መግቢያ » ልዩ ልዩ ሁለት » ቅድስት ሥላሴ

የትምህርቱ ርዕስ | ቅድስት ሥላሴ

ሥላሴ ማለት ሦስትነት ማለት ነው ። አንድ አምላክ በሦስት አካላት ፣ ሦስት አካላት በአንድ ባሕርይ የተገለጡበት ትምህርት ምሥጢረ ሥላሴ ይባላል ። ሥላሴ የሚለው ሦስት ማለት ሳይሆን ሦስትነት ማለት ነው ። ሥላሴ የብዙ መጠሪያ በመሆኑ ሥላሴዎች ብዙ መናገር ተገቢ አይደለም ። የሥላሴ ትምህርት በብሉይ በሐዲስ የታወቀ ነው ። ፍጹም ትምህርት ነውና ፍጹሙ መምህር ክርስቶስ እስኪመጣ በደንብ አልተረዳነውም ነበር ። በክርስቶስ ሰው መሆን የሥላሴ ትምህርት በጉልህ ታወቀ ። በላቲን ትሪኒቲ (Trinity) የሚለው ሥላሴን ለመግለጥ የዋለ ሲሆን ሦስትነት በአንድነት ማለት ነው ። ይህን ቃል በግሪኩ የተጠቀመው ቴዎፍሎስ ዘአንጾኪያ (180 ዓ.ም.) ሲሆን በላቲን ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀመው ተርቱሊያን የተባለው ሊቅ ከ155-220 ዓ.ም የነበረው የሰሜን አፍሪካው የካርቴጅ የዛሬዋ ቱኒዚያ ተወላጅ ነው ። ሥላሴ የሚለው ቃል ቀጥታ በመጽሐፍ ቅዱስ ባይገኝም ትምህርቱ ግን በሰፊው ሰፍሯል ። እውነቱ ካለ ስያሜው የሚያጣላ አይደለም ።

እግዚአብሔር በሦስት አካላት በአንድ አምላክነት የተገለጠ ነው ። ይህንን የሚያብራራው ትምህርት ትምህርተ ሥላሴ ወይም ምሥጢረ ሥላሴ ይባላል ። እግዚአብሔር ሦስትነት አለው ስንል በምድር ላይ እንደምናውቀው ሦስት ፣ አንድ ነው ስንልም እንደ ቍጥር ሕግ ነጠላ አንድ ማለታችን አይደለም ። ሥላሴን ሊያብራራ የሚችል ምድራዊ ምሳሌና ቀመር የለም ። ምሥጢር መባሉ ከእውቀት ያለፈ ነውና በእምነት የምንቀበለው ፣ የተፈቀደልንን ያህል አውቀን ከዚያ ያለፈውን “አንተ ራስህን ታውቃለህ” በማለት ዕፁብ ዕፁብ የምንልበት ነው ።

ሦስት ነው ስንል የአካል ሦስትነት እንጂ የመለኮት ሦስትነትን እየተናገርን አይደለም ። አንድ ነው ስንልም የመለኮትን አንድነት እንጂ የአካልን አንድነት እየተናገርን አይደለም ። ሦስት ነው ስንል ሦስት አማልክት እያልን አይደለም ። አሕዛብ ብዙ ጣኦታትን አማልክት ብለው ይከተላሉ ። እኛ ግን አንድ አምላክ ብለን እናምናለን ። አንድ ነው ስንልም እንደ ሰባልዮሳውያን ፣ እንደ ሙስሊም ፣ እንደ አይሁድ ስለ አንድ ገጽ ወይም ስለ አንድ አካል እየተናገርን አይደለም ። በሦስት አካላት በአንድ አምላክነት የሚኖር እግዚአብሔር ብለን ማመናችን ነው ።

ሥላሴ በጎልማሳ አምሳል ቢገለጡ መልካቸው ያ ነው ማለት አይደለም ። ኃይልን የሚገልጥ አርአያ ነው ። ሥላሴ በሽማግሌ አንጻር ቢገለጡም ጥበብን ለማሳየት ነው ። ለነቢዩ ዳንኤልም በዘመናት የሸመገለ ሁኖ ተገልጧልና ሥላሴን በሽማግሌ መመሰል የተለመደ ነው (ዳን. 7፡13)። እንደ እግዚአብሔር የሸመገለ የለም ፣ ግን ኃያል ነው ፣ ረዳት አይሻም ፣ መንግሥቱም አልጋ ወራሽ ፣ ተተኪ ዳኛ የለውም ። እግዚአብሔር በዘላለማዊ አዲስነት ነዋሪ ነው ። የክርስትናን እምነት ልዩ የሚያደርገው ምሥጢረ ሥላሴ ነው ። በሥላሴ የሚያምኑ ከሥላሴ በላይ የአንድነት መሠረት የለምና ሊቀራረቡ ይገባል ።

የብሉይ ኪዳን ንባባት ስለ ሥላሴ ይነግሩናል ። ቤተ ክርስቲያንም በዓለ ሥላሴን ስታከብር በጥር 7 የሰናዖር ግንብ መፍረሱን ከዘፍ.11 ላይ በመውሰድ ታስባለች ። የዓለም ቋንቋ የተፈጠረበት ፣ ሰዎች ባለመግባባት የተደበላለቁበት ስፍራ ነው ። የሰናዖር ግንብ ታላቅ ሥልጣኔ ነው ። እግዚአብሔር የሌለበት ሥልጣኔ ፈራሽ መሆኑን ፣ በትልቁ ኅብረትን የሚያፈርስ መሆኑን ያሳያል ። የዛሬም ሥልጣኔ ግንቡ እንደ ሰናዖር ግንብ ቆሟል ፣ አንድነት ግን ጠፍቷል ። ቋንቋ የመግባቢያ መሣሪያ መሆኑ ቀርቶ የመለያየት ርእስ ሁኗል ። ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔር የሌለበት ከፍታ በመለያየት እንደሚጠናቀቅ ለመግለጥ ፣ እግዚአብሔር ከሥልጣኔ በላይ መሆኑን ለማስታወስ ፣ የቋንቋ ጦርነትን ለመገሠጽ ይህን በዓል ታስባለች ። በሐምሌ 7 በዓለ ሥላሴን የምታከብረው በዘፍ. 18 ላይ ተመሥርታ ነው ። ሥላሴ በአብርሃም ቤት በሦስት አረጋውያን ምሳሌ መገለጣቸውን በማሰብ እግዚአብሔር ወደ ኑሮአችን እንዲገባ የምታስተምርበት ነው ። “በቀትርም ጊዜ እርሱ በድንኳኑ ደጃፍ ተቀምጦ ሳለ እግዚአብሔር በመምሬ የአድባር ዛፍ ተገለጠለት ። ዓይኑንም አነሣና እነሆ ፥ ሦስት ሰዎች በፊቱ ቆመው አየ ባያቸውም ጊዜ ሊቀበላቸው ከድንኳኑ ደጃፍ ተነሥቶ ሮጠ ፥ ወደ ምድርም ሰገደ” ይላል (ዘፍ. 18፡1-2)። እግዚአብሔር ተገለጠለት ይልና ሦስት ሰዎች ደግሞ ይታዩታል ። አብርሃምም አንድነትና ሦስትነት ተገልጦለታልና አንድ ጊዜ “አትለፈኝ” ብሎ በነጠላ ሲናገር ሌላ ጊዜ “እግራችሁን ታጠቡ” በማለት በብዙ ቍጥር ይናገራል ። ለሣራም ትእዛዝ ሲሰጥ ሦስት መስፈሪያ የጠራ ዱቄት ሰፍረሽ በአንድ ለውሺው በማለት የተገለጠለትን ሦስትነትና አንድነት ለማብራራት ሞክሯል ። ሥላሴ በአብርሃም ቤት እንደ ተገለጠ ቅዱስ አውግስጢኖስ ቅዱስ አምብሮስ ተናግረዋል ። እግዚአብሔር አሁን በአብርሃም ድንኳን የተገለጠው በኋለኛው ዘመን ከአብርሃም ዘር እንደሚወለድ ተስፋ ለመስጠት ነው ። እውነተኛዋም የአብርሃም ድንኳን ድንግል ማርያም ሁና ከእርስዋ ጌታ ተወለደ ። ይስሐቅ የክርስቶስ ምሳሌ ሆነ ። ይልቁንም የክርስቶስን ሕማምና መከራ የሚያሳይ መገለጫ ሆነ ።

የሥላሴ ትምህርት ድንቅ ነው ። በዚህ ቀንም የሃይማኖታችን መሠረት የሆነው ምሥጢረ ሥላሴ ይነገራል ። የምሥጢራት ሁሉ መሠረትም ምሥጢረ ሥላሴ ነው ። በቅድምና የነበረው ወልድ ሰው ሆኗል ። የሥጋዌ መሠረትም ምሥጢረ ሥላሴ ነው ። ክርስቶስ ሰው ባይሆን ሌሎች ምሥጢራት አይታወቁም ነበርና ሥላሴ የምሥጢራት መሠረት ነው ። የተወለድነውም ከሥላሴ ነው ። የጸጋ ልጆች የተባልነው ፣ ለወራሽነትም የተመደብነው በጥምቀት ባገኘነው ጸጋ ነው ።

እግዚአብሔር በስም ፣ በአካል፣ በግብር ሦስት ሲሆን በመለኮት ግን አንድ ነው ። ስሙ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ይባላል ። አካሉ ለአብ የራሱ ሙሉ መልክ ፣ ገጽና አካል አለው ። ለወልድም የራሱ መልክ ፣ ገጽና አካል አለው ። ለመንፈስ ቅዱስም የራሱ መልክ ፣ ገጽና አካል አለው ። የግብር ሦስትነትም አብ ወላዲ ፣ ወልድ ተወላዲ መንፈስ ቅዱስ ሠራጺ ብለን የምናምነው ነው ። አንድነታቸው በመለኮት ፣ በሥልጣን ፣ በመፍጠር ፣ በማዳን … ነው ። አካሉም ረቂቅ ነው ፣ የማይወሰን ነው ። ሦስቱ አካላተ ሥላሴ ምሉአን ቢሆኑም መገፋፋት የለባቸውም ። በዓለም ላይ ብርሃን ፣ ሙቀትና ነፋስ ምሉአን ሁነው ሳለ መገፋፋት እንደሌለባቸው በሥላሴ ምልአተ አካልም መገፋፋት የለም ። መልክ አለው ስንል ከእኛ መልክ ልዩ ነው ። የአካሉ ርቀትም ከመላእክት አካልና ከአሳባቸው ይልቅ የረቀቀ ነው ።

የሥላሴ በረከት በሁላችን ላይ አድሮ ይኑር !

ሐምሌ 7 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ