እግዚአብሔር በፍቅር ውበት የሚኖር አምላክ ነው ። ሰው ብርሃናዊ ፊት ፣ የሚማርክ ገጽ ፣ የማይጠገብ ንግግር ፣ ንጹሕ ልብ የሚኖረው በፍቅር ሲቃኝ ነው ። ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የምንገባበት የይለፍ ካርዱ ፍቅር ነው ። እምነታችን የተመሠረተው ስለ ኃጢአተኞች በሞተውና በተነሣው የፍቅር ጌታ በሆነው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ነው ። ፍቅር ከሌለን አላመንም ማለት ነው ። ያለ ፍቅር በልምምድና በልዩ ተልእኮ የሚከወኑ ደግ ሥራዎች ይኖራሉ ። ሁሉም በጎ ሥራዎች እውነተኛ የሚሆኑት ሕይወትም የሚኖራቸው በፍቅር ሲደረጉ ብቻ ነው ። እግዚአብሔር እጅግ የሚማርክ አምላክ ነው ። እኛ ለደግ ሰው ብንሞትም አይቆጨንም ። “ለገቢህ ተንገብገብ” ይባላል ። በችግርህ ለሚደርስልህ ወዳጅህ በእጅህም በዓይንህም አልቅስ ማለት ነው ። “ለእገሌ አንገቴን እሰጣለሁ” ብለን በአደባባይ እንቆማለን ። ክርስቶስ ግን አንገቱን የሰጠው ፣ በመስቀል የዋለው ለኃጢአተኞችና ለደካሞች ነው ። ይህም የራሱን ፍቅር ብቻ ያስረዳል ።
ፍቅርና ቸርነት በእኛ ዘንድ ቢገኙ እንኳ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን በፍጹምነት ይኖራሉ ። እግዚአብሔር ፍቅር ነው ስለ ተባለ ያለ ፍቅር የተገለጠበት ዘመን የለም ። እኛ አባት ስንሆን የልጅ ፍቅርን መለማመድ ጀምረናል ። የእግዚአብሔር ፍቅር ግን ልምምድ አይደለም ። የአዲስ ኪዳን ትልቁ ጸሎት “አባታችን ሆይ” የሚል ነው ። እግዚአብሔር በቤተሰባዊ ፍቅር ወደ እኛ መምጣቱን የሚያሳይ ነው ። ጸሎት የፍቅር ንግግር ነው ። ጸሎት ዋነኛ ዓላማው አምጣ ማለት ሳይሆን ኅብረት ነው ። ፍቅር ከእግዚአብሔር የኃይል ጠባያት የሚመደብ ነው ። ፍቅር ኃያል ነው ። ኃያል ወልድን ወደ ምድር የሳበው እስከ ሞትም ያደረሰው ፍቅር ነው ። እግዚአብሔር ፍቅር ነው ስንል ሲመሽ ለመጡ ዋስትና ነው ። እግዚአብሔር በጥበብ ያቅዳል ፣ በፍትሕ ነገርን ይለያል ፣ በፍቅሩ ይምራል ። ሁሉም ጠባያቱ ያለ ፍቅሩ አይገለጡም ። ፍርዱም ፣ ቅጣቱም ፍቅር ነው ።
ነገረ እግዚአብሔርን ስንማር ፍቅሩን እየተገነዘብን እንመጣለን ። የእግዚአብሔር ፍቅር በተለያዩ ነገሮች ቢገለጥም አንድ ልጁን በመላክ የፍቅርን ጥግ አሳይቷል ። ለሚወዱት ሰው ራሳቸውን አሳልፈው ስለ ሰጡ ሰዎች ታሪክ ያነሣል ፣ ልብ ሁሉ እየሳሳ ያዳምጠዋል ። አንድ ልጁን ለበደለ ባሪያ ለአዳም አሳልፎ የሰጠው የአብ ፍቅር ግን ተዘንግቷል ። ዓለም ይህን ፍቅር መስማት አለመፈለጉ ይገርማል ። ከእግዚአብሔር ፍቅር ውስጥ ምሕረት አለ ። ምሕረት በነጻ መልቀቅ ነው ። የበደለንን ከሕሊና እስራት መፍታት ፣ ለጎደለበት ሳያሳቅቁ መሙላት እርሱ ምሕረት ይባላል ። ፍቅር ሲኖረን ይህን ምሕረት እንለማመዳለን ። ልብ አድርጉ ብዙ መንፈሳዊ ጠባያት የልምምድ ውጤት ናቸውና ዛሬ መጀመር አለብን ። ከእግዚአብሔር ፍቅር ውስጥ ቸርነት አለ ። ቸርነት የሚያፈሱ እጆች ማለት ነው ። ይህ ፍቅር የነካው ሰው እጆቹ ልሙጥ ሳይሆኑ ዘርዛራና የሚያፈሱ ናቸው ። የኃጢአት አውራው ስስት መሆኑን ብዙ ሰው አላወቀም ።
ከእግዚአብሔር ፍቅር ውስጥ አዛኝነትና ርኅራኄ ይወጣል ። ጌታችን በአልዓዛር መቃብር ላይ ያለቀሰው ለእኅቶቹ የልብ ስብራት አዝኖ ፣ ከሚያለቅሱ ጋር ለማልቀስ ነው ። ይህ ፍቅር የገባው ሰው ከሰርግ ቤት ይልቅ ልቅሶ ቤት መሄድ ያስደስተዋል ። ልቡ በቶሎ ይነካል ፣ የሌሎችን ኀዘን ይካፈላል ። ከእግዚአብሔር ፍቅር ውስጥ ይቅርታ አለ ። ይቅርታ ከትላንት በደልህ የነገ ካሣህ ይበልጣል የሚል እምነትን ለወደቀ ሰው መስጠት ነው ። ይህ ፍቅር ሲገባን ይቅርታ እናደርጋለን ። ይቅር ያላልነው ሰው ታስሮ የሚሮጥ ነው ። ያዘነብን ሰው ካለ ታስረናል !
ይቀጥላል
መስከረም 15 ቀን 2019 ዓ.ም.