አዋቂዎቹ ተደበቁ ፣ የጎንዮሽ ኑሮ ተጀመረ ፣ በጎች ተኩላ ሆኑ ፣ ፍርሃት በሁሉ ነገሠ ፣ ንብረት የሕይወት ዋስትና መሰለ ፣ ማጣት አጽናኝ አጣ ፣ እስከ መጨረሻው መናገር በዛ ። አስቦ የሚናገር ፣ ተናግሮም የሚያስብ ጠፋ ፤ ላለው የሚያረግድ ፣ የሌለውን የሚሰድብ ትውልድ መጣ ። ልብላችሁ የሚል ላብላችሁን የማያውቅ ፣ የወላጆቹን ሞት የሚመኝ ወገን ተትረፈረፈ ። ባለቤት ደባል ፣ ባዕዱም ባለቤት ሆነ ፤ የሚያስብ ሰው አለቀ ፣ የሚራራው ቶሎ ቶሎ ሄደ ። በግንዱ ላይ ያለው ለምለም ለዓይን ታጣ ፣ የወደቀው እንክልካይ ምድርን ሞላ ። የሚያዙት ሰው አለቀ ፣ የሚያዝን ልጅ አልገኝ አለ ። ያሳደጉት ጉበኛ ሆነ ፣ የወገኑን ቆዳ በቁሙ ገፈፈ ፣ አልኖር ብሎ ረገፈ ። ከዘመን መግባባት ፣ ያለውን ውሸት እውነት ብሎ መቀበል እኮ እንዴት ቻላችሁ ?!
እንዴት እኮ እንዴት ?!
ቆንጆዎች አስፈሪ ሆኑ ፣ በቅላታቸው ውስጥ ጽልመት ፣ በቁመናቸው ውስጥ ድንክነት ፣ በሳቃቸው ውስጥ አራጅነት ተገኘ ። በር የከፈቱለት በር ዘጋ ። ያሰለጠኑት ያስተማሩት ላይ ተቀኘ ። ያጎረሱት ነከሰ ፣ ክፉዉ እየተከበረ ደጉን ተቆረጠመ ። ብቻዬን ነኝ ብሎ ያሞቁት ብቻ የሚያስቀር ሆነ ። ገመድ ያስጣሉት ካልገደልሁ አለ ። እኮ እንዴት ሰምና ወርቅ ለቋንቋ እንጂ ለኑሮ አለው ወይ ? ዘመኑን ሳትመስሉ ዘመኑን የዋጃችሁ ካላችሁ እስኪ ተናገሩ ?
ካህን እውቀት አልባ ፣ መነኵሴ ጥግ የለሽ ሆነ ። የሞቱት አላርፍ አሉ ፣ ሬሳ የሚገርፍ ጀግና ትውልድ መጣ ። የእህሉ ክምር ፣ የእውቀቱ ጥግ ነቀዝ በላው ። ደጎች የማያቋርጥ ልቅሶ ገጠማቸው ። ሌባውም ሊሰርቅ ፣ ሠራተኛውም ሊሠራ ማልደው ይወጣሉ ። ከሙያ ይልቅ አፍ መኖሪያ ሆነ ። አጫዋች ተወደደ ፣ መካሪ ተጠላ ። ዋዘኛ ቤት ሠራ ፣ ጸሎተኛው ደጅ ወጣ ። ሞቻለሁ ብሎ የመነኮሰ ዘር አለኝ ፣ ጎሣዬ ይለምልም አለ ። ምስኪኖች ሞት ተፈረደባቸው ፣ በውስጥ በውጭ የሞት ፍርድ ይሰማል ። የሃይማኖት አስተማሪ የጠገበ አወዳሽ ፣ የተራበ ከሳሽ ሆነ ። እኮ እንዴት በሁሉም ነገር ለመምከን ፣ ለባዶነት ዋጋ ከፈልን ?
እንዴት እኮ እንዴት ?
ነገ ለመክሰስ ዛሬ በፍቅር የሚያወራ ፣ ለመራቅ የሚቀርብ ፣ ለመቆሸሽ የሚጸዳ ትውልድ መጣ ። ከብዙ ምኞት ጥቂት ተግባር እንደሚበልጥ ተረሳ ። ቁመና ያላቸው ወደቁ ፣ ዛላ ያላቸው ዛላ ብላሽ ሆኑ ። ቆንጆዎች እንደ እሳት ይለበልባሉ ። አካላቸውን ያዳበሩ አእምሮአቸው እንጭጭ ነው ። ሞኝ ለገንዘብ ብልጥ ሆነ ፣ የሌላውን ቀምቶ የእኔ ነው ማለት ተለመደ ፣ ለደከመው ድካሙን የሚከፍል ጠፋ ። ቸርነት ማስታወቂያ ሆነ ። ሳይቀርጽ የሚሰጥ ጠፋ ። የሰው ረሀብ መነገጃ ሆነ ። እናትም የውሸት ፍቅርን ከልጅዋ ተቀበለች ። አዋቂ ተደፈረ ፣ ሽበትን የሚያፍር ጠፋ ። ሃይማኖት ካላቸው የተወለዱ ከሀዲ ሆኑ ። እኮ እንዴት?! በጋራ ይኖሩታል እንጂ በጋራ እንዴት ይሞቱታል?
አጋላጩ መርማሪ ዘጋቢ ፣ አዋራጁ ሐቀኛ ፣ ወረኛው ምሥጢር መጋቢ ፣ ትዳሩን አደባባይ የሚያወጣው አስተማሪ ፣ አባትን የሚያዋርደው ጠበቃ ተባለ ። ያ የከበረ ሕዝብ እንዴት በቁመቱ ልክ ወደቀ ። የራሱን ሊቅ ስም የሚቀባ ፣ የነጭን መሃይም የሚያደንቅ ወገን እንዴት መጣ ። ሰንበት ሥራ ፣ አዘቦት እንቅልፍ እንዴት ታወጀበት ? ሲመሽ የሚወጣ ፣ ሲነጋ የሚተኛ ልጅ እንዴት ተፈጠረ ?
መልስ የለም መልሱ አንተ ነህ ። ይህች ጀምበር ያለ መልስ አትለቅብን ። አማኑኤል ሆይ እዘንልን! ክርስቶስ ሆይ በፍቅርህ አስበን !
ግንቦት 5 ቀን 2018 ዓ.ም.