ያደገ ሰው መገለጫ
መራራ ነገርን ያጣጥማል
ፈተና ራሳችንንና ሰዎችን የምናወቅበት ትልቅ ባለውለታ ነው ። ፈተና ለጊዜው መራራ ነው ፣ ቆይቶ ግን ይጣፍጣል ። እነዚያ ቀኖች እንዳይሆኑ ብዙ ሰጋን ፣ ስጋት አንዳንድ ነገሮችን አያስቀርምና ሆኑ ፤ በሆኑ ጊዜ በብርቱ አለቀስን ። አሁን ግን እንኳን ሆኑ ብለን እንዘምራለን ። ፈተና ድልድይ ነው ። ድልድይን ይሻገሩበታል እንጂ አይኖሩበትም ። ፈተናም ለጊዜው እንጂ ለዘላለም አይደለም ። በሚያልፈው ፈተና የማያልፈውን ትምህርት እናገኛለን ። ፈተና አላዋቂዎችን ፣ ግብዞችንና ጥቅመኞችን ከእኛ የሚያርቅ የዕድሜ ማትረፊያ ነው ። ፈተና መምህሩ ተማሪዎቹን ያውቅበታል ፣ የራሱንም ማንነት ይገመግምበታል ። ፈተና በመጣ ሰዓት ጴጥሮስ ካደ ፣ ይሁዳ ጌታው ሸጠ ። ፈተና ከሁሉ በላይ ደቀ መዛሙርትን ያበጥራል ። አንዳንዱ ክዶ የሚመለስ ነው ፣ ሌላው ሸጦ የሚቀር ነው ። ማንኛውም ትክክለኛ እርምጃ የሐሙስ ማታውን ጴጥሮስና ይሁዳን ያስከትላል ። ለሚመለሱት በሩን ገርበብ ማድረግ ፣ ሄደው የሚቀሩትን መተው ይገባል ። ፈተና ሁሉም ፍጥረት የሚገጥመው ነው ። መላእክትም በመልአክ ተፈትነዋል ። የጸና ፣ የተጠራጠረና የወደቀ ተገኝቶባቸዋል ። ፈተና ሳጥናኤልን ዝቅ ሲያደርግ ፣ ታማኙን ደግሞ ሊቀ መላእክት ያደረገ ነው ። ፈተና ለታላቅ ክብር ፣ አሊያም ለታላቅ ውርደት የሚመጣ ነው ።
ወርቅ ይፈተናል ። መፈተኑ ከአፈር ተለይቶ ከከበረ አካል ላይ ለመቀመጥ ነው ። ማርም ይፈተናል ። በእሳት ይፈትኑታል ፣ ሰም ከሸተተ መልካም ነው ፣ ስኳር ከሸተተ የተደባለቀ ነው ይባላል ። ይህ ብቻ አይደለም ውኃ ውስጥ ሲገባ ክብደት ካመጣ እውነተኛ ነው ። እውነተኛ ያልሆነ ይንሣፈፋል ፣ ፈተና ብዙ መሳይ ሰዎችን ያቀላል ። ፈተናን የሚያልፍ መሆን ብቻ ነው ። እውነት በፈተና ፊት ትጸናለች ። ፀሐይም በደመና ትፈተናለች ። እርስዋ ከደመና ጋር ስትታገል ዋጋዋ በምድር ይታወቃል ። ሁልጊዜ መገኘት ሁልጊዜም መታጣት መልካም አይደለም ። እንዳያቀሉን ሁልጊዜ መገኘት ፣ እንዳይረሱን ሁልጊዜ መጥፋት ተገቢ አይደለም ። ፈተና የዘላቂ ጓደኝነት መመሥረቻ ሰነድ ነው ።
“ያጣም ያገኝና ያገኘም ያጣና
ያስተዛዝበናል ይህ ቀን ያልፍና” የሚባለው ለዚህ ነው ። ብዙ የተከበሩ ሰዎች በአጉል ቀን በተናገሩት አጉል ንግግር ሙሉ ዘመናቸውን አርክሰውታል ፣ አንዳንዶችም ቀብራቸውን አበላሽተዋል ። የፈተና ሰዓት ጥቂት ናት ፣ የዘላለም ስም ግን ታሰጣለች ። ሕንፃ ይፈተናል ፣ በራሱ መለኪያ ደኅንነቱ ይረጋገጣል ። ያላለቁ ቤቶች ሲገዙ መፈተን አለባቸው ። ደካማ መሠረት ከሆነ ፣ ፀሐይና ርጥበት ከጎዳው ቤቱን አይሸከምም ። ሰዎች የሚተማመኑብንና ከእኛ ጋር ተረጋግተው የሚኖሩት መፈተንን ስናውቅ ነው ። የተፈተነ ሰው ሌላውን መርዳት ይችላልና ፈተና ለእርዳታ ሰጪነት ይመጣል ።
ፈተና ፍርሃት አለው ። ከመከራው ጭነት በላይ የመከራው ስጋት ይጎዳል ። መከራው የመጣ ቀን ረድኤተ እግዚአብሔር ይመጣል ፣ ደካማ የሚመስለው ሰውም ጠንካራ ሁኖ ይታያል ። እግዚአብሔር ሲያመጣው ከመቻያው ጋር ነውና ። ደግሞም “ከሰማይ የመጣ ለምድር አይከብደውም” ይባላል ። እግዚአብሔር ሲያሸክም እኔ አልችልም አይባልም ፣ እርሱ አቅማችንን ያውቀዋልና ። ፈተና ጥርጣሬ ፣ የመኖር ስጋትን ያመጣል ። እግዚአብሔር ቢወደኝ እንዴት ለዚህ ተወኝ ? ያሰኛል ። አባት የሚወደው ልጁን ለቀዶ ጥገና ፈርሞ ይሰጠዋል ። ልጁን ስለማይወድ ሳይሆን የበለጠ ስለሚወደው ነው ። እያንዳንዱ ፈውስ የሕመም ሂደት አለው ። ከዘላቂው በሽታ ለመዳን ጊዜያዊውን የፈውስ ሕመም መታገሥ ይገባል ። ገበሬ ስለት ይዞ በወይኑ ዙሪያ ይንቀሳቀሳል ። የደረቀውን ሊያስወግድ እጁን ይሰነዝራል ። ፈተና የደረቁና የሞቱ ነገሮቻችን እንዲወገዱ ያደርጋል ። ከትምህርት ቤት በላይ ፈተና ብዙ ያሳውቃል ። ፈተና ሲመጣ አሉኝ ያልናቸው ነገሮች አለመኖራቸውን ፣ የለኝም ያልነው ነገር መኖሩን እናረጋግጣለን ። ፈተና የእውነት አውጫጪኝ ነው ።
ሕፃን ልጅ ስኳርን ሲያጣጥም ፣ ያደገ ግን መራራን ያጣጥማል ። ከመከራው በላይ መከራ የሚሰጠውን ትምህርት ተጠንቅቆ የሚማር ያደገ ሰው ነው ። እያንዳንዱ ችግር ከፍታ ይዞ ይመጣል ። ሌሊት በቀን ይተካል ። የፈተና ዘመንም በደስታ ዘመን ይለወጣል ። ይህን እንደማልፈው እርግጠኛ ነኝ እንበል ። እንጸልይ ፣ ቃለ እግዚአብሔርን እንስማ ። ከገደሉ ለመውጣት የተንጠለጠለው ገመድ ፣ የተሸረበው ፈትል ቃሉ ፣ ጸሎትና ኅብረት ነው ።
ይቀጥላል
ሚያዝያ 23 ቀን 2018 ዓ.ም.