተረት ዛሬ ተግባራዊ ሆኗል ። ልጅ ምንም ጥሩ ቢሆን የባልን ያህል አይሆንም ። ልጅ ምንም መልካም ቢሆን ከሚስትህ አይበልጥም ። ልጅ የአካል ክፋይ ሲሆን ሚስትና ባል ግን አካል ናቸው ። በስተርጅና ልጅ ሠራተኛ ይቀጥራል ፣ ባል ወይም ሚስት ግን አብሮ ይኖራል ። ገንዘቡን ከሚሰጥና ራሱን ከሚሰጥ የትኛው ይበልጣል ?

ማለቃቀስ ያለ ማደግ የሰውን ኀዘኔታ የመፈልግ ጥማት ነው ። ማለቃቀስ ብሶት አይደለም ፣ የዛሬን ጉዳት መግለጫም አይደለም ። ማለቃቀስ በማይድን ቍስል ውስጥ መኖር ነው ። ምክንያት ኖረም አልኖረም ማለቃቀስ በራሱ በቂ ምክንያት ይሆናል ። ይህ እያደገ ይመጣና አሞኛል ወደሚል ስሜት ያድጋል ። አሞኛል ደግሞ አልጠየቃችሁኝም ወደሚል የብቸኝነት ስሜትና የመወቃቀስ ፣ የመጣላት ርእስ ይሆናል ። ማለቃቀስ ተራቡም ጠገቡም ሕይወት ሊሆን ይችላል ። ገደብ ካልተሰጠው ኀዘን ያሰጥማል ። የደረሰብን መከራ ካለም እኔ ከማን እበልጣለሁ ፣ በሁሉ የሚደርስ በእኔ ደርሶአል ብለን ራሳችንን መገሠጽ ይገባናል ። ማለቃቀስ እንደ ነሐሴ ዝናብ ፣ እንደ እኝኝ ብላ ነው ። መቆሚያ የለውም ። ካሁን ካሁን ይቆማል ሲባል ከቤት ሳይወጡ ያስቀራል ። ወይ ዘንቦ አያባራ ፣ ወይ ደርቆ አይበራ እኝኝ ብላ ያውካል ። ማለቃቀስም ርእስ አልባ ነውና መቆሚያ የለውም ። የሚፈልጉትን የማያውቁ ሰዎች ማለቃቀስ ጠባያቸው ነው ። አጠገባቸው ያለውን ሰው ማወክ ፣ በዓመት በዓል ሰውን መረበሽ ፣ ምግብ ሊበላ ሲል የነገር ቁርጥ ማቅረብ ፣ ሊጠይቁ ሄደው የሰው ሰላም ማናጋት ደስ ይላቸዋል ። እነዚህ ሰዎች ይህን ያህል ተበድያለሁ ካሉ መራቅ ይገባቸው ነበር ፣ ነገር ግን አይላቀቁም ፣ ሁልጊዜ እሮሮ ያበዛሉ ። እንደ ተበደሉ እንጂ እንደ በደሉ አይሰማቸውም ። የራሳቸውን መስጠት አይፈልጉም ፣ የሌላውን ግን ሲቀሙ ይውላሉ ። የማያቋርጥ ነቃፊ ይሆናሉ ፣ ለሰው ሁሉ ጥሩ አመለካከት ስለሌላቸው ስም ሲሰጡ ይውላሉ ። ያልወለዳችሁትን ያስታቅፋሉ ። ስለ ደረሰባቸው መከራ ሲናገሩ እነ ቅዱስ ጊዮርጊስ ምኑን ሰማዕት ሆኑት ፣ ምኑን መከራ ተቀበሉት ያሰኛል ። መከራቸውን ትልቅ ያደርጋሉ ። ስለ ጠባያቸው የደረሰባቸውን ነገር ስለ ክርስቶስ ወይም ስለ ቅንነታቸው የመጣ አድርገው ማቅረብ ይችላሉ ።

ማለቃቀስ ያለ ማደግ ውጤት ነው ። ያደገ ሰው አያለቃቅስም ። ቍስሎቹንም አማካሪዎች ጋ ሄዶ ያጠፋል ፣ የትላንት እስረኛ በመሆን ዛሬን አያበላሽም ።

ይቀጥላል

ሚያዝያ 8 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ