እንኳን ለበዓለ ብሥራት አደረሳችሁ !
ዛሬ መላእክት ታላቅ የሆነ ምስጋና በደስታና በሐሴት ይዘምራሉ ። የክርስቶስ የመምጣቱ ብርሃንም በአማኞች ላይ በድምቀት ይበራል ። ዛሬ ለኛ የደስታችን ምንጭ ቀን ነው ። የጽድቅ ፀሐይ የሆነው ክርስቶስ በመካከላችን ብሩህ በሆነ ብርሃን በርቷል ፤ የአማኞችንም ልቡና አብርቷል ። ዛሬ አዳም አዲስ የሆነበት በመላእክት ዝማሬ መንገዱን ወደ ገነት ያቀናበት ቀን ነው የመንፈስ ቅዱስ መምጣት ለሰው ታውቋልና ዛሬ ዓለም በመላው በደስታ ተሞልቷል ። ዛሬ የእግዚአብሔር ጸጋና የማይታየው (አምላክ) ተስፋ ከመታሰብ በላይ በሆነው ተአምር ፈሷል ። ለዘመናት ተሰውሮ የነበረውን ምሥጢርም ለእኛ ግልጥና የሚረዳ አድርጎታል ። ዛሬ ፈጽሞ የማይጠፋው የጸጋ ጉንጉን ተሸምኗል ። ዛሬ እግዚአብሔር በእርሱ በዓል ሐሴት የሚያደርጉትን እርሱን በንቃት ማድመጥ ደስ የሚላቸውን ሰዎች ቅዱስ የሆነውን ራስ በዘውድ (ለማስጌጥ) ፈቅዷል ። የማይለወጠውንም እምነት የሚወዱትን እንደ ምርጦቹና እንደ ወራሾቹ ይጋብዛል ፣ ይጠራል ። ሰማያዊው መንግሥትም ረቂቅ የሆኑ ሰማያዊ መዘምራን የሚያገለግሉትን መለኮታዊ አገልግሎት ለመምሰል የሚወዱትን ለመጥራት ይፈጥናል ፤ ዛሬ “ሰማያት ደስ ይበላቸው ፥ ምድርም ሐሤትን ታድርግ ፤ ባሕርና ሞላዋ ይናወጡ ፤ በረሃ በእርስዋም ያሉ ሁሉ ሐሤትን ያድርጉ ፤ የዱር ዛፎች ሁሉ በዚያን ጊዜ በእግዚአብሔር ፊት ደስ ይላቸዋል ፤ ይመጣልና” (መዝ 95(96)፥11-13) ያለው የዳዊት ቃል ተፈጽሟል ። ዳዊት “ዛፍ” የሚል ቃል ጠቅሷል በተመሳሳይ መልኩ የጌታ መንገድ ጠራጊም እነርሱን እንደ ዛፍ ይናገራል “እንግዲህ ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አድርጉ” (ማቴ 3፥8) ወይም ደግሞ ለጌታ የሚገባ (ፍሬ) አድርጉ (ማለት ነው) ። ነገር ግን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእርሱ ለሚያምኑት ሁሉ ዘላለማዊ የሆነ ደስታን ቃል ገብቷል ። እንዲህ ብሏልና፡- “አያችኋለሁ ልባችሁም ደስ ይለዋል ፥ ደስታችሁንም የሚወስድባችሁ የለም ።” (ዮሐ. 16፥22)
ዛሬ በፈቃዳቸው ተስፋቸውን እንደ ማኅተም በክርስቶስ ላይ (ያተሙ) የክርስቲያኖች ዝነኛና ገናና የሆነው በቃልም የማይገለጠው ምሥጢር በግልጥ ታውጆልናል ። ዛሬ በእግዚአብሔር ፊት የሚቆመው ገብርኤል (ሉቃ 1፥19) “ደስ ይበልሽ፥ ጸጋ የሞላብሽ ሆይ” (ሉቃ 1፥28) የሚለውን ደስ የሚያሰኘውን ብሥራት ይዞ ወደ ንጽሕት ድንግል መጣ ። እርሷም በልቧ ይህ እንዴት ያለ ሰላምታ ነው ብላ አሰበች ። መልአኩም በፍጥነት እንዲህ አለ፡- “ከእግዚአብሔር ዘንድ ጸጋን አግኝተሻልና ማርያም ሆይ አትፍሪ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው።” “ስለዚህ ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ ስሙንም ኢየሱስ ትይዋለሽ ። እርሱም ታላቅ ይሆናል የልዑል ልጅም ይባላል ። ጌታ እግዚአብሔርም የአባቱን የዳዊት ዙፋን ይሰጠዋል በያዕቆብ ቤትም ለዘላለም ይነግሣል ። ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም ። ማርያምም መልአኩን መልሳ እንዲህ አለችው “ወንድ አላውቅምና ይህ እንዴት ይሆንልኛል?” [1] ድንግል እንደሆንሁ እቀጥላለሁን ? የድንግልናን ክብር አላጣምን ? በእነዚህ ነገሮች ግራ እየተጋባች ሳለ ወዲያውኑ መልአኩ መልእክቱን ጠቅለል አድርጎ በአጭሩ አቀረበላት ንጽሕት የሆነችውን ድንግልም እንዲህ አላት፡- “መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፥ የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል ስለዚህ ደግሞ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል” (ሉቃ 1፥35)። በትሕትና ፣ ጸጋ ከትውልዶች ሁሉ ንጽሕት ማርያምን ብቻ መረጣት ። እርሷ በሁሉም ነገሮች ውስጥ በእውነት ብልህና አዋቂ እንደሆነች አስመስክራለች። በትውልዶች ሁሉ እንደ እርሷ ያለ ሴት አልተወለደም ። እንደ ጥንቷ ድንግል ሔዋን አይደለችም ። እርሷ (ሔዋን) ግድ የለሽ በሆነ ልቡና በገነት ብቻዋን በዓል እያከበረች የክፋት ሁሉ ፈጣሪ የሆነውን እባብ (ዲያብሎስ) አሳብ ያለማስተዋል ሰማች ። በዚህም በልቡናዋ አሳብም ሳተች ። ያ አታላይ (ዲያብሎስ) ሞት ቀላቅሎ መርዙን ተፋ ፤ ወደ ዓለምም አስገባው በዚህም ለቅዱሳኑ ሁሉ መከራ መጣ ። ነገር ግን የመጀመሪያዋ እናት ውድቀት በድንግል ማርያም ብቻ መፍትሔ አገኘ ።
ሆኖም ቅድስት አስቀድማ የላከው ማን እንደሆነ ፣ ስጦታው ምን እንደሆነ መልእክቱን ያመጣው ማን እንደሆነ ሳታውቅ ስጦታውን ለመቀበል ብቁ አልነበረችም ። ቅድስቷ ግራ በመጋባት ከራሷ ጋር ይህን ካወጣች ካወረደች በኋላ መልአኩን እንዲህ አለችው “እንዲህ ባለ መልክ ለእኛ በረከት ከወዴት ነው ያመጣህልን ? ከምን መዝገብ የዓለም ሉል ለእኛ ተላከ ? ስጦታው በእኛ ላይ ያለውን ዓላማ ያገኘው መቼ ነው ? ከሰማይ መጣህ ሆኖም ግን በምድር ትራመዳለህ ! ሰው ትመስላለህ ፣ ሆኖም ግን በሚያንጸባርቅ ብርሃን ደምቀሃል።” ቅድስት እነዚህን ነገሮች አሰበች ፤ መልአኩም እንዲህ ባለ አመክንዮ የተፈጠረውን ችግር እንዲህ ብሎ ፈታው “መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፥ የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል ስለዚህ ደግሞ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል ። ማርያም ሆይ አትፍሪ የመጣሁት በፍርሃት ልሞላሽ ሳይሆን ፍርሃትን ለማራቅ እንጂ ። ከእግዚአብሔር ዘንድ ጸጋን አግኝተሻልና ማርያም ሆይ አትፍሪ ። ጸጋ በተፈጥሮ ሕግ አይሠራምና ጸጋን በተፈጥሮ ሕግ አትለኪ ። ድንግል ሆይ (የብሉይ ኪዳን) አባቶችና ነቢያት ያላወቁትን አውቀሻል ። ድንግል ሆይ እስካሁን ድረስ ከመላእክት ተሰውሮ የነበረውን ነገር አውቀሻል ። ንጽሕት ሆይ (በመንፈስ ቅዱስ) የተነቃቁ ዘማሪዎች እንኳን ይሰሙት ዘንድ ያልተገባቸውን ሰምተሻል ። ሙሴ ፣ ዳዊት ፣ ኢሳይያስ ፣ ዳንኤልና ሁሉም ነቢያት ስለ እርሱ ተነበዩ ። እንዴት እንደሚወለድ ግን አላወቁም ።
ኦ! ንጽሕት ድንግል ሆኖም ግን አንቺ ብቻ እነዚህ ሁሉ ያላወቁትን (ምሥጢር) ተቀበልሽ ፤ የነዚህንም መሠረት ተማርሽ ። መንፈስ ቅዱስ ባለበት ሁሉም ነገሮች ተስማምተው ይኖራሉ ። አምላካዊ ጸጋ ባለበት ሁሉም ነገር ከእግዚአብሔር ጋር ይቻላል ። መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፥ የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል ስለዚህ ደግሞ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል።”
እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆነ ከአብ ጋር በባሕርይ የሚተካከል ከእርሱም ጋር በቅድምና የነበረ እግዚአብሔር ነው ። በእርሱም አብ ሁሉንም መገለጦች በምልአት አካቷል ፤ እርሱ የአብ መልክ ነው ፣ በመንጸባረቁም የአብ ክብር ይበራል ። ከዘላለማዊው ምንጭ እንደሚገኝ ልክ እንደዚሁ ሁል ጊዜ ከሚመነጨውና ከሚፈሰው ዘላለማዊና ሕያው ከሆነው የዓለም ብርሃን፣ ዘላለማዊና እውነት የሆነው ክርስቶስ አምላካችን ይወለዳል ። ነቢያት የሰበኩለት ይህ ነው “የወንዝ ፈሳሾች የእግዚአብሔርን ከተማ ደስ ያሰኛሉ” (መዝ 45(46)፥4)። (ደስ የሚያሰኘውም) አንድን ከተማ ብቻ አይደለም ነገር ግን ሁሉንም ከተሞች እንጂ ። አንድን ከተማ ደስ እንደሚያሰኘው መላውን ዓለምም እንዲሁ ያደርጋል ። በእርሷ ዘንድ የጸጋ ሙሉ መዝገብ ነበርና በሚገባ ሁኔታ መልአኩ በመጀመሪያ ቅድስት ድንግል ማርያምን እንዲህ አላት ፡- “ደስ ይበልሽ ፥ ጸጋ የሞላብሽ ሆይ ፥ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው” (ሉቃ 1፥29) ። ከትውልድ ሁሉ እርሷ ብቻ በሥጋም በመንፈስም ንጽሕት ድንግል ሁኖ ኖራለች ። ሁሉንም በቃሉ የሚይዘውን እርሷ ብቻ ያዘቸው ። የሚያስደንቀው የዚህች ቅድስት ውበት ብቻ አይደለም ነገር ግን የነፍሷ ውበትም እንጂ ። ስለዚህ መልአኩ አስቀድሞ ሰላምታ ሰጣት “ደስ ይበልሽ፥ ጸጋ የሞላብሽ ሆይ፥ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው። (ሉቃ 1፥29) በምድርም ባል የለሽም።” የቅድስና ጌታ ፣ የንጽሕና አባት ፣ የሕያውነት ባለቤት ፣ ነፃነት ሰጪ ፣ የድኅነት ባለቤት ፣ የእውነተኛ ሰላም መጋቢና ሰጪ ከድንግል መሬት ሰውን የፈጠረው ከአዳምም ጎን ሔዋንን ያስገኘው እርሱ ራሱ ከአንቺ ጋር ነው። ይህ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው ። በሌላ መልኩ (እርሱ) ከአንቺ ተገኘ።
ስለዚህ የተወደዳችሁ ወንድሞቼና እህቶቼ መልአካዊውን ፍጽምና እንውሰድ፤ ባለን አቅም ሁሉ የሚገባውን ምስጋና “ደስ ይበልሽ፥ ጸጋ የሞላብሽ ሆይ፥ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው። (ሉቃ 1፥29) እያልን እንስጥ ። የእግዚአብሔር ጸጋ እርሱ በሚያውቀው አንቺ ላይ ለማደር መርጦሻልና በእውነት ደስ ይልሽ ዘንድ ይገባል ። የክብር ጌታ ባሪያው ላይ አደረ ። “ውበትህ ከሰው ልጆች ይልቅ ያምራል” (መዝ 44(45)፥2) (የተባለለት እርሱ) ውብ ከሆነችው ድንግል ጋር ፣ ሁሉንም ነገር የሚቀድሰው እርሱ ንጽሕት የሆነችው ላይ (አደረ)። እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር ነው ። የመለኮት ሙላት በእርሱ ያለው ፍጹም ሰው የሆነውም ከአንቺ ጋር ነው ። ጸጋን የተሞላሽ ሆይ ደስ ይበልሽ ! የሚያምኑበትን ሁሉ ብርሃን የሚያደርግ የብርሃን ምንጭ (ከአንቺ ጋር ነው።) ጸጋን የተሞላሽ ሆይ ደስ ይበልሽ ! የጽድቅ ፀሐይ ፣ ንጹሕ የሆነው የሕይወት አበባ መውጫ ! የሆነው መድኅን ጥዑም መዓዛ ጸጋን የተሞላሽ ሆይ ደስ ይበልሽ ! ሁል ጊዜ የሚያብበው ወይን ፣ የሚያከብሩሽን ሰዎች ነፍስ ደስ የምታሰኚ ጸጋን የተሞላሽ ሆይ ደስ ይበልሽ ! የማይነጥፈውን ፍሬ ያፈራሽልን መልካሟ ምድር በእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስን አግኝተሻልና ደስ ይበልሽ !
ይቀጥላል
ታሕሣሥ 22 ቀን 2011 ዓ.ም.
[1] ሉቃ 1፥29