መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » የኃጢአት ስሞች » የኃጢአት ስሞች -5

የትምህርቱ ርዕስ | የኃጢአት ስሞች -5

አለመጸጸትም ሲጸጸቱ መኖርም ሁለቱም ትክክል አይደሉም ። አለመጸጸት የሕሊና ፣ የእምነትና የሞራል መሞትን የሚያሳይ ነው ። የሕመም ስሜት ያለው ሁሉ በሕይወት አለ ማለት ነው ። የሥጋ ደዌ ሕሙማን ትልቁ ችግራቸው ሕመም የማይሰማቸው መሆኑ ነው ። ሕመም እንዲሰማቸው የሚያደርጉት ነርቮች በበሽታው ስለ ተጎዱ ቢላ ሲቆርጣቸው የሚያውቁት በማየት እንጂ በስሜት አይደለም ። እነዚህም ወገኖቻችን ሕመም ካላቸው ታማሚዎች በላይ የተጎዱ ናቸው ። ታዲያ የሚደረግላቸው ሕክምና ወደ ሕመም ስሜት እንዲመጡ የሚያደርግ ነው ። ሕመም አልባነት ትልቅ አደጋ ይዞ ይመጣል ። የማይጸጸቱ ሰዎች ወደ ጸጸት ስሜት የሚመጡት በክርስቶስ ያለውን ሕይወት ሲያገኙ ብቻ ነው ። ክርስትና ሕይወት ነው ስንል አንበድልም በዚህ ሥጋ ፍጹም እንሆናለን ማለት ሳይሆን ስንበድል ይሰማናል ማለት ነው ። የጸጸት ስሜትና ርኅራኄ ሰማያዊ ሕይወትን የመካፈል ውጤት ናቸው ። ሰዎች ታላቁን ፍቅር አጣጥመው ሳይቀየሙ ሁሉንም ሰው በይቅርታ ሊያልፉ ይችላሉ ። ይህ ከሰማዕትነት የሚቆጠር ነው ። ጨርሰው በመደንዘዝ ምንም ቢያደርጓቸው ምንም የማይሰማቸው ሰዎች አሉ ። ያለ እውቀትና ያለ እምነት የሆነ ደግነት ዋጋ የለውም ። ብዙ ጅሎች በደልን አያስታውሱም ። እነዚህ ሰዎች ስሜታቸው ጉዳት ደርሶበታል ማለት ነው ። ይቅር ባይ ተብሎ የሚጠራ ግን ይቅር ለእግዚአብሔር ብሎ መተው የሚችል ነው ። አለመጸጸት ከባድ እንደሆነ ሁሉ ሲጸጸቱ መኖርም ኢክርስቲያናዊነት ነው ። ሁሉም ነገር የራሱ የሆነ መፍትሔ አለው ። የኃጢአት መፍትሔውም ንስሐ ነው ።

ሰዎች አርአያ የሚያደርጉት ሰው ሲያጡ መጸጸት ያቆማሉ ። ሁሉም አንድ ዓይነት ከሆነ ራስን ማየት አይቻልም ። ከመሰሎቹ ጋር የሚኖር እውቀትም ዕድገትም አያገኝም ። ከሚበልጡት ጋር የሚኖር ግን ራሱን ማየት ስለሚችል ይለወጣል ። አንድ ዓይነት የኑሮ ዘዴ ፣ አንድ ዓይነት አለባበስና አስተሳሰብ የሚፈልገው ይህ ዘመን አንድ ዓይነት በደለኛነትንም እያጸደቀ ነው ። ሁሉም አንድ ዓይነት ከሆነ የንስሐ መንፈስ እየራቀ ይመጣል ። የጎረቤታችንን በደል ማየት ለንስሐ አያበቃንም ። ለንስሐ የሚያበቃን በክርስቶስ ቅዱስነት ፊት ፣ በመስቀሉ አንጻር መቆም ነው ። ቆሻሻ መስተዋት መልክን አያሳይም ፣ ንጹሕ መስተዋት ግን መልክን ያሳያል ። የተቀደሱ ሰዎች ሲኖሩ ብዙዎች ራሳቸውን ያያሉ ፣ ይጸጸታሉ ፣ ንስሐ ይገባሉ ። ሰጪ ሰዎች ለድሆች ያለንን ጭካኔ እንድናይ ያደርጉናል ። በጋብቻ የተወሰኑ ሰዎች ዘላንነትን ይወቅሳሉ ። እነዚህ ሰዎች መኖራቸው በራሱ ተጽእኖ ይፈጥራል ። ነቢዩ ኤልያስ በነበረበት ስፍራ ምንም ቢጠሩት የሰይጣን መንፈስ መምጣት አልቻለም ። የሚጸልዩ ሰዎች ባሉበት ሰይጣናዊ ተጽእኖ አይኖርም ።

ሰዎች አርአያ የሚያደርጉት ነገር ሲያጡ ጸጸት ያቆማሉ ብለናል ። አንድን ማኅበረሰብ በመጥላትም ይመረዛሉ ። አንድን ግለሰብ ሲጠሉ ሊሰማቸው የሚችል ሲሆን አንድን ማኅበረሰብ ሲጠሉ ግን ፍትሐዊነት ይሰማቸዋል ። ትክክለኛ ፍርሃት የጤንነት ምልክት ነው ። ይህን ፍርሃት የሚያስተምሩን ወላጆች ናቸው ። ሕፃኑ ሲያጠፋ ይቀጡታል ፣ ያንን ስህተት እንደገና ለመሥራት እየፈራ ይመጣል ። ያደጉት ጎልማሶች ግን በስህተታቸው ራሳቸውን ይቀጣሉ ። ራስን መቅጣት ተወዳጅ አይደለም ። ሰው ለራሱ ኃጢአት ትክክለኛውን ዋጋ መክፈል አይችልም ። የክርስቶስንም ቤዛነት የምናቃልለው ለራሳችን ስህተት ዋጋ ለመክፈል ሕሊናን ለማሰቃየት ስንፈልግ ነው ። ሌላውን ማኅበረሰብ በጠላትነት የሚፈርጅ ሰው አይጸጸትም ። የዘረኝነት አስተሳሰብ ካለን ፣ ለሌላው ማኅበረሰብ ጥላቻን ካዳበርን መግደልና ማሳደዳችንን እንደ ጽድቅ እንቆጥረዋለን ። የጸጸት ስሜት አለመኖሩ ከሰውነት ሲያወጣን ፣ ለንስሐ ሳንበቃ እንድናልፍ ያደርገናል ።

የኃጢአት አንዱ ትርጉም ስንፍና ነው ። ስንፍና በአልጋ ላይ መኖር ነው ። ዘማውያንም ሰነፍ ይባላሉ ፣ ኑሮአቸው አልጋ ላይ ነውና ። ሕይወት ብዙ አደራና ታላላቅ ጥሪዎች አሉአት ፣ ዘማዊ ግን ከስንፍናው ውጭ ምንም ነገር የማሰብ አቅም የለውም ። ስንፍናውም ወደ በሽታ ስለሚወስደው ያንን አልጋ በውድቀትም በቅጣትም አይለየውም ። ለሥራ መለገም ኃጢአት መሆኑን ብዙዎች አላወቁም ። በየሰበቡ ከሥራ መቅረት እግዚአብሔርን ያሳዝናል ። አንዳንዶች ዘመዶቻቸውን ሳይቀር በውሸት እየገደሉ ከሥራ ይቀራሉ ። እግዚአብሔር ከሰጠን የሕሊና መድኃኒት አንዱ ሥራ ነው ። ከክፉ አሳብ የምንድነው ፣ ጥሩ እንቅልፍ የምናገኘው ፣ የጣፈጠ እንጀራ የምንበላው በሥራ ነው ። ሥራ ከሰዎች ጋር የሚያገናኝ በመሆኑም ብቸኝነትን ያርቃል ። የኃጢአት አንዱ ስም ስንፍና የሚል ነው ። ሰነፍ እጅ እግር እያለው አይጠቀምበትም ። ለመስጠት እጅ ፣ ወንጌልን ዞሮ ለመስበክ እግር ኖሮት የማይጠቀምበት ሰነፍ ነው ። ሰነፍ ተፈጥሮውን ፣ ጸጋውንና ዕድሜውን ያባክናል ። የሰነፎች አገር ምኞት እንጂ ዕድገት የላትም ። ስንፍና በሁሉ አገር አለ ፣ በእኛ ግን ይጸናል ።

ይቀጥላል

ሰኔ 17 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ