መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » ድንግል ማርያም

የትምህርቱ ርዕስ | ድንግል ማርያም

 

አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ፡- “ሦስት ነገሮች ያስደንቁኛል፦ አባቱ የማይቀድመው ልጅ ፤ እናቱን የፈጠረ ልጅ ፤ የፈጠራትን የወለደች እናት” ብሏል ። አባት በዘመን የሚቀድም ፣ በክብር የሚበልጥ ነው ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ከአባቱ በዘመን የማይቀዳደም ፣ በክብር የማይበላለጥ ነው ። እናት የወለደችው ልጅ በዓለም ሁሉ ሞልቷል ፣ እናቱን የፈጠረ ልጅ ግን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው ። ፈጣሪዋን ፈጣሪዬ ያለች ብዙ ሴት አለች ። ፈጣሪዋን የወለደችና ልጄ ብላ የጠራች ግን ድንግል ማርያም ብቻ ናት ። የጌታችን ሰው መሆን ተተንትኖ የማያበቃ ልዩ ምሥጢር ነው ። የምሥጢር ባለሟልም እመቤታችን ድንግል ማርያም ናት ። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሰው መሆን ታላቅ ትሕትና ፣ ለሰው ልጆች ግን ታላቅ ልዕልና ነው ። ያለ ልክ ዝቅ ዝቅ ብሎ ያለ ልክ ከፍ ከፍ አደረገን ። ክብር ያገኘንበት የሥጋዌው ድልድይ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት ።

እስራኤል ለአራት መቶ ዓመታት ቃሉን የሚያመጡ ነቢያትን አጥታ በተስፋ ማጣት ጨለማ ውስጥ ተቀምጣ ሳለ ፣ በነቢዩ በአሞጽ የተነገረው የቃሉ ረሀብ ምድርን ባስጨነቀ ዘመን ፣ አንድ የምሥራች ተሰማ ። ይህንን የምሥራች ከበደለው አዳም እስከ አሁን ያለውን ወደፊትም የሚነሣውን የሰው ልጅ ወክላ የተቀበለች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት ። በሰው በደል ምክንያት ምድርም ተረግማ ነበርና ይህን የበረከት ድምፅ ምድር ሳይቀር የምትናፍቀው ነበር ። ፍጥረተ ዓለሙን ወክላ የምሥራቹን የተቀበለች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት ። /ሉቃ. 1 ፡ 28 ።/ በእምነት የሚያመልኩትን አምላክ በዓይናቸው ለማየት ይመኙ ነበርና መላእክትን ደስ የሚያሰኘውን የክርስቶስን ሰው መሆን ቀድማ የተቀበለች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት ። /1ጴጥ. 1፡12 ።/ በሥላሴ መንግሥት የተወሰነውን ሰውን የማዳን ቍርጥ አሳብ ከሰው ልጆች ወገን መጀመሪያ የሰማችው ቅድስት ድንግል ማርያም ናት ። ከመላእክት ወገንም ቀድሞ የሰማው ቅዱስ ገብርኤል ነው  ።

ነቢያት ክርስቶስ እንደሚወለድ ትንቢት ተናገሩ ፣ ድንግል ማርያም ግን ክርስቶስ ሰው ለመሆን በማኅፀንዋ አደረ ። ሐዋርያት ከክርስቶስ ሞት በኋላ አዳኝነቱን ለመስበክ ወጡ ፣ ድንግል ማርያም ግን የዕለት ፅንስ ሁኖ ጌታ በማኅፀንዋ ባደረ ጌታዬና መድኃኒቴ ብላ ሰበከችው ። /ሉቃ. 1 ፡ 47 ።/ ሰማዕታት ሁሉ በአንገታቸው ሰይፍ በማለፉ እናከብራቸዋለን ፣ በድንግል ማርያም ግን በነፍስዋ ላይ ሰይፍ አልፏልና የሰማዕታት እናት እንላታላን ። ሉቃ. 2 ፡ 35 ። ሊቃውንት ሁሉ በመጽሐፍ የሚያውቁትን ጌታ ድንግል ማርያም ጡትዋን አጥብታዋለች ። ከድንግል የተወለደ ጌታ ክርስቶስ ብቻ ነው ፣ ከድንግል ጡት የጠባ ሕፃንም እርሱ ብቻ ነው ። እኛ አማኝ ሆነን ለምን እንቸገራለን? ብለን እናጕረመርማለን ፣ ድንግል ማርያም ግን አምላክን የወለደችው በበረት ነው ። ጌታን የያዘ ሁሉ ይገባዋል እንላለን ፣ ድንግል ማርያም ግን ጌታን ታቅፋ ወደ ግብጽ ተሰደደች ። ድንግል ማርያም በድንግልና በመውለድ ፣ ወላዲተ አምላክ በመባል ልዩ ናት ። ነቢይት ፣ ሰባኪ ፣ ሐዋርያ ፣ ዘማሪ ፣ የአርምሞ ወዳጅ ናት ። 

ከዚህ በፊትም ያልሆነ ከዚህ በኋላም የማይሆን ጸጋ በድንግል ማርያም ላይ ተከናውኗል ። ጸጋ የሞላባት በመሆንዋ ወደፊት ጸጋን አትጠብቅም ። በዚህም ብፅዕት እንላታለን ። ወላዲተ አምላክ መባል ከእርስዋ ሌላ ለማንም የማይሰጥ የማይደገም ጸጋ ነው ። ኢያሱ በገባዖን ፀሐይን ማቆሙ የማይደገም እንደሆነ ድንግል ማርያምም የማይደገም ጸጋ ተሰጥቷታል ። ለኢያሱ፡- “እግዚአብሔር ለእስራኤል ይዋጋ ነበርና እግዚአብሔር የሰውን ቃል የሰማበት እንደዚያ ያለ ቀን ከዚያም በፊት ከዚያም በኋላ አልነበረም” ተብሏል ። /ኢያሱ 10 ፡ 14 ።/ በድንግል ማርያም ግን ፀሐይ ጌታ ከሰማይ ወደ ምድር ወረደ ። ከዚህ በፊትም ከዚህ በኋላም ቢደረግልን ከመዳናችን የበለጠ ነገር አይደረግልንም ። ኢያሱ ቀኑን ለቀጣይ 48 ሰዓት አራዘመው ። ጨለማንም ለ12 ሰዓት ከለከለው ። ፀሐይ ክርስቶስ ግን ለዘላለም ጨለማን አስወገደው ። ምስኪን ነፍስ ሁሉ በእምነት ክርስቶስን ልጄ ብላ ትጠራለች ፣ ይሆንላትማል ። በሕጋዊ መንገድ ክርስቶስን ልጄ ብላ የጠራች ግን እመቤታችን ድንግል ማርያም ናት ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰማይና በምድር አንድ አባት አለው ። በሰማይና በምድርም አንድ እናት አለችው ። እርስዋም ድንግል ማርያም ናት ። 

ድንግል ማርያምን ወላዲተ አምላክ ብለን ካላመንን መዳን የለም ። በመስቀል ላይ የሞተው ክርስቶስ የሚያድነን አምላክ ከሆነ ብቻ ነው ። ስለዚህ አማኝ ሁሉ ድንግል ማርያምን የአምላክ እናት ይላታል ። ክርስቶስ ከእመቤታችን ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍስዋ ነፍስ ነሥቶ መወለዱን ማመን ግድ ይላል ። ወላዲተ አምላክ አይደለችም ብሎ የካደው ንስጥሮስ ፣ ከእርስዋ ሥጋን እንጂ ነፍስን አልነሣም ያለው አቡሊናርዮስ የተወገዙ መናፍቃን ናቸው ። በሦስቱ ዓለም አቀፍ ጉባዔያት በኒቅያ ፣ በቍስጥንጥንያ ፣ በኤፌሶን ጉባዔያት ነገረ ማርያም ተነሥቷል ። ብዙ ክርስቶሶች ቢነሡ እውነተኛው ከድንግል ማርያም የተወለደው ነው ። አማኑኤል ማለት እግዚአብሔር ከሥጋችን ሥጋ ከነፍሳችን ነፍስ ነሥቶ ከእኛ ጋር ሆነ ማለት ነው ። የነሣውም ሥጋና ነፍስ ከድንግል ማርያም ነውና እናከብራታለን ። 

ክርስቶስን አምላክ ብሎ የሚያምን የእርሱን እናት ሊንቅ ፣ መንፈስ ቅዱስ አድሮበት መንፈስ ቅዱስ የመሰከረላትን ሊጠላ አይችልም ። የእመቤታችን የድንግል ማርያም በረከት ይድረሰን !

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን 

ሐምሌ 30 ቀን 2013 ዓ.ም.

እውነት 10

ለልባችሁ የቀረላችሁን አሳብ እስቲ ግለጡ ። እግዚአብሔር ዘመናችሁን ይባርክ !

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ

አዳዲስ መጻሕፍት

ትርጉሙ:- ቀይ ዕንቈ

ለምድራችንና ለአገልግሎታችን በረከት የሆነ መጽሐፍ
የመጀመሪያ እትም ጥቅምት 2016 ዓ.ም

1ኛ ጢሞቴዎስ ትርጓሜ – ክፍል አንድ

የመጀመሪያ እትም ሐምሌ 2013 ዓ.ም

ምክር አዘል መጽሐፍ

የመጀመሪያ እትም