“ኢየሱስም መልሶ፦ ከዚህ ውኃ የሚጠጣ ሁሉ እንደ ገና ይጠማል፤ እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ሁሉ ግን ለዘላለም አይጠማም፥ እኔ የምሰጠው ውኃ በእርሱ ውስጥ ለዘላለም ሕይወት የሚፈልቅ የውኃ ምንጭ ይሆናል እንጂ አላት” /ዮሐ. 4፥13-14/ ።
ሳምራዊቷ ሴት ለጌታችን መቅጃ የለህም የሚልና ከአባታችን ከያዕቆብ ትበልጣለህን ? የሚል ሁለት ጉዳዮችን አነሣች ። ጌታችን ግን የሰጣት ምላሽ የሕይወት ውኃን የሚያብራራ ነበር ። እርሱ ንግግሩ ፍሰት ስላለው በየስላቹ አይቀርም ። ይናገራል ፣ የተናገረውን ይተረጕማል ፣ ከሕይወት ጋር ያዛምዳል ፣ በረከትን ይሰጣል ። ባዶ እጁን መሆኑን አይታ መቅጃ የለህም በማለት ቊሳዊ ነገር እንደሌለው ተናገረች ። ዕድሜውንም በማየት ከአባታችን ከያዕቆብ ትበልጣለህን ? በማለት ወጣትነቱን ገመገመች ። እርሱ ግን መቅጃ የለውም ፤ ነገር ግን ዓለሙን በእጁ የያዘ ነው ። እርሱ በሥጋ አሁን ቢገለጥም ከያዕቆብ በፊት የነበረ ነው ። እንደውም ያዕቆብን በያቦቅ ወንዝ ያገኘውና ያረጋጋው ነው ። ጌታችን በዚህ በያዕቆብ ጕድጓድ አጠገብ ላይ ሲገኝ ይህን ጕድጓድ የቆፈረውን ያንን ያዕቆብን አስታውሷል ።
ያዕቆብ ብዙ ጊዜ በአታላይነት ይጠቀሳል ። ሲወለድ የወንድሙን ተረከዝ በመያዙ ፣ በምስር ወጥም የወንድሙን በረከት በመውሰዱ ፣ አባቱንም ዔሳው ነኝ በማለት ምርቃትን አታልሎ በመውሰዱ ይታወቃል ። ያዕቆብ ወንድሙን ፈርቶ ወደ አጎቱ ወደ ላባ ወደ ሶርያ ምድር ተሰደደ ። በዚያም አጎቱ ሁለት ጊዜ አታለለው ። ያዕቆብም ለሃያ ዓመታት ያህል በአጎቱ ቤት በመታለል ኖረ ። አሁን ግን ብዙ ልጆች ተወልደውለት ፣ ሀብቱ በዝቶለት ወደ ትውልድ አገሩ ተመለሰ ። ያዕቆብ ምግብና ልብስ ቢኖረኝ በማለት ተስሎ ነበር ። እግዚአብሔር ግን ከዕለት ፍላጎት አልፎ ብዙ ሀብትን ሰጠው። ያዕቆብ 12 ልጆች ተወልደውለታል ፣ ሁለት ሚስቶች ራሔልና ልያ አብረውት አሉ ። ከብቶቹና ንብረቱም ሜዳ የሚሞሉ ነበሩ ። ነገር ግን የኖረለት ነገርና ያገኘው እርካታ አነሰበት ። ወንድሙን ያጣበት ፣ ከአባቱ ቤት የኮበለለበት ፣ ከቤት ወጥቶ የማያውቅ ልጅ ስደተኛ የሆነበት ያ ሁሉ ልፋት ለዚህ ነው ወይ ? በሚል ጥያቄ ባዶ ሆነበት ። ውስጡ ዛለ ፣ የሞተ መንፈሱን ሥጋው መሸከም አቃታት ። ልጆቹንና ሚስቶቹን እንዲሁም ከብቶቹን አሻግሮ እርሱ ግን በያቦቅ ወንዝ ዳርቻ ብቻውን ቀረ ። ሌሊቱን በሙሉ ለመተከዝና ብቻውን ለማልቀስ ፈለገ ። ወንድሙ ዔሳው ስጋቱ ነው። አሁን ሮጦ ለማምለጥ የማይችል በልጆች የታጠረ ነው ። እግዚአብሔር ግን በዚያች የትካዜ ሌሊት ያዕቆብን አገኘው ። ያዕቆብም እግዚአብሔርን መልቀቅ ስላልቻለ ሌሊቱን በሙሉ ሲታገል አደረ ። ልቀቀኝ ቢለውም ያዕቆብ ግን ካልባረከኝ አልቅህም አለው ። ያዕቆብ ሚስቶች ፣ ልጆች ፣ ከብቶች አሉት ። እነዚህ በረከቶች አይደሉም ወይ ? ብንል ያዕቆብ እነዚህ ሁሉ ዕረፍት አልሰጡትም ። በረከት ሰማያዊና መንፈሳዊ መሆኑን ተረድቷል። እነዚህን ነገሮች እስኪያገኝ ያዕቆብ የመጨረሻ ልመናው ይህ ነበር ። ካገኘ በኋላ ግን ሌላ በረከት እንዳለ ገባው ። ስለዚህ ካልባረከኝ አልለቅህም አለ ። እሞትብሃለሁ ፣ ከዚህ በላይ መቆየት የሚችል አቅም የለኝም ማለቱ ነው ። እግዚአብሔርም በዚያች ሌሊት ስሙን እስራኤል ብሎ ለወጠለት ። ያዕቆብ መንፈሳዊ ነገርን በጥልቀት ያስተዋለበት ሌሊት ነውና ስሙ ተለወጠ ።
ያዕቆብም ተባረከ ። ነገር ግን ከትግሉ የተነሣ ያዕቆብ ያነክስ ነበር ። ነገር ግን ፡- “እግዚአብሔርን ፊት ለፊት አየሁት ሰውነቴም ድና ቀረች” አለ /ዘፍ. 32፥30/ ። እያነከሱ ድኖ መቅረት አለ ወይ ? ብንል ያዕቆብ መንፈሱ ዕረፍት ሲያገኝ የእግሩን ማንከስ ረሳው ። የረካ መንፈስ የሚያነክስ ሥጋን መሸከም ይችላል ።
ጌታችን በዚህ በያዕቆብ ጕድጓድ አጠገብ ስለ እርካታ መናገሩ በእውነት ድንቅ ነው ። ያዕቆብ በዚያ ሌሊት የታገለው ከእግዚአብሔር ወልድ ጋር ነው። በነቢዩ በሆሴዕ፡- “በማኅፀን ውስጥ ወንድሙን በተረከዙ ያዘው፥ በጕልማስነቱም ጊዜ ከአምላክ ጋር ታገለከመልአኩም ጋር ታግሎ አሸነፈ አልቅሶም ለመነው። በቤቴልም አገኘው፥ በዚያም ከእኛ ጋር ተነጋገረ።እርሱም የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር ነው የመታሰቢያው ስም እግዚአብሔር ነው”ይላል /ሆሴዕ.12፥4-6።
ሴቲቱ አላወቀችምና አንተ ከአባታችን ከያዕቆብ ትበልጣለህን ? አለችው ። ያዕቆብን ያረካው ጌታ ሊያረካት መጥቶ ነበር ። እርስዋም አምስት ባሎች ዕረፍት ሊሰጧት አልቻሉም ። ሙከራ ያደከማት ሴተ ናት። እቤት ያስቀመጠችውንም ባል ያልሸኘችው ስድስተኛውም ያው ነው ብላ ይመስላል ። አምስተኛውን ባል ከመባረር ያዳነው የእርስዋ መሰልቸትና ሁሉም ነገር ድግግሞሽ ሆኖ ስለታያት ነው ። ከውኃ ጥያቄ በላይ የነፍስ ጥያቄ አለባት ። “ኢየሱስም መልሶ፦ ከዚህ ውኃ የሚጠጣ ሁሉ እንደ ገና ይጠማል፤ እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ሁሉ ግን ለዘላለም አይጠማም፥ እኔ የምሰጠው ውኃ በእርሱ ውስጥ ለዘላለም ሕይወት የሚፈልቅ የውኃ ምንጭ ይሆናል እንጂ አላት” /ዮሐ. 4፥13-14/ ።
ይህ ውኃ ሲል የእርስዋ ሙከራና እርካታን የፈለገችበት መንገድ ነው ። ያ መንገድ የሰው መንገድ ነው ። ይህን ባገኝ እረካለሁ የሚለው የሰው ምኞት ነው ። ሰው የቆፈረው ጕድጓድ መልሶ ያስጠማል ። ጥያቄው መልስ ካገኘ በኋላ መልሱ ጥያቄ ይሆናል ። የሰው ዓለም ምኞት እስኪሆን መቅበዝበዝ ፣ ከሆነ በኋላ እንደገና መመኘት የሞላበት ፣ ፍለጋ የማያልቅበት ፣ ሕልምና ፍችው የተሰወረበት ነው ። ዛሬም በኑሮው ከተደሰተ ያዘነ ፣ በእሴቱ ካመሰገነ የተማረረ ይበዛል ። የሰው ልብ ሁልጊዜ መንገደኛ ነው ። ወደቡን አያውቀውም ሁልጊዜ ቀዛፊ ነው ። እፎይ የሚያሰኘውን ሕይወት የሚሰጠው ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው ። ያ የሚያረካው ምንጭ ነው ። የሚፈለግ ሳይሆን በሆድ ውስጥ የሚፈልቅ ነው ። ከውጭ ወደ ውስጥ የሚገባ ሳይሆን ከውስጥ ወደ ውጭ የሚፈስስ ነው ።
ጌታችን ፡- “ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው” ብሏል /የሐዋ. 20፥35/። በገንዘብ ብቻ ሳይሆን በማንኛውም የሕይወት ገጽታ ከሚቀበል የሚሰጥ ደስተኛ ነው ። ፍቅርን ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ደስተኛ ነው ። ምንጩ ውስጣችን ሲተከል ወደ ውጭ መፍሰስ ብቻ ነው ። በመፍሰስ ውስጥ መርካትና ማርካት ፣ መጥራትና መንጻት አለ ። ሙከራ ወይም ድርጊት በሌለበት መሻሻል የለም ። የማይሳሳቱ የማይሠሩ ብቻ ናቸው ። መደናቀፋችን መራመዳችንን ይሳያል ። ከመቀመጫቸው የማይነሡ ሰነፎች አይደናቀፉም ። የሰው ልጅ እውነተኛው እርካታ የሚጀምረው ዘላለማዊ ጥያቄው ሲመለስ ብቻ ነው ። የነፍስ በረከት ለሥጋ ይተርፋል ፣ የሥጋ በረከት ግን ለነፍስ አይተርፍም በማለት የተነገረው ለዚህ ነው ።
ያዕቆብ ምድራዊውን ውኃ ለማግኘት ብዙ ደከመ ። ያ ምድራዊ ውኃ ግን መልሶ ያስጠማል ። ትግሉ የጀመረው ፣ የወንድምን ተረከዝ በመያዝ ገና ከማኅፀን ደጃፍ ላይ ነው ። ያዕቆብ ጭምትና ከቤት የማይወጣ ፈሪ በመሆኑ የኑሮ ስጋት ነበረበት ። ይህ የኑሮ ስጋቱ ለወንድሙ ረሀብ እንኳ እንዳይራራ አደረገው ። የፈለገውን ከፈለገው በላይ አገኘ ። በምኞት ትልቅ ሆኖበት የነበረው ነገር አሁን ሲጨብጠው ሊያረካው አልቻለም ። ጠማኝ የሚለው ጥያቄው አልረካሁም በሚል ከባድ ጥያቄ ተለወጠ ። ጠማኝ ተዳሳሽ ፍላጎት ነው ። ጠማኝ ለሚል ውኃ መስጠት ይቻላል ። ውኃ የሰጡን አልረካሁም ብንላቸው ውኃ ይጨምራሉ እንጂ እርካታ የሚባለውን መንፈሳዊ ነገር ሊሰጡን አይችሉም ። እርካታ መንፈሳዊ ነገር ነው ። ውኃ እንኳ ጠጥተን ከረካን ብዙ ጊዜያችን ነው ። በልጅነታችን ጠጥተን ስንረካ ይታወሰናል ። ዛሬም የያዕቆብ ጉዞ በብዙ የሰው ልጅ ሕይወት ውስጥ ይደገማል ። ገና በጥዋቱ ከወንድም ከእህት ጋር መታገል ይጀምራል ። በአሻንጉሊት የተጀመረው መነጣጠቅ ፣ እኔን እቀፉኝ በሚል የተጀመረው ቅንዓት እያደገ ይመጣል ። የእኔ በረከት ያለው በእግዚአብሔር እጅ ነው ከማለት ወንድሜ ይዞብኛል ወደሚል አዙሪት ይቀየራል ። ወንድምን ለማጥመድና ለመጥለፍ ከምስር ወጥ እስከ ጸሎት ማሰናከያውን ያሳድጋል ።
ፍቅርን የተራቆትንበት ፣ በወንድማችን ሩጫ ላይ አፈር የደፋንበት ፣ በሥጋዊም በመንፈሳዊም መንገድ ወንድማችንን ለመጣል ያሴርንበት ነገር ሁሉንም ጨብጠን ስናየው ለዚህ ነበር ወይ ? ብለን ራሳችንን እንድንታዘበው ያደርገናል ። ለዚህች ዕድሜ ስንቱን ሆንን ። እግዚአብሔር ያለው ላይቀር ስንቴ ከእምነት ጎደልን ። ጤናችንን አጣን ፣ ጤናም አሳጣን ። በልባችን ዶለትን ፣ በአደባባይ ተካሰስን ። ያገኘነው የተዘጋጀልንን እንጂ የተጠበብንበትን አይደለም ። ያሳለፍነውን ዘመን ለመገምገም ጊዜ ካገኘን ይህችን ለማግኘት ወንድምን ፣ ጤናን ፣ ሃይማኖትን ማጣት ተገቢ እንዳልነበር እንረዳለን ። ዛሬም ጠያቂ ነን ። ቤት ተሠርቷል ፣ ትዳር ተበጅቷል ፣ ልጆች ተወልደዋል ፣ ሀብት ተይዟል ። አሁንም ልባችን መንገደኛ ፣ ውስጣችን ፍለጋ ላይ ነው ። ምክንያቱም መርካት በክርስቶስ ብቻ ነው ። ታዲያ ይህን እርካታ እንዴት ማግኘት ይቻላል ?