መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » ይነጋል ደግሞ ይመሻል

የትምህርቱ ርዕስ | ይነጋል ደግሞ ይመሻል

 “ስለ ኤዶምያስ የተነገረ ሸክም ። አንዱ ከሴይር ፡- ጕበኛ ሆይ ፥ ሌሊቱ ምን ያህል ነው ? ጕበኛ ሆይ ፥ ሌሊቱ ምን ያህል ነው ? ብሎ ጠራኝ ። ጕበኛውም፡- ይነጋል ደግሞም ይመሻል ትጠይቁ ዘንድ ብትወድዱ ጠይቁ ተመልሳችሁም ኑ አለ ።” ኢሳ. 21፡11

 

ኤዶም የዔሳው ስም ነው ። ኤዶምያስ የዔሳው ዘሮች የሚጠሩበት ስም ሲሆን እነርሱ የኖሩበት ሴይርም ኤዶምያስ ተብሎ ይጠራል ። ኤዶም ማለት ቀይ ማለት ነው ። በቀይ ወጥ ብኵርናውን ስለሸጠ ዔሳው ኤዶም ተብሏል ። ዘፍ. 25፡30 ። ዘሮቹም እስራኤል ከግብጽ በወጡ ጊዜ አላሳልፍ ያሉ ፣ በተለያየ ዘመን የእስራኤልን መንግሥት የተፈታተኑ ነበሩ ። በመቃብያን ዘመን ተገርዘው ወደ እስራኤል የገቡ ሲሆን ሄሮድሳውያንም የኤዶም ዘሮች ነበሩ ። ሄሮድሳውያን ታላቁን ቤተ መቅደስ በማደስ ፣ የቤተ ልሔምን ሕፃናት በማስፈጀት ፣ ጌታችን ሲሰቀል ሐሰተኛ ፍርድ በመስጠት ይታወቃሉ ። ከአንዱ አብርሃም የተወለዱ እስማኤልና ይስሐቅ አንዱ በጣዖት የሚያምን አንዱ በሕያው ጌታ የሚያምን ነበሩ ። ከቡሩኩ ይስሐቅ የተወለዱም ያዕቆብ የተወደደ ፣ ዔሳው ደግሞ ለመንፈሳዊ ነገር ክብር ስላልነበረው በእግዚአብሔር የተጠላ ነበር ። አንዱ ክብርን ሲመርጥ ፣ አንዱ ውርደትን ይመርጣል ። የእናት ሆድ ዝንጉርጉር እንዲሉ ከአንዱ ምንጭ ሁለት ዓይነት ጅረት ይፈስሳል ። መንፈሳዊነት ከቤተሰብ ብንወርሰውም በምርጫ የምንቀጥልበት ነው ። ቅድስና በዘር አይተላለፍም ፣ በምርጫ እግዚአብሔርን የምንመስልበትም ነው ። ጕበኛ ማለትም ጠባቂ ማለት ነው ። ሴይር ማለት ጠጉራም ማለት ነው ፣ ዔሳው ጠጉራም ነበርና እርሱን የሚገልጥ ነው ። አሁንም ሴይር ማለት ዐውሎ ነፋስ ማለት ነው ። ስፍራው ዐውሎ ነፋስ ስለማይለየው የተሰጠው ስያሜ ነው ይላሉ ።

 

የእግዚአብሔር ሰዎች ከእግዚአብሔር የተቀበሉትን መልእክት ሸክም ይሉታል ። ሸክም አደራ ነው ፣ የእግዚአብሔር ቃልም የአደራው ቃል ነው ። ሸክም ከዚህ ወደዚያ የሚደርስ ነው ፣ የእግዚአብሔር ቃልም ከእግዚአብሔር ወደ ሰው የሚደርስ ነው ። ሸክም የማያሳርፍ ነው ፣ ቃሉም እስኪያደርሱት የሚያስጨንቅ ነው ። ሸክም ያለ ቦታው አይወርድም ፣ ቃሉም ወደ ተላክንበት ሕዝብ መድረስ አለበት ። ሸክም የሚያጎብጥ ነው ፣ ቃሉም ኃላፊነት ያለበት ነው ። ሸክም የማያስተኛ ነው ፣ ቃሉም አጥንትን የሚቆጠቁጥ ነው ። ኢሳይያስ ስለዚያ ሕዝብ ሸክም ነበረው ፣ ሸክም ተሰጥቶት ነበር ። እስራኤልን መንገድ አላሳልፍም ላለ ፣ የእስራኤልን ልዑላዊነት ለተዳፈረና የአምልኮ ነጻነቷን ለተጋፋ ሕዝብ ሸክም ይሰማው ነበር ። የእግዚአብሔር ፍቅር ፣ ቃሉና ጸሎት ድንበር የላቸውም ። በጸሎት ወገናዊ እንደመሆን እግዚአብሔርን የሚያሳዝን ነገር የለም ። ቤተ ክርስቲያን ለእንስሳትና ለአፍላጋት ሳይቀር ትጸልያለች ።

 

ጠያቂው ከሴይር ነው ። ተጠያቂው ኢሳይያስ ሳይሆን አይቀርም ። ጠያቂው ደጋግሞ ይጠይቃል፡- ጕበኛ ሆይ ፥ ሌሊቱ ምን ያህል ነው ? ጕበኛ ሆይ ፥ ሌሊቱ ምን ያህል ነው ? ብሎ ጠራኝ ።” የሌሊቱን ሰዓት የሚጠይቅ እንቅልፍ የከዳው ነው ። ሰዓት ስለሌለው እየጠየቀ ነው ። የሚጠየቀው ደግሞ በኛው ነው ። በኛው የከተማው ጠባቂ ነው ። ከፍ ባለ ማማ ላይ ተቀምጦ ፣ ሰላይ አሰማርቶ ፣ በአራቱም ማዕዘን ወደ ከተማይቱ ያለውን እንቅስቃሴ እያየ ለንጉሡና ለሕዝቡ የሚያመለክት ነው ። የሌሊቱን ሰዓት የሚጠይቀው ሰው ከቤቱ ወጥቶ የከተማው በር ላይ ሂዷል ። የሚጠይቀው ከሴይር ከኤዶም ወገን የሆነ ሰው ነው ። በኛው ሕዝቡን በጸሎትና በትምህርት የሚጠብቅ ነው ። በጸሎት ከተዋጊዎች ፣ በትምህርት ከራስ አለማወቅ ወገንን የሚጠብቅ ነው ። ሕዝቡ ሲተኛ እርሱ ይነቃል ። ሕዝቡ ሰላም ነው ሲል ጉበኛው ከሩቅ እየመጣ ያለውን ያያልና ያለቅሳል ። ንጉሥና ሕዝብ አደራ የጣሉበት ወይም አደራ የተሰጡት ለማንቃትም የሚተጋ ነው ። አገርን አርግዞ ፣ ንጉሥን ሳይቀር የሚጠብቅ ነው ። እንደ ጋሪ ፈረስ ወደ አንድ አቅጣጫ ብቻ የሚያይ ሳይሆን እየተሽከረከረ በአራቱም ማዕዘን የሚመለከት ነው ። በኛው ሌሊት ብቻውን ሲሆን ይጸልያል ፣ ቀን ሕዝቡን ያስተምራል ። በከተማው በር ላይ ኑሮውን መሥርቷልና የተጣሉትን ያስታርቃል ፣ የቄሣርን ለቄሣር ስጡ ይላል ። አምሽተው የመጡትን ይመልሳል ። ጠላት እንዳይገባ በሩን ይዘጋል ። የእግዚአብሔር ሰዎች በኛ ወይም ጠባቂ ናቸው ። የሩቁን ያያሉ ያሳያሉ ። እየመጣ ያለውን ጥፋት ያሳውቃሉ  ። የእግዚአብሔር ሰዎች የአገር ዓይን ናቸው ።

 

ጕበኛውም፡- ይነጋል ደግሞም ይመሻል ትጠይቁ ዘንድ ብትወድዱ ጠይቁ ተመልሳችሁም ኑ አለ ።”

 

የጕበኛው ምላሽ የሚደንቅ ነው ። ንጋቱ ወዲያው እንደሚመሽ የሚያመለክት ነበር ። ንጋቱ አሦራውያን እስራኤልን ከለቀቁ ወይም ስጋታቸው ካበቃ በኋላ ትንሽ ጊዜ ዕረፍት ይሆንና ባቢሎናውያን ሕዝቡን ማጋዛቸውን የሚያመለክት ነው ። አሦራውያን ሰማርያን የያዙት ከክርስቶስ ልደት በፊት 722 ዓመት ነው ። ባቢሎናውያን ደግሞ በ586 ዓመት ኢየሩሳሌምን አፈረሱ ። ትንሽ ብርሃን ይሆናል ቀጥሎ ጨለማ ይሆናል ። ነግቶ ወዲያው መምሸቱን ያ ጠባቂ ተናገረ ። ቀጣዩን ለማወቅም ጠያቂ ካለ ኑ በማለት ይመክራል ። የዘመን ካርታ በጸሎተኛው እጅ ላይ ተቀምጧል ።

እስራኤል የገጠማት ፈተና አንዱ አገዛዝ ሲያልፍ ሌላኛው ጨምሮ የሚመጣ ነበር ። ነጋ ሲባል ወዲያው የሚጨልም ነበር ። የተፈጥሮ ሥርዓቱ እስኪዛባ ድረስ ከጨለማ በኋላ ጨለማ ይመጣ ነበር  ። ይህን ያስተዋለው ግን ያ በኛ ነበር ። አገር ሰንሰለታማ በሆነ ችግር ፣ መቆሚያ በሌለው ጅረት ውስጥ ስታልፍ መከረኛው ሕዝብ ይደነዝዛል ፣ የእግዚአብሔር ሰዎች ግን ጉዳዩን ያውቁታል ።

 

በአገራችንም ሌሊቱ የረዘመበት ወገን ብዙ ነው ። የሚጠይቀው የእግዚአብሔር ሰው ግን ያጣ ይመስላል ። ከሌሊቱ በኋላ ብርሃንን መስማት ሲናፍቅ ሌላ ሌሊት ይመጣል ፣ ብልጭ ብሎ የሚጨልም ነገር ይታያል ። የተጀመረ ነገር አይለቅላችሁ ተብሎ የተረገምን እስኪመስል ብርሃናችንን ጠብቀን መቆም ቸግሮናል ። ወጣ ወጣ ያሉ ቶሎ ይቀጫሉ ። ራእይ የሰነቁ መቃብር ይወርዳሉ ። የሚበጅ ነገር ያረገዙ ጽንሱም እነርሱም ይሞታሉ ። እኛም አውቀነው የምንጨፍረው ሲጀመር ነው ። የጨፈርንባቸው ጅማሬዎች ፍጻሜ አጥተው መሠረት ብቻ ሁነው ይታያሉ ። መከራችን ያለቀ እየመሰለን ብልጭ ባሉልን ቀኖች ደስ ስንሰኝ በሌላ በአዲስ ገራፊ እንሸማቀቃለን  ። ሌሊቱ ምን ያህል ነው ብለን ለመጠየቅም የእግዚአብሔር ሰዎችን ንቀናል ፣ አሊያም የእግዚአብሔር ሰዎችን መለየት አቅቶናል ።

 

የባቢሎንን ቅኝ ያመጣው ሳምራውያን የሆኑት ወገኖቻቸው በአሦራውያን እጅ መሰቃየታቸውን አይተው መማር ባለመቻላቸው ነው ። እኛም በዙሪያችን ያሉ አገሮች “ውድቀት ማለት ምን ማለት መሆኑን” ፣ አገር አልባ መሆን ማለት እንዴት ያለ ውርደት መሆኑን እየነገሩን ነው ። ብልጭ የሚሉ ብርሃኖች ሙሉ ቀን ወደሚሆን ብርሃን እንዲያድጉ ፣ ከሌሊት በኋላ ሌሊት እንዳይመጣ ፣ ቀን እንዲበሰር የሚያግዝ ስለ አገርና ስለ ወገን ብርቱ ጸሎት ማቅረብ ነው ።

 

አዎ ይነጋል ደግሞ ይመሻል ።

 

አቤቱ ለእኛ ያደረከውን መልካም ነገር አጽናው ።

 

ዲያቆን አሸናፊ መኮንን

ሐምሌ 29 ቀን 2012 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ

አዳዲስ መጻሕፍት

ትርጉሙ:- ቀይ ዕንቈ

ለምድራችንና ለአገልግሎታችን በረከት የሆነ መጽሐፍ
የመጀመሪያ እትም ጥቅምት 2016 ዓ.ም

1ኛ ጢሞቴዎስ ትርጓሜ – ክፍል አንድ

የመጀመሪያ እትም ሐምሌ 2013 ዓ.ም

ምክር አዘል መጽሐፍ

የመጀመሪያ እትም