መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » ከተማይቱን አይቶ አለቀሰላት » ከተማይቱን አይቶ አለቀሰላት -5

የትምህርቱ ርዕስ | ከተማይቱን አይቶ አለቀሰላት -5

ንድ ሰው:- “ማዘን ተለይቶኝ ሄዶአል” ብሎ የተናገረውን አስታውሳለሁ ። ብዙ መከራና ስቃይ ያዩ ፣ ጆሮአቸው መርዶ የጠገበ ሰዎች ማዘን ተለይቶአቸው ሊሄድ ይችላል ። ተስፋ መቍረጥ እየከበበን ሲመጣም በሞቱት መቅናት እንጀምራለን ። ዘመናችን የንብረት ውድመትን እንጂ የሰው ማለቅን ከቁም ነገር ውስጥ አስገብቶ የሚያወራ አይደለም ። ድሮ አንድ ሰው ሲሞት የከተማው ሁሉ ኀዘን ነበረ ፣ አሁን ግን ስንት ሰው ሞተ እንላለን ። ሰው ሰው የሆነበት ዘመን አልፎ ሰው ቍጥር ሆነ ። ሞትን እየለመድነው መምጣታችን በጣም ያሳስባል ። በጦርነት ውስጥ ያሳለፉ ሰዎች የሥነ ልቡና እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ፣ ሞትን ለምደውታልና ። ስቃይን ማየት ፣ የስቃይ ተባባሪ መሆን ትልቅ ሕመም ነው ። እነዚህ ሰዎች ወደ ማኅበረሰቡ ከመቀላቀላቸው በፊት እርዳታ ያሻቸዋል ፣ ማዘን የተለየው አደጋ ይፈጥራልና ። ማዘን እየተለየን ሲመጣ አንድ ችግር ውስጥ እንዳለን መገንዘብ አለብን ። ጌታችን ስለ ከተማይቱ በማልቀሱ የርኅራኄን መንገድ አሳየን ። እርሱ ራሱ፡- “የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው” ብሎ ነበር ። ያስተማረውን በተግባር አሳየ ።

ኢየሩሳሌም የአሁኑን ደስታ ብቻ አየች ፣ ጌታ ግን የወደፊቱን መከራ አየ ። “የዘፈን ቤት ሳይፈርስ አይቀርም” እንዲሉ ብዙ መቦረቅ ብዙ መተከዝ ያመጣል ። ደስታን በቅጡ ካልያዙት የሞት መንገድ ይሆናል ። እንባ የልብ መልእክተኛ ነው ፣ የክርስቶስ እንባም የልቡን ፍቅር የሚገልጥ ነው ። ኢየሩሳሌም የወከለችው የሰውን ነፍስ ነው ። ጌታ ፍቅርና ፍርድ በእጁ ቢሆኑም ፍቅርን ያስቀድማል ። ፍርድ ፍቅርን ለገፉ ይመጣል ። ያለቀሰውን ጌታ ኢየሱስን መምሰል አለብን ። ያ እንባ ኢየሩሳሌም ለራስዋ ጥፋት የምታለቅሰው ነበር ። እርስዋ ደንዳና ሆናለችና ጌታ አለቀሰ ። ዛሬም በጥፋት ጎዳና ላሉት ማልቀስ ይገባናል ። ፍርዱን ባንለምንባቸውም ሁሉም የእጁን መቀበሉ አይቀርም ። ለሌሎች መጥፋት ማልቀስ ደካማነት ሳይሆን የክርስቶስን ምሳሌ መከተል ነው ። አስቀድሞ የሰው ሥነ ምግባር ፈርሶ ነበር ፣ ቀጥሎ ሕንፃዎች ፈረሱ ። ለማታለቅሰዋ ከተማ ጌታ አለቀሰ ። እንባ አልነበራትምና እንባውን አፈሰሰላት ። አልተጸጸተችምና አዘነላት ። ብዙ ሰው የሚያለቅሰው ኃጢአቱንና ግፉን ለመፈጸም አቅም ሲያጥረው ነው ። እልህ ያስለቅሰዋል ፣ በግፍ የሚወዳደር ሰው አቅም ሲያንሰው ያዝናል ። መጸጸት የሕሊና ሕያውነት ምልክት ነው ። ሕሊና እንደ አካል የሕመምና የሞት ዘመን አለው ። ሕሊና መጸጸት ሲያቆም ሞቷል ማለት ነው ። የምንጸጸተውና ንስሐ የምንገባው መንፈስ ቅዱስ ሲወቅሰን ነው ። መጸጸት ያቆመ ሰው መንፈስ ቅዱስ እየራቀው ነውና መንቃት አለበት ።

“ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ አይቀርም” የሚለው ዝነኛ ትንቢት በኢየሩሳሌም ተፈጽሟል ። ኃጢአትም እንደ ሕንፃ ነው ። ኃጢአት በአንድ ቀን አይገነባም ። ዕለት ዕለት እያደገ ይመጣል ። የተካበው የኃጢአት ድንጋይ ይፈርሳል ። ጌታችን ከእንባው ቀጥሎ የተናገረው አለ፡- “ለሰላምሽ የሚሆነውን በዚህ ቀን አንቺስ ስንኳ ብታውቂ ፤ አሁን ግን ከዓይንሽ ተሰውሮአል ። ወራት ይመጣብሻልና ፥ ጠላቶችሽም ቅጥር ይቀጥሩብሻል ይከቡሻልም በየበኵሉም ያስጨንቁሻል ፤ አንቺንም በአንቺም ውስጥ የሚኖሩትን ልጆችሽን ወደ ታች ይጥላሉ ፥ በአንቺ ውስጥም ድንጋይ በድንጋይ ላይ አይተዉም ፥ የመጐብኘትሽን ዘመን አላወቅሽምና።” (ሉቃ. 19 ፡ 42-44) ። ዛሬ እንኳ ዕድል ነው ። ዕድል እያለው ዕድል የሚጠብቅ አይሳካለትም ። ሰው ለብዙ ነገሮች እውቀት አለው ። አንድን ሥራ ለመሥራት ብዙ ዓመታት በትምህርት ይዘጋጃል ። ለሰላሙ የሚሆነውን ግን አያውቅም ። ለሰላም ዋጋ እየከፈልን እንጂ ሰላምን እየሠዋን መኖር ተገቢ አይደለም ። ብርም ወርቅም ከሰላም አይበልጥም ። ደማቅ ከተሞች የጥይት ድምፅ አይሰማባቸውም ። ድምፅ አልባ ጦርነት ግን በሕሊና ውስጥ ይከናወናል ። የተደላደለ ኑሮ የሚኖሩ ሕዝቦች በከፍተኛ ጭንቀትና አለመርካት ይሰቃያሉ ። ምቾት ብቻውን የሕይወት መልስ አይደለም ። እንደውም ሕይወት ይህ ብቻ ነው ወይ ? የሚል ጥያቄ ያሥነሣል ። የመጎብኘትሽን ወራት አላወቅሽምና አላት ። ዘመነ ሥጋዌ በሙሉ የእግዚአብሔር ጉብኝት ነው ። ጌታ ከዚህች ከተማ ስህተትዋን እንድታምን ብቻ ፈለገ ። የለውጥ መነሻው ስህተትን አምኖ ይቅርታ መጠየቅ ነው ። ይቅርታ የሚጠይቅ ሰው ትልቅ ሰው ነው ። ለራሱም ክብር አለው ። እኛ ኢትዮጵያውያን እንደ ሰማይ መላእክት ስለሆንን ይቅርታ መጠያየቅ አያስፈልገንም ። ይቅርታ መጠየቅ ሰው መሆንን መቀበል ነው ።

ጌታችን ስህተትን እንደ አለማወቅ ይመለከተዋል ። ለኢየሩሳሌም “ብታውቂ” ደግሞም “አላወቅሽምና” በማለት ተናገረ ። መስቀል ላይም “አባት ሆይ ፥ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው አለ።” እኛ ሰዎችን ይቅር ማለት የሚያቅተን አውቀው ነው ብለን ስለምናስብ ነው ። እንኳን ሰው እንስሳም ሲያጠፋ አውቆ ነው እንላለን ። ጌታችን ኃጢአተኞችን እንዳላዋቂ እያየ ያስተምራቸዋል ፣ እንደ ሕመምተኛ እያየ ያክማቸዋል ። ሐኪም እንዴት በዚህ በሽታ ታመምህ ? ብሎ በሽተኛውን አይወቅስም ። ጌታ ለማዳን ይበረታል ። እኛ ደግሞ ለመውቀስ እንበረታለን ። ከሰዎች ጋር ያለንን ግንኙነት በወቀሳ ስንጀምር ይሸሹናል ። ምክንያቱም ዋጋ የላችሁም ያልናቸው ስለሚመስላቸው ነው ። በእነርሱ ላይ ተስፋ እንዳለን በመግለጥ መጀመር አለብን ። እርሱም ያላቸውን ጥሩ ነገር መናገር ነው ።

ጳጉሜን 4 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ