የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ጋኖቹን ውኃ ሙሉአቸው

“አይሁድም እንደሚያደርጉት የማንጻት ልማድ ስድስት የድንጋይ ጋኖች በዚያ ተቀምጠው ነበር፥ እያንዳንዳቸውም ሁለት ወይም ሦስት እንስራ ይይዙ ነበር። ኢየሱስም፦ ጋኖቹን ውኃ ሙሉአቸው አላቸው። እስከ አፋቸውም ሙሉአቸው አላቸው። እስከ አፋቸውም ሞሉአቸው” /ዮሐ. 2፡6-7/ ፡፡
ብሉይ ኪዳን ብዙ ነገሮችን አርክሷል ፡፡ በፍጥረት ርኩስ ያልነበረው በሕግ ግን ርኩስ ተብሏል ፡፡ ሰው አስቦ የሚናገረውና የሚያደርገው ብቻ ሳይሆን በተፈጥሮ የሚገጥመው ነገር ሁሉ ያረክሰው ነበር ፡፡ መብሎች ፣ የተፈጥሮ ግዳጆች ፣ በድኖች ፣ ፈሳሾች ፣ በሽታዎች ያረክሱ ነበር ፡፡ ኦሪት እነዚህን ሁሉ ያረከሰችው ለምንድነው? ቢባል ቀዳሽ የሆነው ክርስቶስ እንዲናፈቅ ለማድረግ ነው ፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ፡- “በደልም እንዲበዛ ሕግ ጭምር ገባ” ይላል /ሮሜ .5፡20/፡፡ እግዚአብሔርን በደልን እያበዛ እንዴት በበደል ይጠይቃል? የሚል አሳብ በውስጣችን ሊፈጠር ይችላል ፡፡ አዳም መጠበቅ የተሣነው አንድ ሕግን ነው ፡፡ አንድ ሕግን በገነት መፈጸም አቅቶት ወደቀ ፡፡ እግዚአብሔርም በሙሴ ዘመን አሥር የሕግ ዝርዝር ሰጠ፡፡ በአንድ ያልታመነ በአሥር ይታመናል ወይ ? በገነት ያልተፈጸመ በተረገመው ምድር ላይ ይፈጸማል ወይ? ብንል ሰው ሕጉን መጠበቅ ባቃተው ጊዜ ሕመሙ እየበረታ ይመጣል ፡፡ ሕመሙ ሲበረታም አዳኝ ክርስቶስን ይበልጥ እየናፈቀ ይመጣል ፡፡ ስለዚህ ሕጉ በአንድ ጊዜ የሰውን ኃጢአተኝነትና የክርስቶስን አዳኝነት ለመናገር ወደ ዓለም ገብቷል /ሮሜ . 3፡19-20/፡፡

ስለዚህ ኦሪት ብዙ ነገሮችን ስታረክስ ማንጻት የሚፈጸምባቸው መንገዶች ነበሩ ፡፡ የመጀመሪያውና ትልቁ መሥዋዕት ነው ፡፡ ሌላው ውኃ ነው ፡፡ በቃና ዘገሊላ ሰርግ ላይም ምናልባት የሚያረክሱ ነገሮች ቢገጥሙ ዝግጁ የነበሩ የድንጋይ ጋኖች ነበሩ ፡፡ እነዚህ ጋኖች ለግብዣ ውለው አያውቁም ፡፡ ዛሬ ግን መጋበዣ ሊሆኑ ነው ፡፡ በአንዳንድ የጥንት አብያተ ክርስቲያናት በር ላይ ውኃ በገበቴ ይደረጋል ፡፡ ሰዎች ሲገቡ በእጃቸው እያጠለቁ እየተቀባቡ ይገባሉ ፡፡ ይህ ከኦሪቱ የተወሰደ ልማድ ነው ፡፡ የድንጋዩን ጋኖች ስናስብ በሰርግም ላይ መርከስ ቢገጥም ተብሎ ይታሰብ እንደ ነበር መንፈሳዊ ዝግጅትም አብሮ እንደ ነበረ እንረዳለን ፡፡
እነዚህ የድንጋይ ጋኖች ገና እድምተኛው አልገባም ነበርና ውኃ መሞላት አላስፈለጋቸውም ፡፡ የሰርጉ የመጀመሪያ ቀን ስለነበርም ውኃ ለመሙላት አልታሰቡም ነበር ፡፡ በድንግል ማርያም ምልጃ ግን ውኃ እንዲሞሉ ጌታችን አዘዘ ፡፡ ምናልባት በርቀት የሚያይ ሰው ለተለመደው ተግባር እንደሆነ ይገምት ይሆናል ፡፡ ያልተለመደና የማይደገም ነገር ሊደረግበት እንደሆነ የምታውቀው እናቱ ድንግል ማርያም ነበረች ፡፡ ጋኖቹ ብዛታቸው ስድስት ነው ፡፡ እያንዳንዳቸው ከሁለት እስከ ሦስት እንስራ ይይዙ ነበር ፡፡ አንድ እንስራ ሃያ ሊትር ይይዛል ፡፡ ሦስት እንስራ ስድሳ ሊትር ይይዛል ፡፡ ስለዚህ በአንድ ጋን ውስጥ ስድሳ ሊትር ውኃ ይሞላል ማለት ነው፡፡ ስድስቱ ጋኖች 360 ሊትር ውኃ ተሞልተዋል ፡፡ አንድ ሊትር አራት ብርጭቆ ይይዛል ፡፡ ስለዚህ ጌታችን ያበረከተው 1440 ብርጭቆ የወይን ጠጅ ነው ፡፡ ይህ ለወይን ጠጅ ያውም በተአምራት ለተለወጠ በጣም በጣም ብዙ ነው ፡፡ ከዚህ የምንረዳው ፡-
1-  ጌታችን ያበረከተው ለዕለቱ የሚበቃውን ሳይሆን የሰርጉ ቀናት እስኪፈጸም ድረስ እንግዳ የሚሸኘውን ነው ፡፡ እርሱ የለመነውን ያህል ሳይሆን ከለመነው አትረፍርፎ የሚሰጥ አምላክ ነው ፡፡ የሚሰጠን ከጉድለቱ ሳይሆን ከሙላቱ ነው ፡፡ ማንም ባለጠጋ ሲሰጥ እያጎደለ ነው ፡፡ እግዚአብሔር ግን ሀብቱ ፍጹም ነውና አይጎድልበትም ፡፡ ሐዋርያው ፡- “እንግዲህ በእኛ እንደሚሠራው ኃይል መጠን ከምንለምነው ወይም ከምናስበው ሁሉ ይልቅ እጅግ አብልጦ ሊያደርግ ለሚቻለው” በማለት ያመሰግነዋል /ኤፌ. 3፡20/፡፡
2-  ነገን የሚያይ አምላክ ነው ፡፡ እንደ ነገ ሩቅ ፣ አጠራጣሪ ፣ አስጨናቂ የለም ፡፡ ሩቅ መባሏ ካልደረስንባት ዘላለም ስለሆነች ነው፤ አጠራጣሪነቷ ያለችው ከቁጥጥራችን ውጭ መሆኗ ነው ፡፡ አስጨናቂነቷ ስላልደረስንባት ስናስባት ታውከናለች ፡፡ ምክንያቱም ነገን የሚያውል ኃይል የሚመጣው ነገ ላይ ነው ፡፡ ዛሬ ግን ያለ ኃይል ስናስባት አስጨናቂ ናት ፡፡ ነገን የምንደፍረው በዘላለሙ አምላክ በክርስቶስ ነው ፡፡ እርሱ ነገን አይቶልናል ፡፡ ለእስራኤል ሕዝብ በመስፍኑ በኢያሱ በኩል የተነገረ አዋጅ አለ፡- “ነገ እግዚአብሔር በመካከላችሁ ድንቅ ነገር ያደርጋልና ተቀደሱ አለ”/ኢያ .3፡5/፡፡ ዛሬን ከተቀደስን ነገ ድንቅ ነው ፡፡ ዛሬ መቀደስ እንጂ መጨነቅ ጥቅም የለውም ፡፡
እመቤታችን ለአገልጋዮቹ ፡- “የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ”ብላቸው ነበር ፡፡ የነገረቻቸው ለምንና እንዴት የሚሉ መጠይቆች የሌሉበትን የእምነት መታዘዝ ነው ፡፡ የእምነት መታዘዝ ስለመታዘዝ እንጂ ስለ ውጤቱ አይጨነቅም ፡፡ ጆሮአቸውን እንዳነቁ ባወቀ ጊዜ ጌታ ተናገረ ፡፡ እግዚአብሔር ይናገራል ፡፡ ነቅተው ለሚሰሙት ይናገራል ፡፡ ጌታ ፡- “ጋኖቹን ውኃ ሙሉአቸው” አላቸው ፡፡ ያዘዛቸው ቀላል ትእዛዝ ነው ፡፡ ካልፈጸሙት ግን ትልቁን ውጤት ያበላሻል ፡፡ ከአገልጋዮች የሚጠበቀው ጋኖቹን ውኃ መሙላት እንጂ ውኃውን መለወጥ አይደለም ፡፡ እነርሱ የታዘዙትን ሲያደርጉ ጌታ ደግሞ ክብሩን ይገልጣል ፡፡ እነዚያ አገልጋዮች እንደ ታዘዙት ጋኖቹን እስከ አፋቸው ውኃ ሞሉአቸው ፡፡
 ዛሬ አገልጋዮች ጋኖቹን ውኃ ለመሙላት ተስፋ ቆርጠው ይገኛሉ ፡፡ ሕዝቡ አይሰማም በማለት ዱዳ ለመሆን እየወሰኑ ነው ፡፡ አትሮንሶች እየተሰበሰቡ ፣ መጻሕፍት እየታጠፉ ይመስላል ፡፡ ክፍት ቦታ ያገኙ ደፋሮች ደግሞ እየፋነኑበት ፣ የደፈረሰ ውኃ እየሞሉበት ነው ፡፡ ነገር ግን የአገልጋዮች ድርሻ መሙላት ነው ፡፡ መለወጥ የክርስቶስ ሥልጣን ነው ፡፡ ሐዋርያው ፡- እኔ ተከልሁ አጵሎስም አጠጣ ነገር ግን እግዚአብሔር ያሳድግ ነበር” ብሏል /1ቆሮ.3፡16/፡፡ አገልጋይ ሊተክል ፣ ሊያጠጣ ይችላል ፡፡ ማሳደግ ግን የእግዚአብሔር ድርሻ ነው ፡፡ ይህን ማወቅ ከብዙ ግብግብ ደግሞም ከቀቢፀ ተስፋ ያድናል ፡፡ አገልጋዮች በታማኝነት መሙላት አለባቸው ፡፡ ብዙ የተዘጋጁ ጋኖች አሉ ፡፡ የተዘጋጁት ለሌላ ዓላማ ቢሆን እንኳ ጌታ አዝዟልና መሙላት ይገባል ፡፡ እግዚአብሔር ይለውጣል ፡፡
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ