መግቢያ » ልዩ ልዩ ሁለት » ማን አለ እንደ ጌታ

የትምህርቱ ርዕስ | ማን አለ እንደ ጌታ

ደብቆ የሚያጎርስ ፣ ብቸኛውን የሚሰበስብ ፣ በሌሊት የሚደርስ ፣ በቀትር የሚመጣ ከልሎ የሚያሳልፍ ፣ በደካማው የማያፍር ፣ ስሙን የሚሰጥ ፣ ተጠሩብኝ የሚል ፣ ባለጠጋ ሳለ ከድሀ ቤት የሚያድር ፣ ንጹሐን መላእክት ሳሉት ኃጢአተኛውን የሚወድ ፣ በጠላት ወረዳ ነፍስን የሚያተርፍ ፣ የክፉዎችን ዓይን አውሮ ቤትን የሚጠብቅ ፣ አቤት ብሎ የሚሰማ ፣ ለመርዳት የሚመለከት ፣ ጠባብ ቀንን የሚያሰፋ ማን አለ እንደ ጌታ !? አንተ የዓለም ፀሐይ ፣ አንተ የዓለም ጤና ፣ አንተ የተባበረ ምስጋና የማይገልጥህ አዶናይ ሆይ ተመስገን ።

ማን አለ እንደ ጌታ

ከእኛ በላይ ለእኛ የሚያስብ ፣ የረሳነውን ጸሎት የሚመልስ ፣ አትረባም ለተባለው ረብ የሚሆን ፣ የተጣለውን የሚያነሣ ፣ መንገድ ለጠፋው የሕይወት መንገድ የሚሆን ፣ ሳቅ ለራቀው ሳቅን የሚሰጥ ፣ ሁሉ ላደመበት አገር የሚሆን ፣ የተዘጋውን ደጃፍ የሚከፍት ፣ በማንነቱ ብቻ ደስ የሚያሰኝ ፣ ለድሀ የሚፈርድ ፣ ረሀብተኛን በበረከት የሚያጠግብ ፣ ትምክሕተኞችን የሚያዋርድ ፣ ለማስተማር እንጂ ለመበቀል የማይቀጣ ፣ ፊቱን የማያዞር ፣ ገጹን የማያጠቁር ማን አለ እንደ ጌታ !? በጸጋ የበረታ ፣ ለማዳን የሚመጣ ፣ ሲመሽ የሚያነጋግር ማን አለ እንደ ጌታ !? አንተ የማትጨልም ብርሃን ፣ አንተ የቀትር ጥላ ፣ አንተ የምሽት ወዳጅ ፣ አንተ ከእስረኛው ጋር የምትታሰር ፣ አንተ የስደተኛው ተስፋ ኢየሱስ ሆይ ተመስገን ።

ማን አለ እንደ ጌታ

ድንጋይ ለሚወረውሩ ዳቦ የሚሰጥ ፣ ለሚጠሉት የፍቅር ፀሐይ የሚያወጣ ፣ ለንፉጎች የበረከት ዝናብ የሚያወርድ ፣ ለውለታ ቢሶች የእንደገና ዕድል የሚሰጥ ፣ ጣራ ሳያነሣ ቤትን ፣ ልብስ ሳይገልጥ አካልን የሚያይ ፣ አብሮ የሚታመም ፣ አብሮ የሚያስታምም ፣ ወዳጅ በመንገድ ሲቀር እስከ መጨረሻው የሚዘልቅ ፣ አብሮቱ ክዳት ፣ ፍቅሩ ወረት የሌለበት ፣ ያነጋውን የሚያስመሽበት ተገዳዳሪ የሌለው ፣ በመስጠቱ የማይጸጸት ፣ በጠላት መንደር የደኅንነት ዋስትና የሚሰጥ ፣ በክፉ ቀን የሚሸሽግ ፣ በተኩስ ወረዳ የሚሸፍን ፣ ለማያስተውሉ ዓይናቸው ፣ ለሞኞች ጥበባቸው ማን አለ እንደ ጌታ !? አንተ ጥሩ ወርቅ ፣ አንተ ክቡር አልማዝ ፣ አንተ አቻምየለህ ፣ አንተ ወደር የለህ ፣ አንተ ስመ መልካሙ ፣ አንተ ወደህ የማትጠላ ፣ አንተ የጓዳው ዳባሽ ፣ አንተ የጦሩ ጀግና ሕያው መንፈስ ቅዱስ ተመስገን ።

ማን አለ እንደ ጌታ

ሳይቆጥር የሚሰጥ ፣ ሰለቸኝ ብሎ በሩን የማይዘጋ ፣ ለማኝ አፍቃሪ ፣ ጸሎትን የማያፈስ ፣ የመሻገሪያው መርከብ ፣ የአማኞች ዓለም ማያ ፣ የሕፃናት ጥበብ ፣ የመንገደኞች ካርታ ፣ የፈላስፎች እውቀት ፣ የተመራማሪዎች ትዕግሥት ፣ የመናኞች እንጀራ ፣ የመነኮሳት ኑሮ ፣ የሰባኪዎች ውብ ቃል ፣ በበረሃ የተገኘ ምንጭ ፣ በረሀብ ዘመን የወረደ መና ፣ የኢሳይያስ መነጽር ፣ የዮናስ መርከብ ፣ የድንግል ልጅ ፣ የመሐን አነጋጋሪ ፣ የባልቴት ራስ ፣ የመበለት አጥር ፣ ቤተ ሠሪ ፣ አገር ጠባቂ ፣ የዳኛው ዳኛ ፣ የወታደሩ ጋሻ ፣ ጠጠር ላበደሩት ወርቅ ከፋይ ፣ አፈር ለሰጡት እህል ሰፋሪ ፣ በዱር የኖረውን መርቶ ከለማ ከተማ የሚያደርስ ፣ እንግዳ ተቀባይ ፣ አገር አላማጅ ። እኮ ማን አለ እንደ ጌታ !? አንተ ቡሩህ ፀሐይ ደመና የማይጋርድህ ፣ አንተ ነቅዕ ንጹሕ/የማትነጥፍ ምንጭ ፣ አንተ የድንግል ብሥራት ፣ አንተ የማርያም ልጅ ፣ አንተ የእመ ብርሃን ታዛዥ ፣ አንተ የቤተ ልሔሙ ሕፃን ፣ አንተ የገሊላው ውብ ወጣት ፣ አንተ የቀራንዮ በግ ፣ አንተ የትንሣኤው አንበሳ ፣ አንተ የፈተናው ውጤት ፣ አንተ የመከራው አክሊል ፣ አንተ የመጨረሻው ቤት ፣ አንተ የማትፈርሰው ከተማ ፣ አንተ ጸንተህ የምታጸናው ፣ አንተ በነፋስ ውስጥ የምታበራ መቅረዝ ፣ አንተ ልበ ሩኅሩኅ ፣ አንተ ለእናት የእናት አንጀትን የሰጠህ እናታችን ቅዱስ ጌታ ተመስገን ።

ማን አለ እንደ ጌታ !? የደረሰላችሁ አመስግኑ ፣ በረሀብ ዘመን እንጀራ የቆረሰላችሁ ተናገሩ ፣ በተከበበ ከተማ አስደናቂ ምሕረቱን ያሳያችሁ ዝም አትበሉ ። ጉልበት የማያልፈውን ቀን ያለፋችሁ እስኪ ዘምሩ ። እንዲህ በሉ፡- ማን አለ እንደ ጌታ !?

ግንቦት 18 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ