ያደገ ሰው መገለጫ
ሌሎችን ማወክ ያቆማል
በአገራችን የነበረው የልጆች አስተዳደግ ከአሁኑ ዘመን ጋር ተነጻጽሮ ሊጠና ይገባዋል ። የቀደመው የልጆች አስተዳደግ እንግዳ ሲመጣ ፣ አዋቂዎች ሲጫወቱ ልጆች ወደ ጓዳ ግቡ ይባል ነበር ። አዋቂዎች ስለ ብዙ ነገር ይጫወታሉና ልጆች ያንን ሰምተው አእምሮአቸው እንዳይበከል በማሰብ ነው ። ልጅነት ይህችን ዓለም እንደ ገነት የሚኖሩበት የዕድሜ ምዕራፍ ነው ። ዛሬ ልጆች ከአዋቂዎች ጋር ተቀምጠው ሁሉንም ይሰማሉ ፣ የወላጆቻቸው ጠብ ላይ ገላጋይ ይሆናሉ ። ያለ ጊዜአቸው ብዙ ክፉ ነገሮችን እያወቁ ያድጋሉ ። በሰዎችና በጎሣዎች ላይ ጥላቻን ይዘው ከፍ ይላሉ ። በቀደመው ዘመን ልጆች እንግዳ ሲመጣ ሰላምታ እንዲሰጡ ፣ እጅ እንዲነሡ ይደረጋሉ ። በዚህም አክብሮትንና ፍቅርን ይማራሉ ። የመጣው እንግዳ ወንድ ከሆነ አጎትህ ነው ፣ ሴት ከሆነች አክስትህ ናት ፣ የክርስትና አባት ከሆነ አባትህ ነው… ይባላሉ ። በዚህም ብዙ ዘመድ እንዳላቸው እያሰቡ ልበ ሙሉ ሁነው ያድጋሉ ። ጨዋታ ሲጀመር ወደ ጓዳ የሚገቡት ንጹሕ አእምሮአቸው እንዳይበከል ለመጠበቅ ነው ። ዛሬ የምንለፋባቸውን ልጆች የገዛነው ቴሌቪዥንና ፣ የሰጠናቸው ስልክ ወስዶብናል ። ልጆች ያ እንዲሰጣቸው ያውካሉ ፣ እኛም ሰላም ለማግኘት ብለን ስልኩንና ቴሌቪዥኑን ስንፈቅድ ልጆች የወደፊት ሕይወታቸውን የሚሰርቅ ነገር ውስጥ ይገባሉ ።
ልጆች በተለያየ መንገድ ያውካሉ ። የመጀመሪያ ሲርባቸው ነው ። ሁለተኛው ሲቆሽሹና ምቾት ሲያጡ ነው ። ሦስተኛ የረሳናቸው ሲመስላቸው ነው ። አራተኛ የሚፈልጉትን ብልጭልጭ ነገር ለማግኘት ነው ። አምስተኛ ለሌሎች ትኩረት ሰጥተን ስናወራ ነው ። የሚገርመው ልጆች ሲታመሙ አያውኩም ። ሲታመም የሚያውክ ያደገው ሰው ነው ። ከሕመም ቀጥሎ ሞት ሊኖር ይችላል ብሎ ስለሚያስብ ያደገው ሰው ያውካል ። አስተሳሰባቸው ያላደገ ሰዎች በማወክ የታወቁ ናቸው ። ብዙ ቤቶች የቀረበውን ገበታ እንዳይበሉ በሁከት ተሞልተዋል ። የሚያውኩ ሰዎች መንፈሳዊ ረሀብ ያለባቸው ፣ በእግዚአብሔር በመተማመን ያልታነጹ ናቸው ። በስህተት ውስጥ የተዘፈቁና ራሳቸውን ማውጣት ያቃታቸው ሰዎችም ያውካሉ ። የተረሱ ሲመስላቸው አትኩሮት ለማግኘት ብለው ብዙ ሚስቶችና ብዙ እናቶች ፣ ብዙ ወንዶች ያውካሉ ። “የቤቱ ጌታ ወንዶች ቢሆኑም የሚወስኑት ግን ሴቶች ናቸው” ይባላል ። ደግሞም “ሴት ልጅ የምታለቅሰው ከጋብቻ በፊት ነው ፣ ወንድ ልጅ ግን የሚያለቅሰው ከጋብቻ በኋላ ነው” ይባላል ። ብዙ ትዳሮች በአንደኛው አዋኪነት ሰላምና ጣዕም አጥተዋል ።
የስኬትና የፍላጎት ማማው እስካሁን አልታወቀም ። ብልጭልጭ ነገር በመፈለግ የሚያውኩ ብዙዎች ናቸው ። ለዛሬ የሚያስብ ጋባዥ እንጂ ለነገ የሚያስብላቸውን የማይፈልጉ እየተበራከቱ ነው ። ወንዶች የሚበቃቸውን ባለማወቃቸው ፣ በስግብግብነት ሲሯሯጡ ልጆቻቸውን አጥተዋል ። መሮጥና መክነፍን አለዩምና ለፍተው እንዳለፋ ይሆናሉ ። ሕንፃውን ሠርተው ሲጨርሱ ልጆቻቸው ፈርሰው ያልቃሉ ። የወንዶች ማታ የኀዘንና የብስጭት የሚሆነው ልጆች ላይ ባለ መድከም ነው ። ከዚህ ስሜት ለመውጣት ይጠጣሉ ። “ኀዘናቸው እንዲሰጥም የሚጠጡ ሰዎች ኀዘን ጥሩ ዋናተኛ መሆኑን ንገራቸው” ይባላል ። ሚስቶች የሚያውኩ ሲሆኑም ባሎች መጠጥ ይጀምራሉ ። ምክንያቱም ሳይጠጡ ከገቡ ጭቅጨቅ ሲገጥማቸው ፣ ከጠጡ ግን በሰላም እንዲተኙ እንክብካቤ ይደረግላቸዋል ። ሌሎችን ማወክ ትልቅ ኃጢአት ነው ። ሥራ እንዳይሠሩ ፣ በቢሮና በሙያቸው የተሳሳተ ውሳኔ እንዲወስኑ እናደርጋቸዋለን ። ይልቁንም አስጨናቂ አደራ ያለባቸውን ሰዎች ማወክ አገርን መግደል ነው ።
እናቶች በማወክ ይደሰታሉ ። የተረሱ ሲመስላቸው ፣ ልጆቻቸው እንደ ጣሉአቸው ሲያስቡ ያውካሉ ። “ናፈቅኸኝ ልጄ ና” ሲሉ ልጁ ይዘገያል ። አሞኛል ብለው ሲተኙ ግን ቶሎ ይመጣል ። የብዙ እናቶች ሕመም ልጆቻቸውን መፈለግ ነው ። ናፍቆት ሐኪም የማያውቀው በሽታ ነው ። እናቶችን በሳምንት መጎብኘት ይገባል ። ቢያንስ በቀን አንድ ጊዜ መደወል ቀኑን ጥሩ ያደርግላቸዋል ። ለጥቂት ደቂቃ ብሶታቸውን ሲናገሩ ያለ ነቀፋ መስማት ይፈውሳቸዋል ።
በጓደኝነት መካከል በጣም የሚያውኩ ሰዎች አሉ ። እነዚህ ሰዎች ሥነ ልቡናቸው በብዙ መንገድ የተጎዳ ሊሆን ይችላል ። ያደገ ሰው ግን አያውክም ። ቅንዓት የማወክ ትልቅ መነሻ ነው ። ግምትም ያሰቃያል ። ማወክ በራስ የሚቀር ሳይሆን የሌሎችን ሰላም ሁን ብሎ ማመስ ነው ። ሰዎች ለሰላማቸው ብዙ ዋጋ ይከፍላሉና ስናውካቸው ለመለየት ያስባሉ ። ወታደር በዳር ድንበር የሚሞተው ለሰላም ነው ። የሰዎችን ሰላም ሰርቀን የእኛ ልናደርጋቸው በፍጹም አንችልም ። ሁከትን በወሬ ፣ በሐሜት የሚዘሩ ሰዎች አሉ ። ገና ሲደውሉ ጸሎት አድርጎ ማንሣት ይጠይቃል ። አንዳንድ ሰዎች የሚናገሩትን ለመርሳት አንድ ወር ይፈጃል ። ከአእምሮ የማይወጣ ክፉ ንግግር የሚናገሩ የሰይጣን መጠቀሚያ የሆኑ ምስኪን ሰዎች አሉ ። አንዳንድ ሰባክያን ሳይቀር የዚህ ተጠቂ ናቸው ።
ደስተኛነት የሚፈልግ ሰው ያደገ አስተሳብ መያዝ አለበት ። ደስታ ከመንፈሳዊ ጥጋብ የሚገኝ ነውና መጸለይ ፣ ቃሉን መስማት ይገባል ። ያለኝ ይበቃኛልን መልመድ ፣ ብልጭልጭን መናቅ ለደስታ ወሳኝ ነው ። የሰዎችን አትኩሮት መፈለግ ሊበቃን ይገባል ። ሰዎች እኛ ከማናውቀው ችግር ጋር እየታገሉ ነውና እኔን ብቻ እዩኝ ስሙኝ ማለት አይገባንም ። ይልቁንም የተሰጠንን ዘመን ለጸሎት ማዋል ይገባናል ። ያልታከመ ብዙ ስብራት ከልጅነት ጀምሮ ደስታችንን እየሰረቀ ነውና የሥነ ልቡና እርዳታ ማግኘት አስፈላጊ ነው ።
ያደገ ሰው ሌሎችን ማወክ ያቆማል ።
ይቀጥላል
ሚያዝያ 30 ቀን 2018 ዓ.ም.