የትምህርቱ ርዕስ | ዕድገት -10

ያደገ ሰው መገለጫ

ያየውን ሁሉ ለእኔ አይልም

አንድን ሰው እንደምንወደው ከምናውቅበት ነገር አንዱ አለው ሳይሆን የለውም ብለን ስናስብ ፣ በልቷል ሳይሆን ርቦት ይሆናል ብለን ስናዝን ነው ። ፍቅር ለሚወደው ያዝናልና ። መተዛዘን የሌለበት የዚህ ዘመን ትዳር ፣ የራሱ ጉዳይ የሚባልበት የዚህ ዘመን ጥምረት ከሰማይ በረከት እያራቀን ነው ። እግዚአብሔርን ባማረ ምንጣፍ ፣ በተዋበ መንበር መቀበል አይቻልም ፣ እግዚአብሔርን የሚስበው የእርስ በርስ መዋደዳችን ነው ። በሰው አገር እንኳ ተሰደው ያሉ ባልና ሚስት እየተዛዘኑ አይደለም ። በዙሪያቸው ያለው የማያውቃቸው ፣ የት መጣቸውን የማይገነዘብ ፣ አንድ ችግር ቢገጥማቸው ወደ አገር ቤት የማይደውልላቸው ነው ። በሩቅ አገር የሚኖሩ ከተጨካከኑ በአገር ውስጥ ያሉት የበለጠ እንደሚጨካከኑ መገንዘብ ይቻላል ። እውነተኛ ፍቅር ለሚወደው ያዝናል ። የዘገየው ምን ገጥሞት ነው ብሎ ይሰጋል እንጂ ምን ይሆናል ( ብሎ አይደላደልም ። ፍቅር ለሚወደው ያስባል ። ለራሳችን አስበን ምግባችንን እንሠራለን ፣ ልብሳችንን አጥበን እንለብሳለን ። ለምንወደውም ያንን እናደርጋለን ። እስካሁን ድረስ ከብድር ጋር ያልተያያዘ ንጹሕ ፍቅርን የምንተረጉመው ልጆቻችን ላይ ብቻ ነው ። እነርሱም የፍቅሩ ልክ አይገባቸውም ፣ ልጆቻቸውን ይወዱ ይሆናል እንጂ መልሰው እኛን መውደድ አይሉችም ። ውኃ ሽብቅ አይፈስም እንዲሉ ልጆች ወላጆቻቸውን በሚገባቸው ልክ ለመውደድ ይቸገራሉ ። ይህ የመጀመሪያው የወላጅን ፍቅር ለመረዳት ብስለት ላይ አለመድረስ ሲሆን ሁለተኛው የወላጅ ፍቅር ሲገባን ወላጆች በሕይወት ስለማይኖሩ ነው ። ያልተመለሰ ፍቅር ቁጭት ሆኖ ይቀራል ።

ልጆች ስናሳድግ ለወንድም ለእኅታቸው እንዲያስቡ አድርገን ሊሆን ይገባዋል ። ያለውን ምግብ ሁሉ ገልብጦ የሚበላ ፣ ለወንድሙ የማያስቀር ከሆነ ራስ ወዳድ እየሆነ ያድጋል ። ለሌላው ማሰብን እንዲለማመድ ፣ የራሱንም ድርሻ እንዲያውቅ መንገር ያስፈልጋል ። ልጆች ሁሉ ለእኔ የሚል የስግብግብነት ጠባይ ይታይባቸዋል ። እነርሱን ለመውቀስ እውቀታቸው አናሳ በመሆኑ አይቻለንም ። ካደጉ በኋላ ግን የሚመዘኑበት ጠባይ ነው ። ለእኔ ብቻ የሚል አስተሳሰብ ከሁሉ ሰው ጋር ያጣላል ። ለሌላው በመስጠት ውስጥ ያለውን እርካታ እንዳያጣጥሙ ያደርጋል ። ዓለም የሁሉም ናት ። ነጻነት የምንለውም ዓለምን የጋራ ቤት ማድረግ ነው ። ሁሉም ነገር ሊኖረን አይገባም ፣ ምንም ነገር የሌለን መሆንም የለብንም ። ሁሉን ሙያ ማወቅ ፣ ሁሉን ትምህርት መማር ፣ በዚህ ቢያጡ በዚያ ለመኖር ማቀድ አስፈላጊ አይደለም ። እኛ ሁሉን ይዘነው ሰው ምን ሠርቶ ሊበላ ነው ( ከትርፎቻችን ላይ ያገዙን ሊበሉ ፣ ከድርጅቱ ዕድገት ላይ ሠራተኞችም ሊጠቀሙ ያስፈልጋል ። ያ ሲሆን ዘላቂ የሆነ ዕድገት ይኖረናል ። አንድን ተቋም ከባለቤቱ ይልቅ ሠራተኞቹ ሲጠብቁት ይሻላል ። የጋራነት ስሜትን መመሥረት ትልቅ የአስተዳደር ችሎታ ነው ።

የእኔ የሚሉ ስሜቶች በጣም እየጎዱን ነው ። አገርን ስናስብ የእኛ ብቻ ዕዳ መስላ ከተሰማችን ፣ ለቤተ ክርስቲያን ያለሁት እኔ ብቻ ነኝ የሚል ሙግት ከያዝን ከባድ ነው ። ይህ ለራሳችን ጭነት ማምጣት ሲሆን ሁለተኛ ከእውነቱ መሸሽ ነው ። ከዚህ ሁሉ በላይ ከራሳችን ውጭ ያለውን ሁሉ እንደ ጠላት መቍጠር እንጀምራለን ። አገር የጋራ ነው ። ቤተ ክርስቲያን የአማንያን ሁሉ ናት ። ከዚህ ሁሉ በላይ የክርስቶስ ናት ። የምድር ንብረትም ሁሉም በፍትሐዊነት ሊጠቀመው ይገባል ።

ሰዎች የነዱትን መኪና ሁሉ መንዳት አለብኝ እያሉ መኪና ሰብሳቢ መሆን ፣ ሰዎች የለበሱትን ሁሉ መልበስ አለብኝ እያሉ ጨርቅ ከማሪ መሆን አይገባም ። ዕቃዎቻችን መጠን ከሌላቸው ጭንቀትን የማምጣት ጠባይ አላቸው ። የጠሩ ግን ትንሽ የሆኑ ነገሮች ለሰላማችን አስፈላጊ ናቸው ። ጊዜያችንን ለመቆጠብ ፣ ንብረቱን ለመቆጣጠር ፣ ጭንቀትን ለማራቅ ትንሽ ነገር ጥሩ ነው ። ይልቁንም እውቀት ሳይኖረን ገንዘብ ከመጣ ወይ የልብስ ወይም የመኪና ሰብሳቢ ያደርገናል ። ይህ በሽታ ነው ። ከመጠን በላይ በታኝ ፣ ከመጠን በላይ ስስታም መሆን ካለመማር የሚመጣ ነውና ከገንዘብ በፊት ግንዛቤ/ገንዘብ ማለት ያስፈልጋል ። ገንዘብ እንደ አብሾ የማሳበድ ጠባይ አለውና ጌታ ሆይ የምጠቀምበትን እውቀቱን አስቀድመህ ስጠኝ ማለት አስፈላጊ ነው ።

ያደገ ሰው ያየውን ሁሉ የእኔ አይልም ። ያየውን ሁሉ ለትዳር አያጭም ፣ ካየው ሁሉ ጋር ጓደኛ አይሆንም ። ወዳጅነት እንደ አበባ በብዙ እንክብካቤ የሚያድግ እንጂ በተአምር የሚገኝ አይደለምና ያደገ ሰው የዕለት ወዳጁን ዘላቂ አድርጎ ማሰብ የለበትም ። እንኳን የማያውቁት ሰው የሚያውቁትም ሰው የማያውቁት እየሆነ ነውና ማስተዋል ይገባል ። ሁሉን መውደድ ፣ ለሁሉ ቀና ማሰብ ግን ይቻላል ። ወደ ሕይወታችን ማንን እንደምናስገባ ማሰላሰል ግን ያደገ ሰው ምልክት ነው ። ያዩትን ሁሉ ለእኔ የሚሉ ሰዎች ሰውን ከሥራው ያፈናቅላሉ ፣ በወንድማማች መካከል ጠብ ይዘራሉ ፣ የሰው ትዳር ይቀማሉ ። ለሰው ስሜት አይጨነቁም ፣ ረግጠው ያልፋሉ ። ማደግ ልክን ማወቅ ፣ በጋራ መጠቀምን መርሕ ማድረግ ነው ።

ይቀጥላል

ሚያዝያ 12 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ