መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » ወፎችን ተመልከቱ » ወፎችን ተመልከቱ -2

የትምህርቱ ርዕስ | ወፎችን ተመልከቱ -2

ጭንቀት ለሚታገላችሁ

በአንደኛው የዓለም ጦርነት አንድ የፈረንሣይ ወታደር ከሁለት አንዱ ይሆናል መጨነቅ የለብኝም የሚል መርሕ ይዞ ዘመቻ ወርዶ ነበር ። “ከሁለት አንዱ መሆኑ የማይቀር ነው ፣ በጦር ዐውዱ ከፊት ለፊት እሰለፋለሁ አሊያም ከኋላ እሆናለሁ ። ከፊት ግንባር ከሆንሁ ከሁለት አንዱ ያጋጥመኛል ፣ አደጋ ይገጥመኛል ፣ ላይገጥመኝም ይችላል ። ለአደጋ ከተጋለጥሁ ከሁለት ነገሮች አንዱ ይሆናል ። እቆስላለሁ ላልቆስልም እችላለሁ ። ከቆሰልሁ ከሁለት ነገሮች አንዱ አይቀርም ። እሞታለሁ ወይም እድናለሁ ። የምድን ከሆነ መጨነቅ አያስፈልገኝም ፣ ከሞትሁ ደግሞ መጨነቅ አልችልም” በሚል መመሪያ ስጋቱን ጥሎ ነበር ።

ከሁለት አንዱ በግድ ይሆናል ። ዓለም ሁለት እንጂ ሦስትነት የለውም ። ወይ ቀን ነው ወይም ሌሊት ነው ። ክረምት ይሆናል አሊያም በጋ ነው ። ዓለም ሁለት ብቻ አይደለም ፣ የሚሆነው ሁሉ ሲሆን የነበረ ነው ። ብዙ ጭንቀቶች በሆኑ ነገሮች ላይ ሳይሆን ሊሆን ይችላል በሚል ስጋት ላይ የሚመጡ ናቸው ። ብዙ ጊዜ እንደ ጠበቅነው አይሆንም ። ያልመጣ ነገር ከሆነ ክፉ ከማሰብ መልካም ሊሆን ይችላል ብለን ብናስብ ጥሩ ነበር ። ሥጋ ግን እንደ ስሙ ሲሰጋ ይስተዋላል ። ከተጨባጩ መከራ በላይ በሕሊናችን የምንፈጥረው መከራ ብዙ ነው ። ሩቅ ምሥራቆች ስለ ሁለት ቀስቶች ይናገራሉ ። አንደኛው ቀስት የሚወረወርብን ሲሆን ሁለተኛው ቀስት ግን ወደ ራሳችን የምንወረውረው ነው ። እርሱም፡- ለምን በእኔ ላይ ይህ ሁሉ ደረሰ ? የሚከፈለኝ ዋጋ ይህ ነው ወይ ? እንዴት ከዚህ እወጣለሁ ? ጉዳቱ የማይካስበት ደረጃ ላይ ቢደርስስ ? በማለት ወደ ራሳችን ቀስትን እንወረውራለን ። ከመጣው ችግር በላይ የምንፈጥረው ጭንቀት የበለጠ ያሰቃየናል ። ጭንቀት ለመጣው ችግር ወለድ መክፈል ነው የሚባለው ለዚህ ነው ። ጭንቀትን የምናስወግድበት ትልቁ መንገድ እምነት ሲሆን እምነታችን ደግሞ በቃሉ ማደግ አለበት ። በቃሉ ውስጥ ያሉት እልፍ ተስፋዎች ጭንቀትን ያርቁልናል ።

አንድ ደፋር ሰው አገኘሁ ። ብዙዎቻችን ፈሪ ስለ ሆንን ደፋርን ማድነቅ እንወዳለን ። እርሱ ለደፈረውም እኛ የምንፈራበት ጊዜ አለን ። ከልባቸው የሚደፍሩ ሰዎች ዕድሜአቸው ሳብ ሲል እናያለን ። በርግጥ ደፋርነት ጥበብ ያስፈልገዋል ። ደፋርነትም ለተጠቁት በመቆም ሲገለጥ ደስ ይላል ። እግዚአብሔር ተቆርቋሪ ሰው እንዳይጠፋና ምድር በአድርባዮች ጨለማ እንዳትሆን ለዚህ ሰው ዕድሜ ይሰጠዋል ። እኒህን ደፋር ሰው፡- “ደፋር የሆኑት እንዴት ነው ?” አልኳቸው ። ወይ እታሰራለሁ አሊያም እሞታለሁ ። ብታሰር እፈታለሁ ብሞት እቀበራለሁ የምፈራው ለምንድነው ?” አሉኝ ። ከሁለት አንዱ ይሆናል ። ያሰቡት መታሰርም መሞትም ላይኖር ይችላል ። መታሰርም መፈታት አለው ፣ ሞትም መቀበር አለው ፣ አይቀበርም ተብሎ የታገተ ሬሳ የለም ። ከሞት ወዲያ ሊያሳድድ የሚችል ማንም የለም ። ሞት ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለአሳዳጆቻችንም ገደብ ነው ።

ከሁለት አንዱ ይሆናል መጨነቅ አይገባም ። የምንችለውን ማድረግ ተገቢ ነው ። ልንቆጣጠረው በማንችለው ነገር ራስን ማሰቃየት ግን ተገቢ አይደለም ። ሁሉም ነገር ከልኩ አያልፍም ። በዚህ አታልፍም ብሎ መንገድ ቢዘጋብህ መንገድ የግለሰብ አይደለምና ግድ መከፈቱ አይቀርም ። ንብረትህን ቀምቶ ቢጓደድ የሰው የሰው ሊሆን አይችልም ። ነገሮችን በተራ ማስኬድ ለሚቀድመውና ላስቸኳዩ ቅድሚያ መስጠት ጭንቀትን ለመቆጣጠር ይረዳል ። ሁሉን አሁን ካላደረግሁት ማለት የተፈጥሮን ሕግ አለመረዳት ነው ። ሁሉንም አለማድረግ ሊመጣ ይችላል ።

እነዚያ የሞቱት ሰዎች ስለ መውጣታቸው እንጂ ስለ መመለሳቸው አያውቁም ነበር ። ንግግር ጀምረው ሰሚው በተመስጦ እያዳመጣቸው ሳይጨርሱ ብዙዎች እየሞቱ ነው ፣ ኧረ ቅዳሴ ጀምረው ሳይፈጽሙ ካህናት እየተጠሩ ነው ። እያዜሙ ዜማውን ሳይቋጩ ዘፋኞች እያሸለቡ ነው ። እነዚህ መንገደኞች እንደ እኛው በሳቅ በተሸፈነ ኑሮ ራሳቸውን ያሰቃዩ ነበር ። ይሉኝታ የለሾችን እያባበሉ ይኖሩ ነበር ። ከአቅም በላይ በጀመሩት ኑሮ ተጣበው ነበር ። ተበድረው ልጆቻቸውን ያቀናጡ ነበር ። ሲሞቱ ግን ይህ ሁሉ የውሸት ኑሮ አብሮ ያበቃል ። እኮ የምንጨነቀው ለማን ነው ? ንብረት ከሌለን የሚያለቅሱልን ሰዎች በእውነት ያለቅሱልናል ፣ አሊያም ተገላገለ ይሉናል ። ንብረት ካለን ሬሳችን ሳይወጣ ቁልፋችን ይፈለጋል ። የሬሳ ኪስ አውላቂዎች ብዙ ናቸው ። የገዛ ዘመዶቻችን በአንድ ዓይናቸው እያለቀሱ በአንድ ዓይናቸው ይስቃሉ ። በሞታችን ላይ ከትልልቅ ሆቴሎች የድግስ ናዳ ይጋዛል ። ከቀብር በኋላ ይረሱናል ። እቤቴ እንዳይመጣ ያልነው ሰው ሊከርም ሻንጣውን ይዞ ይመጣል ፣ የሙት ቤት የሚያስሱ የሃይማኖት ሰዎች ነን ባዮችም በማጽናናት ስም ወራሽ ይሆናሉ ። “የጠሉት ይወርሳል” እንዲሉ የጠላነውና የካድነው ልጅ ንብረታችንን ይካፈላል ፣ ሞተንም አያሳርፉንም ስማችን በየፍርድ ቤቱ ሲጠራ ይኖራል ። የሞቱትን አሳርፍልን የሚባለው ለዚህ ነው ለካ ! ለራሳችን የሰሰትነውን ንብረት የማናውቀው ሰው ይጫወትበታል ። ሁላችንም የማናውቀው ምክትል አብራሪ አጠገባችን አለ ። እኛ ስንሞት እርሱ ይቀጥላል ። ዛሬ መድኃኒት ለመግዛት እንሰስታለን ፣ አንድ ቀን እንኳ ለራሳችን ጊዜ ለመስጠት ፈቃደኛ አይደለንም ። እኛ ስንቆም ዓለም የሚቆም ይመስለናል ፣ እኛ ስንሞትም ዓለም ይቀጥላል ።

ከሁለት አንዱ ይሆናል ። ወይ እኖራለን ወይም እንሞታለን ። ከኖርን ለምን እንጨነቃለን ? ከሞትን ደግሞ መጨነቅ አንችልም ። “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” ተብሏል ። ራሳችንን በልኩ መውደድ አለብን ። “ደግ ለራሱ ክፉ ነው” ይባላል ። ለሌላው ወርቅ እያለበሰ ለራሱ ካልሲ ለመግዛት ይንቀጠቀጣል ። ለራሳችን ክፉ የሚያደርገን ደግነት ትክክለኛ ደግነት አይደለም ። ሲመሽ ለመንጋቱ ፣ ሲነጋ ቀኑ ለማለቁ እርግጠኛ አይደለንምና፡-

1- መጨነቅ የለብንም ። የሆነልን የሆነው ስለ ተጨነቅን አይደለም ። የነገ ስጋት ዛሬን የሚበላ ነቀዝ ነው ።
2- ሰውን ማስቀየም የለብንም ። “እኔ መንገደኛ ተሸኝቶ አዳሪ ፣ ምን ክፉ አናገረኝ እንግዲህ ከቀሪ” ይባላል ።
3- ዘወትር ንስሐ መግባት አለብን ፣ የሰማይ ቁልፉ ንስሐና እምነት ነውና ።
4- መፍራት የለብንም ፣ የሚሆነው ከመሆን አይቀርም ።

የሰማይ ወፎችን ተመልከቱ !

ኅዳር 17 ቀን 2019 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ