መግቢያ » ልዩ ልዩ ሁለት » ስም ያለው

የትምህርቱ ርዕስ | ስም ያለው

“ስም ያለው ሞኝ ነው” ይባላል ። ስሙ ሲጠራ እኔን ነው ብሎ ይዞራል ። ሌላ ሰው የተጠራ መሆኑን ሲገነዘብ በራሱ ስቆ “ስም ያለው ሞኝ ነው” ይላል ። አጠገባችን ያሉ ሰዎች ሳይቀሩ የእኛ ስም ሲጠራ ዞር ይላሉ ። ሌላ ሰው እየተጠራ መሆኑን ሲያውቁ በራሳቸው ስቀው “ስም ያለው ሞኝ ነው” ይላሉ ። ስም ሞኝ ያደርጋል ፣ ሌላ ሰው ሲጠራም እኔ ነኝ እንድንል ያደርጋል ። ትልቅ ተብሎ ከሚጠራ ቤተሰብ የተወለደ ሞኝ ነው ። ዘመኑን መቀበል ፣ ዘመኑ ከፈቀደለት ጋር በጋብቻ መተሳሰር አልቻሉም ። በየሄዱበት አገር የሚታወቁ ይመስላቸዋል ። ቀኑ ሲገፋ የገዛ አገራቸውም እንደሚረሳቸው ዘንግተዋል ። ጊዜያዊ እንጂ ዘላለማዊ ትልቅነት በዓለም ላይ የለም ፣ የዓለም ክብር ወረፋ እንጂ ቀጣይ አይደለም ። ስም ካለው ቤተሰብ የተወለደ ስለ ትልቅነት ሲወራ እኔ ተራ ሰው አይደለሁም ብሎ የራሱን ትልቅነት በኩራት ማውራት ይጀምራል ፣ የሌሎችን አናሳነት ለመግለጥ ይዳዳዋል ። ዝቅ ብሎ እንዳይሠራ ኩራት ይዋጋዋል ፣ ብቸኝነትን እንዳያሸነፍ ከሰው ርቋል ። ስም ሞኝ ያደርጋል ፣ ሞኝ ቀኑ ሲያልፍ የማያውቅ ነው ።

የዚህን ዓለም ተለዋዋጭነት የማይቀበል ሰው ኀዘነተኛ ነው ። እንኳን መለወጥ ማለፍ የሚጠብቀው ዓለም ላይ ነን ። እንኳን መድከም መሞትን እየጠበቀ ባለ ሥጋ ውስጥ ነን ። እንዳለ የሚኖር እግዚአብሔር ብቻ ነው ። ሞኝ ከከፍታ ሲወርድ መቀበል ያቅተዋል ። ከድህነት በላይ ቁጭቱ ዕድሜውን ያሳጥረዋል ። እንዴት ለሚለው ጥያቄ ሙሉ መልስ ማግኘት ይቸግረዋል ። ጊዜ እየገፋ ሲሄድ የገዛ አካልም መለገም ይጀምራል ። እንዳማረብን እንዲወስደን መጸለይ መልካም ነው ። ስም ያለው ሞኝ ነው ። ግሪኮች ጥንታዊ ሥልጣኔ ያላቸው ፣ አሻራቸው እስካሁን ድረስ በመላው ዓለምና ጥበብ ውስጥ ያለ ነው ። የጥንት ስማቸውን በየቀኑ ቡና ሲጠጡበት ፣ ሌላውን ከእኛ በኋላ የነቃ ነው ሲሉበት እንደ ቀዳሚነታቸው መፍጠን አልቻሉም ። ታሪክ ያለው ሕዝብ መሆን መልካም ነው ። ታሪክ ቁጭትን እንጂ ትረካን ብቻ ከወለደ ገዳይ ነው ። አገራችን ስም ካላቸው አገራት ተርታ የምትመደብ ናት ። ታሪካችን ግን ዛሬ ላይ ለዕድገት ካላነሣሣን ሞኝ ያደርገናል ። አኵሱምን የሠራ ሕዝብ ሆነን እንዴት እንራባለን ? ካላልን አደገኛ ነው ።

ታሪክ ደስታና ኩራት ይሆናል ፣ ዳቦ መሆን ግን አይችልም ። የሌላ አገር መሪዎች የእኛን ስምና ታሪክ ካነሡ መቼም አንረሳቸውም ። ቢገድሉን እንኳ ልንጠላቸው አንችልም ፣ ስም ሞኝ ያደርጋልና ። ስማቸው ሲነሣ ለአወዳሽ ለዘዋሪ ገንዘባቸውን የሚበትኑ ብዙዎች ናቸው ፤ ስም ሞኝ ካደረገን አብሮ መሥራት ሳይሆን አብሮ መዋደቅ ያምረናል ። ሰላም የማናገኝበት መንገድ አንዱ ስም ሞኝ አድርጎን ነው ። “የግጭት ሥሩ ድህነት ነው” ተብሏል ። የእርስ በርስ መተላለቃችን መነሻው ድህነት ነው ። ድህነትን ለማስወገድ ደግሞ ከጦርነት ፋታ ማግኘት ያስፈልጋል ። ኩራታችን ወንድምን እንጂ ድህነትን መጸየፍ አልቻለም ።

ስም ያለው ሞኝ ነው ። ታዋቂ ሰዎች ፈገግ ፈገግ እያሉ ይሄዳሉ ። ሁሉም ሰው ያውቀናል ብለው ስለሚያስቡ ሁሉንም ሰው ለማስደሰት ይሞክራሉ ። ያገኙት ስም ሞኝ እያደረጋቸው ያወቁትን እውነት ሳይሆን ብዙኃኑ የተስማማበትን ውሸት ይኖራሉ ። ስም ሞኝ አድርጓቸው ብዙ አዋቂዎች የተማሩትን እውቀታቸውንና ልፋታቸውን አርክሰውታል ። ለብዙዎች እልቂትም ምክንያት የሆኑ ታሪክንና እውነትን የቀበሩ አዋቂዎች ብዙ ናቸው ። ብዙ አዋቂዎች የጨካኞች አወዳሽ ሆነው ታሪካቸውን አበላሽተዋል ፣ አገርንም ገድለው ቀብረዋል ።

ስም ያለው ሞኝ ነው ፣ ሁሉ የሚወደው ይመስለዋል ። ጅል ሁሉ ይወደኛል ብሎ ያስባል ። በርግጥም አይጠቅመንም አይጎዳንም ብለው ሁሉም አጫዋች ያደርጉታል ። ስም ያለው ሰዎች ሁሉ ስለ እርሱ የሚያወሩ ፣ እርሱ ያለፈ ቀን ዓለም የምንገለበጥ መስሎ ይሰማዋል ። ሁሉን ለማስደሰት እንደ መኖር ያለ የቁም ኵነኔ የለም ። የተፈጠርነው ለእግዚአብሔር ክብር እንድንኖር እንጂ ሁሉን ለማስደሰት አይደለም ። ሰዎች የበለጠ የሚከፉብን ላስደስታቸው ብለን ስንነሣ ነው ። እግዚአብሔር የሚወደውን ብቻ እናድርግ ፤ ያን ጊዜ እግዚአብሔርን የሚያውቅ ይደሰትብናል ።

ምድራዊ ስም ነጻነትን የሚገፍ ነው ። ስም ያላቸው ነጻነትን በማጣት በጭንቀት ኖረው ፣ በአደጋ ያልፋሉ ። የሰው ስሜታዊ ፍቅር አድካሚ ነው ። በእውነት የሚወዱን ግን ጥቂት ናቸው ። የሙያ ወዳጆቻችን የእኛ ወዳጆች አይደሉም ።

ነጻነት የሚገኘው በሰው ሳይሆን በእግዚአብሔር በመታወቅ ነው ። ደግሞም አዋቂ እንጂ ታዋቂ መሆን ምን ይሠራል ? ዝና የገንዘብ ማግኛ ሊሆን ይችላል ፣ ግን የደለበ ባሪያ ያደርጋል ፤ ከእውነት ጋር የኮሰሰ ድሀ መሆን ይሻላል ። ስም ሳንፈልገው ከመጣ በየዕለቱ በማንበብ ፣ በመጸለይ ፣ አቤቱ አድነኝ በማለት መፈጸም ይገባናል ። ይህ ዓለም ሲነጋ እንደ ባንዲራ ይሰቅላል ፣ ሲመሽ ያወርዳል ።

ኅዳር 10 ቀን 2019 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ