የትምህርቱ ርዕስ | ዕድገት -12

ያደገ ሰው መገለጫ

የረዱትን ይረዳል

ማግኘት ደስ የሚለው ራስን ለመቻል ነው ። ራሱን ያልቻለ ግለሰብም አገርም ይናቃል ። ሦስተኛ ዓለም የሚል ስም ያሰጠን ራስን አለመቻል ነው ። የሚበዙት የአፍሪካ አገራት ከሰሐራ በታች ያሉ አገራት የሚል ስም ሲሰጣቸው ከኢኮኖሚ አንጻር ደካማ መሆናቸውን የሚገልጥ ፣ የአበዳሪዎች ስያሜ ነው ። እኛም ባለ ወግ ሆነን የድሀ ድሀ እያልን የራሳችንን ወገኖች እንጠራለን ። ራስን መቻል ያስከብራል ። ራስን መቻል ደስ ይላል ። ራስን መቻል ሌላውን ለመርዳት ያግዛል ወይም ያንደረድራልና ደስታ ይሰጣል ። ሰው ተካፍሎ ካልበላ ደስታ ሊኖረው አይችልም ። ማኅበራዊነት አማራጭ ሳይሆን ግዳጅ ነው ። ቁሳዊ ወጪዎችን የሚፈሩ ሰዎች መንፈሳዊ እርካታ እንደሚያገኙ ይረሳሉ ። ሰው ሁሉ ሞልቶት የመኖር አቅም ሊያጣ ፣ ምንም ሳይኖረው የመኖር ፍላጎት ሊያሳይ ይችላል ። ይህ የሚያሳየን ማኅበራዊነት የመንፈስ ምግብ መሆኑን ነው ። ለድሆች መርዳት መልካም ነው ፣ ከወዳጆች ጋር አብሮ ማሳለፍም ትልቅ የአእምሮ ዕረፍት ነው ። ማግኘት ደስ የሚለው የረዱንን ለመርዳት ነው ። ውለታ ዕዳ አይደለም ፣ የሕሊና ዕዳ ነው ። በዚህ ዘመን የረዱንን ከመርዳት ማጥቃት እየታየ ነው ። አውሬ እንኳ ወዳጁን አይነካም ፣ አውሬ እንኳ በልጁና በወገኑ አይጨክንም ። ሰው ግን መልካም ያደረገለትን እየጎዳ ያለበት ዘመን ነው ። የረዱንን መርዳት እፎይታን ይሰጣል ።

ነፍስ እስረኛ ስትሆን ከባድ ስቃይ ይሰማናል ። ነፍስን ከእስራት መፍታት ትልቁ ነጻነት ነው ። ነፍስ ከእስራት የምትፈታው በራሳችን ምርጫና በእግዚአብሔር ሥልጣን ነው ። “እግዚአብሔር ይፍታ” የሚል ምርቃትና በረከት ትልቅ ነው ። የሚፈታ እግዚአብሔር ሲሆን እርሱ የወኅኒንም የሲኦልንም በር መክፈት ይችላል ። ሦስት ዕዳዎች ካልተከፈሉ ነፍስ እስረኛ ትሆናለች ። የምስጋና ፣ የፍቅር ፣ የምስክርነት ዕዳ ካልተከፈሉ ነፍስ ትታሰራለች ። የምስጋና ዕዳን ለማውረድ የእግዚአብሔርና የሰው ውለታ በምስጋና መመለስ ይገባዋል ። እግዚአብሔርን በሰጠን ዕድሜ ማገልገል ፣ ሰዎችን በአቅማችን መርዳት ይገባል እንጂ ምስጋና ብቻውን በቂ አይደለም ። ተራው የእኔ ነው ብለን ማገዝ ተገቢ ነው ። ተራው የእኔ ነው ብሎ ማጥቃት ፣ ወርቅ ላበደረ ጠጠር መመለስ ተገቢ አይደለም ። ይህን ዘመን ውለታ ቢስነት እየተዋጋው ነው ። የመጨረሻው ዘመን ነዋሪ አንዱ ጠባይ “የማያመሰግኑ” የሚል ነው ። (2ጢሞ. 3፡2)። ቀምቶ ራጭ መሆን ፣ ሰበብ እየፈለጉ ያሳደጉንን ማቆርቆዝ ነውር ነው ። የተደረገልንን ብዙ ነገር ትተን ያልተደረገልንን ነገር መፈለግ ጨካኝነት ነው ። የምስጋና ዕዳ በቃልም በተግባርም መመለስ አለበት ። ውለታ ቢሶች ደጎችን ጨካኝ ያደርጋሉ ።

የፍቅር ዕዳ መከፈል አለበት ። ፍቅር በፍቅር ብቻ ይመለሳል ። ብዙዎች ፍቅርን በገንዘብ ለመመለስ ይሞክራሉ ። ፍቅር ግን ኩሩ ነውና ከራሱ ውጭ አይቀበልም ። ፍቅር ከተመን በላይ ነውና ዋጋ አይቀርብለትም ። ስጦታዎቻችን የፍቅር መግለጫ እንጂ የፍቅር ምትክ መሆን አይገባቸውም ። ለሁለት ሲሄዱ ቅርብ ነው መንገዱ ። መንገዱን ፣ የሕይወትን ጎዳና ለማሳለጥ ፍቅር አስፈላጊ ነው ። መወደድ ብቻውን ዕዳ ነው ። በዚህ ዓለም ላይ ከባድ ጭነቶች ሊኖሩ ቢችሉም ያልተመለሰ ፍቅር ግን የበለጠ ከባድ ነው ። በዚህ ቀን የሚወዱን እነማን እንደሆኑ እናስብ ። ፍቅርን መመለስ ባለመቻላችን የባለ ዕዳነት ስሜት አለን ። የጎዳናቸው መስሎ ይሰማናል ፣ እውነት ነው ። የበለጠ እኛ ተጎድተናል ። የወደዱንን ጥለን የጠሉንን እንፈልጋለን ። ስንነቃ ሁሉን እንደ ከሰርን ይሰማናል ። የፍቅር ዕዳችንን መክፈል አለብን ። ሦስተኛው የምስክርነት ዕዳ ነው ። ምስክሮች እንድንሆን ተጠርተናል ። እግዚአብሔር ያደረገልንን መመስከር ይገባናል ። በዓለም ላይ 500 ሚሊየን የሚጠጉ ቡዲስቶች አሉ ፣ አንድ ቢሊየን የሚጠጉ የሂንዱ እምነት ተከታዮች አሉ ። እስከ 2 ቢሊየን የሚጠጉ ሙስሊም ወገኖች አሉ ። እነዚህ ሁሉ ስለ ክርስቶስ ማወቅ አለባቸው ። በወንጌል አምነው የክርስትና አካል እንዲሆኑ የፍቅር ምስክርነታችን አስፈላጊ ነው ። የምስክርነት ዕዳ አለብን ። ይህንን ዕዳ አለመወጣት ፣ ወንጌል እንዲስፋፋ አለመርዳት ነፍስን ያስጨንቃል ።

ማደግ የረዱንን መርዳት ነው ። የወላጆቻችን ውለታ ብዙ ነው ። እኛን ለማሳደግ የራሳቸውን ሕይወት ሰርዘዋል ። እስካሁን ድረስ ያልተፈተነው የወላጅ ፍቅር ነው ። በእውቀት ያገዙንን ፣ አንቱ ያሰኙንን ፣ የምንናገረው እንዲኖረን ያደረጉንን ምሁራን መርዳት አለብን ። ብዙዎቹ በዕድሜም በቀቢፀ ተስፋም ተዳክመዋል ። ከጭንቀታችን እንድንወጣ የረዱን ዛሬ ተጨንቀዋል ፣ ታስረን የጠየቁን ዛሬ ተግዘዋል ። እግዚአብሔር በጎ ዕድል የሚሰጠን ዕዳችንን እንድንከፍል ፣ ነፍሳችንን ነጻ እንድናወጣ ነው ። ልጆቻችንን ያሳደጉ ሞግዚቶች ሳይወልዱ ፣ የራሳቸውን ትዳር ሳይመሠርቱ ቀርተዋል ፣ እነርሱን መርዳት የትልልቆቹ ብቻ ሳይሆን ያደጉት ልጆች ተግባርም ነው ። ለነገሩ ያገለገሉንን ፈረሶች በየሜዳው ጥለን የጅብ ሲሳይ አድርገናቸዋል ። እንኳን ያገለገለ ሰው ያገለገለ ውሻም አረጀ ተብሎ አይጣልም ። የሰውነት ልኩ ይህ ነው ። በእውነት ሰው እንሁን ።

ይቀጥላል

ሚያዝያ 16 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ