የእግዚአብሔር ፍቅር ሁሉን የሚከልል ፣ ዘላለማዊ የሆነ ፣ ቅድመ ሁኔታዎችን ያላስቀመጠ ነው ። ክርስትናችን የተመሠረተው በእግዚአብሔር ፍቅር ላይ ነው ። እግዚአብሔር እኛን የወደደበት ፍቅር የክርስትና አዋጅ ነው ። የእግዚአብሔር ፍቅር ፍጹም በመሆኑ መሙላትና መጉደል አይታይበትም ። እግዚአብሔር እንደሚወደኝ ምንም ዓይነት ስሜት አይሰማኝም ልንል እንችላለን ። የእግዚአብሔርን ፍቅር የሚያረጋግጥልን ስሜታችን ሳይሆን ቃሉ ነው ። እገሌን ለምን ወደድካት ቢባል ሙያዋን አይቼ ፣ በጦር ሜዳ አተኳኮሷን ተመልክቼ የሚል ምክንያተኛ አለ ። ቅልጥፍናውን ፣ ቁመናውን አይቼ ወደድኩት የምትልም አትጠፋም ። የእግዚአብሔር ፍቅር ግን መስፈርት ያላስቀመጠ ፣ በራሱ መውደድ ላይ የተመሠረተ ነው ። እግዚአብሔር ዘላለማዊ ህልውና ፣ አካል ፣ ክብርና ጠባይ አለው ። ስለዚህ የእግዚአብሔር ፍቅር ከአካሉና ከህልውናው ጋር ለዘላለም የነበረ ነው ። እግዚአብሔር ፍቅርን አልተለማመደም ፣ ፍቅርን አላዳበረም ። እግዚአብሔር ራሱ ፍቅር ነው ። ያለ ፍቅር የኖረበት ዘመን የለም ። ፍቅሩ በዘላለም ውስጥ ስላለ ጊዜ ይለውጠዋል የሚል ስጋት የለብንም ። ገና ኃጢአተኞች ሳለን ፣ ገና ሙታን ሳለን ፣ ገና ጠላቶች ሳለን ወደደን ስለሚል ወደፊት ማንነታችንን ሲያውቅ ይሸሸናል የሚል ጥርጣሬ የለብንም ።
ሰዎች የጎደላቸውን የሚሞላላቸው ሰውን ወደድሁ ይላሉ ። ዝምተኛው ተናጋሪውን ፣ ሰነፉ ጎበዙን ፣ ፈሪው ደፋሩን ሊወድ ይችላል ። ይህ ግን ነገረ ፈጅ ፣ እንደራሴ ፣ ጉዳይ ገዳይ እንደ መቅጠር ነው ። እግዚአብሔር የወደደን የጎደለውን ስለምንሞላለት አይደለም ። የመላእክት ትጋትም አያሻውም ፣ እርሱ የመላእክትም ጠባቂ ነው ። ሊሸከሙት አያስፈልገውም ፣ እርሱ ሁሉን የያዘ ነው ። ይህን አገኝ ፣ በእገሌ እከብር ብሎ ማንንም አልወደደም ። የወደደን ታመን ሳለ ከሆነ ድነው ውለታ ይመልሳሉ ብሎ ይሆናል ። የወደደን ግን ሙታን ሳለን ነው ። የምንወደውን ሰው እያስታመምን ቆይተን ሲሞት እንሸሸዋለን ፣ በሙት መዝገባችን ያልናቀን ፣ ከመቃብር ሕይወት ያወጣን የእግዚአብሔር ፍቅር ነው ። ፍቅርን መግለጥ መሸነፍ ይመስለናል ። በአገራችን ጥላቻን በአፍ መግለጥ ፣ ፍቅርን በልብ መያዝ እየተለመደ ይመስላል ። በተቃራኒው ቢሆን ይሻል ነበር ። እግዚአብሔር ግን፡- “በዘላለም ፍቅር ወድጄሻለሁ ስለዚህ በቸርነት ሳብሁሽ” በማለት ለሚወዳት ነፍስ ይናገራል ። ኤር. 31 ፡ 3 ። ከሰው ወገን ፍቅርን የሰጠኝ ማንም የለም የሚል ብሶት ካለን የእግዚአብሔር ፍቅር የሚያስፈልገው ለእኛ ነውና አሁን መቀበል ይገባናል ። እግዚአብሔር በፍቅሩ ብዙ ነገሮችን ቢያደርግልንም አንድ ልጁን ለቤዛ ዓለም መስጠቱ የፍቅሩ መገለጫ ነው ። ዮሐ. 3 ፡ 16 ።
በዚህ ዓለም ላይ ብዙ ዓይነት ፍቅሮች አሉ ። አንዱም ፍቅር ከሞት አያድንም ። ወዶኛልና አዳነኝ የተባለው ግን ለእግዚአብሔር ፍቅር ነው ። የእግዚአብሔር ፍቅር ከዘላለም ሞት ያድናል ። ልዩ ልዩ ፍቅር አለ፡-
1- የአባት ፍቅር፡- የአባት ፍቅር ያገኙ ልጆች ብርታት እንደሚሰማቸው ይናገራሉ ። ይህን ፍቅር ያላገኙ ጠንካራ አይደለሁም የሚል ስሜት ይሰማቸው ይሆናል ። ከአባት ፍቅር ግን የእግዚአብሔር ፍቅር ይበልጣል ። አባት ወልዶ ሊክድ ፣ እናት ወልዳ ልትረሳ ትችላለች እግዚአብሔር ግን ታማኖ የማይከዳ ፣ ሲወዱት የማይጠላ ነው ።
2- የእናት ፍቅር፡- በዓለም ላይ የእናት ፍቅር ልዩ ነው ። እናት ግን ልጅን ከመወለዱ በፊት ከሞትም በኋላ አታውቀውም ። እግዚአብሔር ግን እናታችን ተፈጥሮዋን ሳታካፍለን በፊት ያውቀናል ። ከሞት በኋላም አብሮን ይኖራል ። የሚሞቱ አባትና እናትን የሰጠን የማይሞተው አባትና እናት እግዚአብሔር ነው ። የሥላሴን አባትና እናትነት ዘንግቶ አባት እናት የለኝም የሚል ከንቱ ሰው ነው ።
3- የሙሽሮች ፍቅር፡- ዕለታዊና ትኩስ የሆነው የሙሽሮች ፍቅር ትልቅ ነው ። ይህ ፍቅር ግን ጠባይ ሲገለጥ ይቅር ማለት እያቃተው ፣ ኑሮና ፍቅር አብሮ አይሄድም እያለ ሲዘናጋ ይስተዋላል ። እግዚአብሔር ግን ያለ ፍቅር የፈጠረው ቅንጣት ነገር ፣ የሚሠራውም ፍንጣሪ ነገር የለውም ።
4- የወዳጅ ፍቅር፡- ወዳጅ አብሮን የሚኖር ፣ አዘቅት ስንወርድ እጁን የሚዘረጋልን ፣ ሲያሙን የማያሳማን ፣ ስንሞት የተውነውን አደራ የሚወጣ ነው ። ወዳጅነት ጥልቅ ቢሆንም የእግዚአብሔር ፍቅር ግን ይበልጣል ። የልብ አውቃ የሆነው ወዳጅ ፣ ሰባት ጊዜ በቀን በድለነው ሰባት ጊዜ ማረኝ ስንለው ይቅር የሚለን ፣ ፍጹመ ምሕረት የሆነው እግዚአብሔር ነው ።
5- የዘመድ ፍቅር፡- የሰርግና የልቅሶ ስፖንሰር ፣ አብሮ የሚያላቅስና የሚንጎራደድ የዘመድ ፍቅር ነው ። የዘመድ ፍቅር ወገንነትን መሠረት ያደረገ ነው ። “ትንሽ ሥጋ ከመርፌ ትወጋ” የሚል ነው ። የዘመድ ፍቅር የራሱ የሆነ የልብ ሙላት ቢኖረውም የእግዚአብሔር ፍቅር ከዚህ በላይ ነው ። ማርጀትና መለወጥ የለበትም ።
6- የእንስሳት ፍቅር፡- እንስሳት ፍቅርን ይሰጡናል ። ስንመጣ በደስታ ይቀበሉናል ። በዚህም ምክንያት እንወዳቸዋለን ፤ አንዳንዴ የማይለወጥ ፍቅርን በመስጠት ከሰው የተሻሉ ናቸው ። የእግዚአብሔር ፍቅር ግን ከዚህም በላይ ነው ።
7- የሕዝብ ፍቅር፡- ትልቅ ዕዳ ከሆኑ ነገሮች አንዱ የሕዝብ ፍቅር ነው ። ያንን ሕዝብ ላለማስቀየም ከባድ ጥረት ይጠይቃል ። የሕዝብ ፍቅር ደስ ያሰኛል ። የአንዱ የእግዚአብሔር ፍቅር ግን ከሕዝብ ፍቅር ይበልጣል ፣ ልብን ያሞቃል ።
8- የንጉሥ ፍቅር፡- ንጉሥ ሲወደን ደስ ይላል ። እርሱን የመሰለ ሰው የለምና ለእኛ ድንቅ ነው ፣ እኛን የመሰለ ሰው ግን ብዙ ያውቃልና ለእርሱ ብቸኛ ወዳጅ አይደለንም ። የንጉሥ ፍቅር በአንገት ላይ ካራ አስሮ እንደ መቅረብ ነው ። ቶሎም እያረጀ ያስቸግራል ። ቢሆንም የንጉሥ ፍቅር ልብን ደስ ያሰኛል ። እግዚአብሔር ሲወደን ግን ሌላ ሰው እንደሌለ አድርጎ ነው ።
9- የሕፃናት ፍቅር፡- ሕፃናት ፍቅራቸው ብርቱ ነው ። የሚወዳቸውን ይወዳሉ ፣ ስጦታ ለሚሰጣቸው የተለየ ወንበር ያዘጋጃሉ ። እኛም ሕፃንን የምንወደው ቢጠላንም ስለማይጎዳን ነው ። ቢሆንም የሕፃን ፍቅር ደስ ይላል ። የእግዚአብሔር ፍቅር ግን ከሕፃን ንጹሕነት በላይ ቅዱስ ነው ።
10- የድሀ ፍቅር፡- ድሀ የሚሰጠው ስለሌለው ራሱን ይሰጠናል ። አያስነካንም ፣ ሊሞትልን ይቀድማል ። አብዛኛው በዓለም ላይ ያለው ወታደር ድሀ ነው ፣ ድሀ ታማኝ ነው ። ሬሳችንን የሚሸከም ባለጠጋው ወዳጃችን ሳይሆን ድሀው ወገናችን ነው ። ከድሀ ፍቅር በላይ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶልናል ።
የእግዚአብሔር ፍቅር ልዩ ነውና ምስጋና አቅርቡለት ።
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሰኞ ነሐሴ 3 ቀን 2013 ዓ.ም.
እውነት 12
ለልባችሁ የቀረላችሁን አሳብ እስቲ ግለጡ ። እግዚአብሔር ዘመናችሁን ይባርክ !