የትምህርቱ ርዕስ | ከስንቱ

ቆሞ ከሚያስቀረው ፣ የጨው ሐውልት ከሚያደርገው ፣ ለሚያልፍ ተድላ የማያልፍ ስቃይ ከሚያበድረው ፣ ከማያልቀው መንገድ ፣ መሆኑ ከሚያስፈራው ፍጻሜ ፣ ኃይልን ከሚበላው ውስጥን ከሚያደቀው ፣ ጣትን ከሚቆርጠው ፣ መንገድን ከሚያሰናክለው ፣ ሲጠጉት ከሚርቀው ፣ ሲሹት ከሚተነው ፣ እስኪያደርጉት ከሚያጓጓው ፣ ሲሆን ከሚያሳምመው ፣ የሕሊና ድጋፍ የቃልህ ምስክርነት ከሌለው ፣ ከጻድቁ ከሚለየው ፣ ከእውነት ከሚያፋታው ከስንቱ አዳንከኝ ፣ ጌታዬ ተመስገን !

ከውስጤ ለመሸሽ ሰዎች ውስጥ እደበቃለሁ ፣ አማኙን ስፈራ ከሀዲን እማጸናለሁ ፣ የአገር ሰውን ስጠራጠር ባዕድን ልዛመድ እሻለሁ ። አንዱም አያድን ፣ አንዱም የልብ ዕረፍት አይሆንም ፤ ሞክሬ ተመልሻለሁ ። የሚበልጠውን ማወቅ ሲሳነኝ ፣ የሚሰጠኝን ትቼ የሚነሳኝን ስማጸን ፣ ከራሴ ለመሸሽ ራሴ ውስጥ ስደበቅ ፣ ጥፋትን በጥፋት ለመካስ ስነሣሣ ፣ ደምን በደም ለማጥራት ከንቱ ሙከራ ሳደርግ ከስንቱ አዳንከኝ ። ሸፍነህ እዚህ አደረስከኝ ። ጌታዬ ተመስገን ።

የአስተያየቱ ብዛት ሲያደክመኝ ፣ ቅንነት የሌለበት ትችን ሲያቆስለኝ ፣ አንተ በሰጠኸኝ ስነቀፍ ፣ ሁን ያልከኝን በመሆኔ በቁመናዬ ስወቀስ ፣ ጊዜ ይክሰኛል ብዬ ጊዜ ሲያልፍብኝ ፣ ዳኛ አገኛለሁ ብዬ የምድር ፈራጅን ስጠብቅ ፣ እየዘራሁ መኸር ሳጣ ፣ እየነገድሁ ትርፍ ሲርቀኝ ፣ እያፈቀርኩ ፍቅር ሲሸሸኝ ከስንቱ አዳንከኝ ። ልቤ እንዳይከዳኝ ብዙ ዘመን ጠበቅኸኝ ። ተመስገን ጌታዬ !

ሳስብህ ዋልሁ ሲሉኝ ደስ ይለኛል ። ባንተ ግን ከዘላለም በፊት ስታሰብ ኖሬአለሁ ። ሌላ ዓለም ላይ የምንተዋወቅና ተጣልተን የመጣን እስኪመስል በዚህ ዓለም ፣ በአጭሩ ዕድሜ ጠባችን መራራ ሆኗል ። አንተ ለተቀበልከኝ ከሳሽ ይደክማል ። ልቤ ይሰፋል ስል በጣም ሲጠብብኝ ፣ ስጦታን በክፍያ ካላገኘሁ ብዬ ጸጋን ሳቃልል ፣ ነቀፋን የመኖርና የመሞት ወሳኝ ኩነት ሳደርግ አንተ አዘንክልኝ ። ከስንቱ አዳንከኝ ፣ ከትምህርት ነፋስ ጠበቅኸኝ ፣ ከአሳቾች ጥርስ ታደግኸኝ ። ተመስገን ጌታዬ!

ዓለም የጠበበ መስሎ ከሚሰማው ቀን ፣ ሰማይ ያጠረ ሁኖ ከሚታየው ዘመን ፣ ሁሉ ተፈታኝ ሁኖ መልስ ከሚርቅበት ወራት ፣ ክፍፍል በዝቶ ሰው ራሱን ከሚያሰቃይበት ምድር ፣ የሚጠላውን እወድሃለሁ እያለ የሚወደውን ፍቅሩን ከማይገልጥበት አገር ፣ ራሱ ጠፍቶበት ሰውን ከሚፈልግ ማንነት ፣ የራሱ አሮበት የሰው ከሚያማስልበት ሹመት ፣ የጸጋ ኑሮ አብቅቶ የብድር ኑሮ ከፈላበት ሰፈር ፣ ስለ መኖሪያው ሲጨነቅ ስለ መኖሩ ከማያመሰግን ትውልድ… ከስንቱ አዳንከኝ ፣ ከራሴ ታደግኸኝ ። ተመስገን ጌታዬ!

የሞት ልጅ ለመሆን ከአውሬ ጋር ስቃለድ ፣ ከእባብ ጉድጓድ ላይ ስጫወት ፣ በፈንጂ ወረዳ ቤት ስሠራ ፣ ለጽድቅ ብልጥ ሁኜ ለኃጢአት ስሆን ተላላ ፣ ሳትመረር ከስንቱ አዳንከኝ ፣ በእጄ የነበረውን የሞት ሠረገላ ሰበርክልኝ ፤ መኖሬ ባንተ ነው ፣ አለሁ ማለቴ ባለኸው ባንተ በአማኑኤል ነው ፣ ወጥቼ የምገባው ዋስትና ስላለ ሳይሆን በዙፋንህ ስላለህ ነው ! ተመስገን ጌታዬ!

ግንቦት 15 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ