መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » በጸጋ መትጋት

የትምህርቱ ርዕስ | በጸጋ መትጋት

 ክፍል 3

በጸጋ መትጋት

“በተጠራችሁበት መጠራታችሁ እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እለምናችኋለሁ፤” ኤፌ. 4፡1 ።

ንጉሣዊ ጥሪ ሲደረግ የመጀመሪያ መቅረት አይቻልም ። መቅረት ቢኖር እንኳ ማሳወቅ ግድ ይላል ። ከዚህ ጋር አለባበስን በተመለከተ የቤተ መንግሥትን ክብር የጠበቀ መሆን አለበት ። በሰማያዊ ግብዣ ላይም እነዚህ ሁለት መርሖች አሉ ። የመጀመሪው ንጉሣዊ ጥሪን መቅረት አይቻልም ። ቢቀር የቀረበት ተጠሪው ነው ። ሁለተኛ ንጉሡ አለባበስን ያያል ። የጽድቅ ልብስ አስፈላጊ ነው ። ጥሪ ብዙ ዓይነት መልእክቶች አሉት ። ደስታዬንና ኀዘኔን ተካፈሉልኝ የሚል ጥሪ አለ ። ኃላፊነትን ተወጡልኝ የሚል ጥሪ አለ ። የፍርድና የቅጣት ጥሪዎችም አሉ ። በዚህ ክፍል ላይ ሐዋርያው ስለ ጥሪ እየተናገረ ነው ። በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የመፈጠር ጥሪ ፣ የመዳን ጥሪና የአገልግሎት ጥሪ አለ ። በሦስቱም ጥሪዎች ጠሪው እግዚአብሔር ሲሆን ተጠሪው ደግሞ የሰው ልጅ ነው ። የተፈጥሮ ጥሪ ካለመኖር ወደ መኖር የመጣንበት ነው ። የመዳን ጥሪ ከሞት ወደ ሕይወት የፈለስንበት ነው ። የአገልግሎት ጥሪ ለመዳናችን የምስጋና ዋጋ ይዘን የምንመጣበት ነው ። ሐዋርያው በዚህ ክፍል ላይ እየተናገረ ያለው ስለ አገልግሎት ጥሪ ነው ። በተፈጥሮ ጥሪ ሥጋና ነፍስን ይዘን መጥተናል ። በመዳን ጥሪ ማኅደረ ሥላሴ ሆነናል ። በአገልግሎት ጥሪ የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ ለብሰናል ። 

ጥሪን ማወቅ ወይም ጸጋን መለየት ተገቢ ነው ። አንድ ንጉሥ ይህን ኃላፊነት ውሰድልኝ ብሎ ለአምባሳደርነት ወይም ለሚኒስትርነት ይጠራል ። እግዚአብሔርም ለጠፋው ዓለም የጽድቅ መልእክተኞች እንድንሆን ጠርቶናል ። ለመገልገል ሳይሆን ሌሎችን ለማገልገል ተጠርተናል ። ጥሪን መለየት እጅግ አስፈላጊ ነው ። ጥሪን መለየት ማለት ጸጋን መለየት ማለታችን ነው ። ሁሉም ጸጋ የለንም ፣ አልቦ ጸጋም አይደለንም ። ጸጋን መለየት ያስፈልጋል ። ጸጋን መለየት ያለንን ማወቅ ነው ። ያለንን ማወቅ ለማመስገንና በሌለን ነገር ከሌሎች ለመቀበል ትሑት ያደርገናል ። ጸጋን መለየት ፈጥኖ ለመሰማራት ይረዳናል ። ጸጋን መለየት እኔም ከእግዚአብሔር የተቀበልኩት አለ ብለን እንድንነሣሣ ያደርገናል ። ብዙ የነጃጅ ክምችት ባለበት መስክ ላይ ተቀምጦ የሚተክዝ ድሀ ገበሬ ሊኖር ይችላል ። እዚያ ቦታ ሀብት እንዳለ አያውቅም ። ይህ ሰው ሀብት የለሽ ሳይሆን  ሀብቱን መለየት አልቻለም ። አዋቂዎች መጥተው በዚህ ስፍራ ሀብት አለ ሲሉት በድህነት የኖረበት ዘመን ሳይቀር ሊያሳዝነው ይችላል ። ፈጥኖ በጸጋ አለመሰማራትም ያጸጽታል ። ጸጋ ከጊዜ ጋር ብርቱ ቁርኝት አለውና ። እንደ ፈያታዊ ዘየማን አንድ ሰዓት ቀርቶን ልናምን እንችላለን ። በአንድ ሰዓት ውስጥ ግን ማገልገል ላይኖር ይችላል ።  አገልግሎት ጊዜ ፣ ስፍራ ይፈልጋል ። ጸጋን መለየት በሌሎች ጸጋ ከመዳከር ያድናል ። 

ባልተሰጠው ቦታ የሚውል የተሰጠውን ቦታ ክፍት ያደርጋል ። ከእግዚአብሔር የምንቀበለው ትንሽ ስጦታ የለምና ጸጋችንን ልንደሰትበት ይገባል ። እግዚአብሔር ይህን ጸጋ ሲሰጠን በቤተ ክርስቲያን የጎደለውን ቦታ አይቶ ፣ የእኛን ተፈጥሮአዊ አወቃቀር ተመልክቶ ፣ ዘመኑን ዋጅቶ ፣ ያለንበትን ማኅበረሰብ ከግምት ውስጥ አስገብቶ ነው ። እግዚአብሔር በእነዚህ ሁሉ ተጨባጭ ጉዳዮች ይህን ጸጋ ሲሰጠን እኛ ግን ከጸጋችን  የምንሸሸው ምኞታችንን ብቻ ተከትለን ነው ። ያማረንን ሳይሆን የሚያምርብንን መያዝ ደስ ይላል ። 

ጸጋን መለየት ያስፈልጋል ። በአንድ አገር ላይ ሁለት አምባሳደር አይላክም ። በአንድ ደብር ላይም ሁለት አለቃ አይኖርም ። ጸጋችንን መለየት ካልቻልን መደራረብ ይከሰታል ። እዚህ ሲደረብ እዚያ ጋ ባዶ ይሆናል ። እግዚአብሔር ማን ለምን እንደሚሆን ያውቃል ። ጸጋን ከመለየት ቀጥሎ በጸጋ እንደሚገባ ማገልገል ይገባል ። ጸጋ ኃላፊነት በመሆኑ አንድ ቀን እናስረክበዋለን ። ሊወሰድብንም ይችላል ። ጸጋን እንደሚገባ መጠቀም በትጋት ማገልገል ነው ። የእግዚአብሔር ሥራ ትጋት ይፈልጋል ። የእግዚአብሔርን ሥራ በቸልታ መሥራት ርግማን እንደሚያመጣ ተጽፎአል ። ሥራው ለሰው ሳይሆን ለአምላካችን ለእግዚአብሔር ነውና በትጋትና በጥራት መሠራት ይገባዋል ። እግዚአብሔር የሚያከብሩኝን አከብራለሁ ስላለ ሥራውን በጥራት መሥራት አስፈላጊ ነው ። እውቀትና ጸጋ ትጋት ከሌለው የባከነ ሀብት ነው ። ይልቁንም ጸጋ ማለት ሀብት ማለት ነው ። ሀብት ሲያስቀምጡት እየቀነሰ ይመጣል ። ሲነግዱበትና ሲያገላብጡት ግን ዋጋው እየጨመረ ይመጣል ። ጸጋም መንቀሳቀስ ይፈልጋል ። 

ጸጋ ከእግዚአብሔር በእኛ በኩል ለሰዎች የተላከ መልእክት ነውና በባለ አደራነት ስሜት ልናደርሰው ይገባል ። ሰዎቹ ይገባቸዋል አይገባቸውም የሚል ሥጋዊ ሚዛንን ጥለን እግዚአብሔር ስጡ ያለንን ምድራዊ ዋጋ ባለመፈለግ ማድረስ ነው ። ጸጋ የሰማይን ደጃፍ በሰዎች ፊት መክፈቻ ነው ። ጸጋ የዓለምን መሬት ማጣፈጫ ነው ። ጸጋ ከሰው አቅም በላይ ለሆኑ ችግሮች ተራራውን መደልደያ ነው ። ጸጋ እርስ በርስ የምንፈላለግበትና የምንከባበርበት ምሥጢር ነው ። ከዚህ ሁሉ በላይ ጸጋ የምንኮራበት ሳይሆን የምንጠየቅበት አደራ ነውና በጥንቃቄ መያዝ ይገባናል ። አንድ ሰው ሚኒስትር ከሆነ በኋላ እንደ ቀድሞ ገበያ መውጣት ፣ በጎዳና መራመድ ፣ ደስ ያሰኘውን ሁሉ መፈጸም አይችልም ። ሚኒስትርነት ጽድቅን የሚፈልግ ከሆነ ጸጋ የበለጠ ታማኝነትን ይፈልጋል ። ያ ሚኒስትር በፈቃዱና ቦታውን በሚመጥነው ኑሮ የተዋቸውን ነገሮች አያስባቸውም ። ክብር ከእነዚህ ሁሉ በላይ መሆኑ ተሰምቶት የተፈቀደለትን ነገር ሳይቀር እየተወ ይኖራል ። 

በጸጋችን እንደሚገባ እንዳንጠቀም የሚያደርጉን ነገሮች አንዱ ምቹ ሁኔታዎችን መጠበቅ ነው ። ጸጋ የማይመቹ ነገሮችን ምቹ የምናደርግበት እንጂ ምቾት ፈላጊ አይደለም ። መንገድ የሚያርስ መኪና የተስተካከለ መሬት አይፈልግም ። አስተካክሎ ለራሱና ለሌሎች ምቹ መንገዶችን ይፈጥራል ። ተቃውሞዎችን መፍራት በጸጋችን እንዳንጠቀም ያደርገናል ። ሰዎች የሚሉት አያጡምና ምን ይሉኛል ብለን በጽድቅ ነገር ማፈር አይገባንም ። እኛ ምን ማድረግ አለብን ማለት አለብን እንጂ በሰዎቹ አእምሮ ውስጥ ገብተን ምን ይሉኛል ማለት አያስፈልገንም ። አብሮ መኖር እንጂ አብሮ መሞት ክብር አይደለም ። ሰውን የሚያሰናክል እንቅፋት ነው ። እንቅፋትን በልጠነው በማየት ፣ በማንሣት ፣ በመዝለል ልናልፈው ይገባል እንጂ ፈርተነው መንገድ ልናቆም አይገባም ። ጸጋን መነገጃ ማድረግ ትልቅ እንቅፋት ነው ። ራሳችንን ጠልፈን ከምንይዝበት ነገር አንዱ ጸጋን መነገጃ ማድረግ ነው ። በጸጋችን ለመመስገን መፈለግ ነውር ነው ። ስለ አፍንጫችን ሰልካካነት ሙገሳ እንደ መቀበል ነው ። ጸጋችንን በሚመለከት ምስጋና  ለእግዚአብሔር መስጠትና ማሰጠት ይገባናል ። የአምልኮ ሌባ መሆን ማለት ስለ ጸጋችን እንድንመሰገን መፈለግ ነው ። ጸጋችንን መለየትና በጸጋችን መትጋት ግን ምስጋናን ያተርፍልናል ። አመስጋኙም እግዚአብሔር ነው ። አንተ ታማኝ ባሪያ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ ይለናል ። ጸጋን ያለ ሥነ ምግባር መያዝ ሌላው አደገኛ ነገር ነው ። ብዙ እውቀትና ችሎታ ያላቸው ሰዎች የመግባባት አቅም የላቸውም ። ጸጋ እያላቸው ግን ሥነ ምግባር የለሽ መሆን ተገቢ አይደለም ። ጸጋ ድልድይ በመሆኑ ሰውና እግዚአብሔርን ፣ ሰውና ሰውን ያገናኛል ። 

እኛም በጸጋችን እንደሚገባ መመላለስ ይገባናል ።

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ነሐሴ 10 ቀን 2013 ዓ.ም ።

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ

አዳዲስ መጻሕፍት

ትርጉሙ:- ቀይ ዕንቈ

ለምድራችንና ለአገልግሎታችን በረከት የሆነ መጽሐፍ
የመጀመሪያ እትም ጥቅምት 2016 ዓ.ም

1ኛ ጢሞቴዎስ ትርጓሜ – ክፍል አንድ

የመጀመሪያ እትም ሐምሌ 2013 ዓ.ም

ምክር አዘል መጽሐፍ

የመጀመሪያ እትም