በፍቅር የተፈጠረ ዓለም ያለ ፍቅር መቀጠል አይችልም ። ፍቅር በሰው ሕይወት ውስጥ አማራጭ ወይም ትርፍ ነገር አይደለም ። ፍቅር እምነትን ፣ ተስፋን ያስገኝልናል ። የዛሬን ሥራ ለማከናወን እምነት አስፈላጊ ነው ። ነገ ላይ ለመድረስ ተስፋ ሠረገላ ነው ። ያለ ፍቅር ያለፉትን ክፉ ገጠመኞች በይቅርታ ማለፍ ፣ የዛሬን መክሊትነት መጠቀም ፣ የነገን ወራሽነት ማረጋገጥ አይቻልም ። ትላንት ይቅርታ ይፈልጋል ፣ ለራሳችንም ሆነ ለሰዎች ስለ ትላንቱ ጉድለት ይቅርታ መስጠት ካልቻልን ዛሬና ነገ ይበላሻሉ ። ለዛሬ እምነት ያስፈልጋል ፣ እምነት ዕዳ ነውና ሰዎች ስናምናቸው ይታመኑልናል ። አራዊት እንኳ አምኖ የቀረባቸውን ሕፃን አይተናኮሉም ። ለነገ ተስፋ ግድ ነው ። የነገ ተስፋ ዛሬን ለመሮጥ ያግዘናል ። ብዙዎቻችን ዛሬ ላይ የምንደክመው ለነገ ነው ። ለዛሬ በእጃችን ያለው በቂ ነው ። ሰው ማለት ያልመጣውን ነገ ለመውረስ የሚፈልግ ተስፈኛ ፍጡር ነው ። እግዚአብሔር ይህን ዓለም ሲፈጥር እጠቀም ብሎ ፣ ሰውን ከአፈር ሲያበጅ እከብር ብሎ አይደለም ። ዓላማው ጸጋውን ለማካፈል ነው ። ይህም የፍቅር ጠባይ ነው ። ፍቅር በጠባዩ ሰጪ ነው ። ፍቅር መቀበል ሳይሆን መስጠት ነው ። መውደድ እንጂ መወደድ ፍቅር አይደለም ። ብዙ ነገሮችን እንወዳለን ። መኪናን ፣ ቤትን እንወዳለን ። በዚያ መጠን ሰውን ብንወድ ገና ፍቅር ላይ አልደረስንም ። ሰውንም በምንወድበት ፍቅር እግዚአብሔርን ብንወድ ገና ፍቅረ እግዚአብሔር ላይ አልደረስንም ። ምክንያቱም እግዚአብሔር ልዩ ፍቅር ይፈልጋልና ።
እግዚአብሔር ሁሉን ካዘጋጀ በኋላ ሰውን ፈጠረ ። ሰው ከመፍጠሩ በፊት የሚያስፈልጉት ነገሮች ተፈጥረዋል ። ለነገ ትውልድ የምናስበው ፍቅር ሲኖረን ብቻ ነው ፤ ደግሞም ሰው የሚጨነቀው ከእርሱ በፊት ለተፈጠሩ ነገሮች ነው ። እግዚአብሔር ሰውን በመልኩ ፈጠረው ፣ የጸጋ ገዥ አደረገው ፣ የሁለት ዓለም ወራሽ እንዲሆን ፈቀደለት ፣ እንስሳት በምድር ፣ መላእክት በሰማይ ብቻ ወራሽ ናቸው ፣ ሰው ግን ልዩ ነው ፤ ሰው የእንስሳትም የመላእክትም ወገን ነው ። ለሰው የሕይወትን እስትንፋስ እፍ አለበት ፣ ትእዛዝን ሰጠው ፣ ከጎኑ ሔዋንን ፈጠራት ። ይህም እንደ ባዕድ እንዳያያትና እንዳይጠላት ነው ። እነዚህ ሁሉ የፍቅር መገለጫዎች ናቸው ። ሰው የሁለት ዓለም ወራሽ ከሆነ በምድርም በሰማይም የሚያስፈልገው ፍቅር ነው ። የሰው ልጅ ለፍቅር ካልኖረ ሞትን ይፈራል ። የሚኖርበት ዓላማም ባዶ ይሆናል ። እግዚአብሔር ሰውን ዘላለማዊ አድርጎ መፍጠሩ ሰው ከእርሱ ጋር ለዘላለም እንዲኖር ነው ። እኛ ግን ለረጅም ጊዜ ከሰዎች ጋር በወዳጅነት ለመቆየት እንፈራለን ። ሰው እንደሚበድለው እያወቀ ሰውን ፈጠረው ። እኛ እንደሚበድለን ብናውቅ ማንንም መቅረብ አንችልም ። አግዚአብሔር ፍቅሩን ለሰው የገለጠው በዋናነት በመልኩ በመፍጠር ፣ ሲጠፋ በመፈለግና በመስቀል ላይ ሞቶ በማዳን ነው ። ዳግመኛ የሚመጣውም ሊሰበስበው ነው ። ይህም ፍቅር ነው ። የሚመጣውም በሙሽራ መልክ ነውና ዳግም ምጽአት የፍቅርና የሰርግ ቀን ነው ። ወዮ የዚያን ጊዜ የሚባልበት አይደለም !
እግዚአብሔር የፍቅር ትምህርት ቤት ነው ። ፍቅርን ከእርሱ እንማራለን ። ጌታ የፍቅር ውቅያኖስ ነው ፣ ስንጎድል ከእርሱ እንቀዳለን ። እግዚአብሔር የፍቅር አገርዋ ነው ፣ ስንጠጋው ማረፊያ እናገኛለን ። እግዚአብሔር የፍቅር ዓምድ ነው ፣ ስንንገዳገድ እንይዘዋለን ። የእግዚአብሔር ፍቅር የክርስትናችን መሠረት ነው ። እንዲህ ለዛ ያጣነው ፣ በአደባባይ አንዳችን አንዳችንን ለመቅበር የምንጥረው ከመሠረታዊው ዓላማ ስለ ወጣን ነው ። ፍቅር የሌለው ሃይማኖት አይማርክም ፣ ፍቅር የሌለው ጸሎት አያርግም ። ፍቅር የሌለው ከተማ ውጡ ውጡ ያሰኛል ። ያለ ፍቅር ደሴት ከመግዛት በፍቅር የውሻ ቤት መኖር ይሻላል ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተገለጠው ፍቅር እንዲህ ነው ብሎ ሊያስተምር ነው ። እርሱ አካላዊ ፍቅር ሁኖ ተገለጠ ። ድሆችና ባለጠጎችን በአንድ ዓይን ተቀበለ ። ካህናት ኃጢአተኞች እኩል ሳይሳቀቁ ይቀርቡት ነበር ። ሕፃናትንም በሊቃውንት መጠን አቅርቧል ። የሙት ልጆች በሆኑ በእነ አልዓዛር ቤት ይመላለስ ነበር ። ያለ ወላጅ ያደጉ ልጆች “ልጄ” ብሎ የሚጠራቸው ሲያገኙ ነፍሳቸው ትቦርቃለች ። ካህናትና አገልጋዮች “ልጄ” ብለው በመጥራት ይህን ክፍተት ይሞላሉ ። ጌታችን የእነ አልዓዛርን ቤት ክፍተት እየሞላ ነው ።
ይቀጥላል
መስከረም 13 ቀን 2018 ዓ.ም.