መግቢያ » ልዩ ልዩ ሁለት » ባንተ እኮ ነው መንፈስ ቅዱስ !!

የትምህርቱ ርዕስ | ባንተ እኮ ነው መንፈስ ቅዱስ !!

ድሀው በሰማይ ስጦታ የበለጸገው ፣ አላዋቂው ተጠያቂ የሆነው ፣ የስንቱ ዕራቁት የተሸፈነው ፣ በዕንባ የዳመነው ዓይን የጠራው ፣ ልብ የሰማይን ጓዳ ያየው ፣ ነፍስ ሁሉ ወደቡን አግኝቶ ጭነቱን ያራገፈው ፣ ደካማው ድካሙን እንደ ልብስ አውልቆ የጣለው ፣ ማዳን በሚችለው ኃይልህ ተባራሪው ያመለጠው ባንተ እኮ ነው መንፈስ ቅዱስ ! ፍጡነ ረድኤት መንፈስ ቅዱስ ፣ ከዋዕዩ/ከሐሩሩ የምትጋርድ ብሩህ ደመና ጰራቅሊጦስ ፣ የዳስ ኑሮ ሲፈርስ የዘላለም መቅደስ ሆይ ተመስገን !

ባንተ እኮ ነው መንፈስ ቅዱስ !

የእውነት መንፈስ ነህና ከሚመስል ነገር የወጣሁት ፣ ለጥልቁ መንፈሴ በጥልቀት የተናገርህ ፣ ከዓለም ቍጣ በሰላምህ ያረፍኩት ፣ የጽድቅ ከተማዬን ያገኘሁት ፣ ያለፈውን ዘመኔን የረሳሁት ፣ ለነገ አዲስ ተስፋ የሰነቅሁት ፣ መሥራት በማልችልበት ዘመን ተሠርቶ ያገኘሁት ፣ ባንተ እኮ ነው መንፈስ ቅዱስ ። አንተ የድል ጮራ ፣ አንተ የፍቅር ዓለም ፣ አንተ ከፀሐይ የምታበራ ፣ አንተ በጻድቃን ሰውነት የምትላወስ ፣ አንተ ስጦታህ የማይነጥፍ ፣ አንተ ሁለተኛ ዕድል የምትሰጥ ፣ አንተ ፀዓዳ ርግብ ፣ አንተ ፈውስን በክንፎችህ ያዘልህ ። ኦ መንፈስ ቅዱስ ሆይ ተመስገን ። በማን ላይ ቆመሽ ማንን ታሚያለሽ ነው ፣ በማን መሠረትነት ላይ ቆሜ ዝም እላለሁ ፣ ምሰሶነትህን ተደግፌ እንዴት እዘናጋለሁ ፣ ያለ ወገን የምታኮራው ሆይ ተመስገን ! አንተን የማይወድ ዕድሉ ባዶ ነው !

ባንተ እኮ ነው መንፈስ ቅዱስ !

ከመንታ ማንነት ፣ ከተቀላቀለ መንገድ ፣ ጸሎትን ከሚያስር በቀለኝነት ፣ አክብሩኝ ከሚል ቅሌት ፣ ዓላማ ይዞ ቅርብ ከማደር ፣ ወተቱን አጥቁሮ ከማየት ፣ እስኪወዱኝ ከመጠበቅ ፣ ልሞክረው ብሎ ወደ ቤትህ ከመምጣት ፣ እውቀት ከሌለው አምልኮት የዳንሁት ባንተ እኮ ነው መንፈስ ቅዱስ ። ነፍሴን እንደ ገና ያገኘኋት ፣ ከልቤ ጋር በድፍረት ያወጋሁት ፣ በማግኘት ያልጠፋሁት ፣ በማጣት ያልካድሁት ፣ የሰው ዋስትናን የናቅሁት ፣ ካላየሁ አላምንም ማለትን የጣልሁት ፣ ነገር ሁሉ ለበጎ ነው ብሎ ማረፍን የለመድኩት ባንተ እኮ ነው መንፈስ ቅዱስ ። አንተ የምትነበብ መጽሐፍ ፣ አንተ የምትጠጣ የበረሃ ምንጭ ፣ አንተ የምትወዳጅ የልብ ወደብ ፣ አንተ የምትሰጥ እጀ ርጥብ ፣ አንተ የተገኘህ የወርቅ እንክብል ፣ አንተ አንተን እስክናውቅህ የተጋህ መምህር ፣ አንተው ጥበብ አንተው ጥበበኛ ፣ አንተ ራስህን ካልገለጥህ ማንም የማያውቅህ አጽናኝ ሆይ ተመስገን ።

ባንተ እኮ ነው መንፈስ ቅዱስ !

ያለ አጥር የምጋረደው ፣ ያለ ዘብ የምጠበቀው ፣ ያለ ካባ የምከብረው ፣ ያለ በጀት የምኖረው ፣ ያለ ጥላ በረዶውን የማልፈው ፣ ያለ ጓደኛ የምጽናናው ፣ ያለ አቅም የምጨርሰው ፣ ያለ ችሎት ፍርድ የማገኘው ፣ ያለ መተማመኛ ወጥቼ የምገባው ባንተ እኮ ነው መንፈስ ቅዱስ ። አንተን ያገኘ ሁሉን አገኘ ፣ አንተን ያመነ መላው ዳነ ፣ አንተን የተወዳጅ ቍስሉ ሻረ ፣ አንተን የሳመ ጠባሳው ጠፋ ፣ አንተን የተተገነ ነፋሱን አለፈ ፣ አንተን ያፈቀረ ጥሙን ረካ ፣ አንተን የተማጸነ በኃይል በረታ ፣ አንተን የጠራ ከእርጅናው ታደሰ ፣ አንተን ያስቀደመ ምርኮ አፈሰ ። መንፈስ ቅዱስ ሆይ በተባበረ ልሳን ፣ ሰማይና ምድር በሚሰሙት ቋንቋ ምስጋና ላንተ ያስተጋባ ። በሚሰጥበት ዘመን የሚከጅል ባንተ ስስቱ ይሰበር ፣ በሚያገለግልበት ዘመን አባብሉኝ የሚል ለጋነቱ ይብሰል ።

ባንተ እኮ ነው መንፈስ ቅዱስ !

የእስትንፋሳችን እስትንፋስ ፣ የሕይወታችን ሕይወት ፣ የመንገዳችን ብርሃን ፣ የብርታታችን ምንጭ አንተ ነህ ። ያለ ደጋፊ የምታቆም ፣ ያለ ወገን የምትረዳ ፣ ያለ አቅም አገልጋይ የምታደርግ አንተ ነህ ። ቡሩክ ፀሐይ ሆይ ለጨለመበት ዓለም እባክህ አብራ ። አውቃለሁ ሲል የደነቆረው ዘመን ባንተ ይዳን ። ሰው ሰውን የሚበላበት ጭካኔ ባንተ ማስተዋል ይለወጥ ። መንፈስ ቅዱስ ሆይ ባንተ ነው ። ሸሽገህ የምታጎርስ ፣ ደብቀህ የምትሰጥ አንተ ነህ ። ለሚደናገሩት መልስ ፣ ለጠፉት መንገድ ፣ በጥም ለተቃጠሉት እፎይታ አንተ ነህ ። መንፈስ ቅዱስ ሆይ አንተን በማወቅ ምድር ትሞላ ። አሜን !

ግንቦት 22 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ