መግቢያ » ልዩ ልዩ ሁለት » የፈረሰውን እንዳንገነባ

የትምህርቱ ርዕስ | የፈረሰውን እንዳንገነባ

ዕ ነሐ፲፭/፳፻፯ ዓ/
የራስጌ ማኅተም፡- ዝ ማኅተም ዘእቴጌ ጣይቱ ብርሃን ዘኢትዮጵያ፡፡
የተላከ ከእቴጌ ጣይቱ ብርሃን ዘኢትዮጵያ፤ ይድረስ ከማህበረ ዴር ሥልጣን ወደብረ ገነት ዘኢየሩሳሌም፣ እንዴት ሰንብታችኋል፡፡ እኔ እግዚአብሔር ይመስገን ደህና ነኝ።
እናንተ ብትስማሙ እርስ በርሳችሁ ብትፋቀሩ አንድነታችሁን ብታፀኑ ይሻላል እንጂ ትግሬ የብቻ ነው፣ ሸዋ የብቻ ነው፣ ቤገምድር ጎጃምየብቻ ነው እያላችሁ ጎሣ እየለያችሁ ብትጣሉ ምን ትረባላችሁ። እኛስ በኢየሩሳሌም ነገር ይህንን ያህል መድከማችን ያነን ያህል ብር ባንክ አግብተን የዚያን ወለድና ከቤቱ የሚወጣውን ክራይ መስጠታችን እንዳትቸገሩ የሰው ፊት እንዳታዩ ያነን እየበላችሁ ለኛም የጌታችን ደም ከፈሰሰበት ላይ ዳዊት እንድትደግሙልን እንድታዝኑልን እናንተም ነታችሁ እንዲጸና ብለን ነው እንጂ ገንዘቡ ተርፎ ባገራችን በኢትዮጵያ ለምንሰጠው ሰው አጥተን አይደለም። አሁንም ስለ እግዚአብሔር ብላችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተፋቀሩ፡፡ ለኛም ዳዊት ድገሙልን እዘኑልን። ሳትቸገሩ እንዴት የድፍን አውሮፓ መሳቂያ ትሆናላችሁ። አሁንም ይኸው እማሆይ ወለተ ተክሌ መቃብሬ ከዚያው ይሁን ብላ መጥታለችና አደራችሁን ምኑም በምኑም ነገር እንዳታስቀይሟት። እንግዲህ እሷ እንዲህ አደረጉኝ ብላ የላከችብኝ እንደሆነ እናንተንም እጣላችኋለሁ እኔንም እንዳታስቀይሙኝ።
ሰኔ ፳፱ቀን ፲፱፻ ዓመት አዲስ አበባ ከተማ ተጻፈ።

በዓለማችን በዘርኝነት፣ በጎሰኝነት፣ በወገንተኝነት ቀውስ የተነሳ የተለያዩ ግጭቶችና ታላላቅ ጦርነቶችን አስተናግዳለች፡፡ ወደ 50 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ያለቀበት የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ዋና ጠብ ጫሪ የነበረው አዶልፍ ሂትለር ጀርመናውያን ልዩ ዘሮችና ዓለምን የማስተዳደር መብት ያላቸው ሕዝቦች እንደሆኑየጀርመንን ሕዝብ ሰብኮ ለጦር ያስከተተና ለዚህ መጠነ ሰፊ የሰው ልጅ እልቂት ዋነኛ ተዋናይና የመጀመሪያውን የጥፋት ክብሪት የጫረ ሰው እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ይናገራሉ፤ እንዲሁም ለአይሁዳውያን በነበረው ከመጠን ያለፈ ጥላቻ (Anti-Semitism)  ምክንያት ወደ 6 ሚሊዮን የሚሆኑ አይሁዳውያን እንዲያልቁ ምክንያት የሆነ  የሞት መልእክተኛና የጥፋት አጋፋሪ ነበር፡፡
የመንግሥት አልባዋ የጎረቤታችን የሶማሊያ የእርስ በርስ እልቂትና ፍጥጫም ዘርንና ጎሳን ምክንያት ያደረገ ነው፤ በዚሁ የሰው ልጅ ስልጣኔ ሰማይን ታኳል በሚባልበት በእኛው ዘመን ከ800,000 በላይ የሚሆኑ ቱትሲና ሁቱስ ሩዋንዳውያን እርስ በርስ ለተጨፋጨፉበት የዘር ማጥፋት እልቂት (Genocide) መነሻው ይኽው የዘረኝነት ጦስ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ የደቡብ አፍሪካውያኑ ዘግናኝ የአፓርታይድ ሥርዓትም ዘረኝነት ዋና መታወቂያው ነበር፡፡ ጥቁር አፍሪካውያንን ከእንስሳ በታች በመመደብ ‹‹ጥቁር ሕዝብ ምንም ዓይነት ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ሰብእና የሌለው በመሆኑ››ለተገዢነት፣ ለአገልጋይነት ብቻ የተፈጠረ እንስሳ በማስመስል በሰው ልጅ ክቡር ኅሊና ላይ መጥፎ የታሪክ አሻራ የተወ፣ ታሪክ በማይረሳ ሁኔታ በጥቁር ማኅደር የከተበው አሰቃቂ ሥርዓት እንደነበረ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡ ዛሬም ስለ ዓለም አቀፋዊነት (Globalization) በሚወራበትና በሚሰበክበት በዚህ ዘመን ሰዎች በቆዳቸው ቀለም፣ በሚናገሩት ቋንቋ እና በመጡበት ዘር/ጎሳ የተነሣ የተለያዩ መድሎዎች፣ የመብት ረገጣዎችንና ሲከፋም የዘር ማጥፋት ዘመቻ ሲደረግባቸው በተደጋጋሚ እየታዘብን ነው፡፡
አስገራሚውና አሳዛኙ ነገር ለቆዳው ቀለምና ለመጣበት ዘር ምንም ዓይነት አስተዋጽኦ የሌለው የሰው ልጅ ከዚህ ዘር በመምጣቴ እኮራለሁ በማለት ሌላውን ሲንቅና ሲያንቋሽሽ መታየቱ በእጅጉ የሚገረም ነው፤ ማንኛችንም ብንሆን እግዚአብሔር በወደደውና በፈቀደው የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ በአፍሪካ ምድር በኢትዮጵያ በመወለዳችን ኢትዮጵያዊ የሆነ ዜግነትና የጥቁር ዘር ልንሆን ቻልን እንጂ፣ ጥቁርነትንም ሆነ ኢትዮጵያዊነትን በእኛ ልዩ አስተዋጽኦና ጥረት ያመጣነው አይደለም፡፡ እንዲያ ባይሆን ኖሮ እውነቱን ለመነጋገር ብዙዎቻችን በአፍሪካ ወይም በኢትዮጵያ ከመፈጠር በአሜሪካ ወይም በአውሮፓ ብንፈጠር የምንመርጥ ነበር የሚሆነው፡፡
ለመሆኑስ ረ እንደው ስንቶቻችን ኢትዮጵያውያን ነን በጥቁርነታችን የምናምንና  የምንኮራው!?… ይሄ እኛ ኢትዮጵያውያንን ብዙ ሊያነጋግረን የሚችል ርዕሰ ጉዳይ እንደሆነ አስባለሁ፡፡ በዚህ ዙሪያ ያየሁትን፣ የሰማሁትንና በተለያዩ አጋጣሚዎች የታዘብኩትን በሌላ ጽሑፍ እመለስበት ይሆናል…ብዙም ሳልርቅ ወደተነሣሁበት የጽሑፌ ዋና ቁምነገር ልመለስ፡፡
በክርስትናው ዓለም ዘረኝነት፣ ወገንተኝነት፣ ጎጠኝነት እንዲሁም ከዚህና ከዚህ ብሔር ነው የተወለድኩት በማለት ሌሎችን መናቅ በክርስትናው የመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመንም የነበረ መሆኑን ከቅዱስ መጽሐፍ እናነባለን፡፡ በተለይ አይሁዳውያን ከአብርሃም ዘር ውጪ ለነበሩት ሕዝቦች የነበራቸው ንቀት ይሄ ነው የሚባል እንዳልነበረ መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ የአይሁድ ሕዝብ የታሪክ ሰነዶች ያረጋግጣሉ፡፡ በሐዋርያት ዘመን እንኳን ከአይሁድ ውጪ ከግሪክና ከእስራኤል ዙሪያ የመጡ ክርስቲያኖች የተጠሉና የተናቁ ኪዳን አልባ ሕዝቦች አድርጎ የማየቱ አባዜ ከጌታቸውና ከመምህራቸው ጋር ለሦስት ዓመት ያህል ትምህርቱንና ታአምራቱን እያዩ ለኖሩ ደቀ መዛሙርቱ እንኳ እጅግ ፈታኝ እንደነበረ በቅዱስ ጴጥሮስ የወንጌል አገልግሎት ውስጥ በግልጽ የሚታይ ነበር፡፡
ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ለሐዋርያው ለቅዱስ ጴጥሮስ በራእይ ተገልፆ እስኪገስጸውና ከአሕዛብ ወገን ከሆነው ቆርኔሌዎስ ዘንድ ከቅዱስ መልአክ በራእይ ተገልፆለት ወደ ቅዱስ ጴጥሮስ ዘንድ የመጡት መልእክተኞችን በምንም ሳይጠራጠር እንዲሄድ በመንፈስ ቅዱስ በራእይ ከተረዳ በኋላ (ሐዋ. ሥራ ፲፣ ፩ -፵፰) ከአይሁዳውያን ውጭ ለነበሩት ሕዝቦች እንዲያውም በአዲስ ኪዳን ዘመን የነበረውን የተዛባ አመለካከት ወይም በዘር ጉዳይ (በይሁዲነት) ላይ የነበረውን ያረጀና ያፈጀ ግብዛዊ እና ፈሪሳዊ የአመለካከት ጭምብል እግዚአብሔር ከልቡና ዓይኑ እስኪያወልቅለት ድረስ ራሱን ለይቶ እና አሕዛብ የነኩትን ላለመንካት፣ አሕዛብ የቀመሱትን ላለመቀመስ በግብዝነት ሲሳብ ብርሃነ ዓለም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በግልጽ እንደተቃወመው በመልእክቱ በግልጽ አስቀምጦልናል፡፡ ገላ. ፪፣ ፲፩- ፳፩፡፡
በአይሁዳውያንና በሌሎች ሕዝቦች መካከል የነበረውን ልዩነት፣ የዘር እና የእኔነት መለያዎች፣ እንዲሁም አሕዛብንና አይሁዳውያንን ለይቶ ለዘመናት የኖረው የጥል ግድግዳ በጌታችን እና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ቅዱስ ደም ድል በተነሣበት እና ከአሁን ወዲህ አይሁዳዊ፣ የግሪክ ሰው፣ ጨዋ ወይም ባሪያ ሰው የሚባል እንደሌለና ሁሉም በክርስቶስ ኢየሱስ የመስቀል ላይ ሥራ አንድ መሆኑን አስረግጦ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስበመልእክቱ በግልጽ አስቀምጦልናል፡፡
‹‹በእምነት በኩል ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁና፣ ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና፡፡ አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፣ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፣ ወንድም ሴትም የለም፣ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና፡፡›› /ገላ. ፫  ፳፮ -፳፰/፡፡
ይሁን እንጂ ይሄ በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን፣ በመድኃኒታችንና በአምላካችን የፈረሰ የመለያየት፣ የዘረኝነት፣ የወገንተኝነት የጥል ግርግዳ በእኛይቱ ቤተ ክርስቲያን ግን በተለያየ ጊዜ እያገረሸ ሰዎችን በመንፈሳዊነታቸውና በችሎታቸው ሳይሆን በመጡበት ዘር/ ጎሳና በሚናገሩበት ቋንቋ የሚዳኙበት አሳዛኝ እውነታ ትላንትና ነበረ፣ ዛሬም በእኛ ዘመን ተባብሶ መቀጠሉን እየታዘብን ነው፡፡ ከዚህም አልፎ የዘረኝነት እና የጎጠኝነት መንፈስ ደም እስከ ማፋሰስ ድረስ የደረሰበትን በርካታ አጋጣሚዎችን የሀገራችንም ሆነ የቤተ ክርስቲያናችን የታሪክ ድርሳናትን ብናገላብጥ የምናገኘው ነው፡፡
ሆዳቸው አምላካቸው፣ ነውራቸው ክብራቸው በሆኑ ቅጥረኞችና የወንጌልን ቃል በሚሸቃቅጡ፣ ምንም ዓይነት መንፈሳዊነት በሌላቸው አገልጋዮች ነን በሚሉ ሰዎች ዛሬም ቤተ ክርስቲያን በዘረኝነትና በጎሰኝነት መዘዝ ክፉኛ እየታመሰች ነው፡፡ ይሄ ክፉ መርዝ ዛሬ ብቻ ሳይሆን ትላንትም ቤተ ክርስቲያንን ሲያምስ የነበረ ክፉ ዲያብሎስ የዘራው የጥላቻ እንክርዳድ ዘር እንደሆነ የትናንት ታሪካችንን ብናገላብጥ የምንረዳው እውነት ነው፡፡
በዚህ ጽሑፍ መግቢያ ያደረግነው የእቴጌ ጣይቱ የተማፅኖ ደብዳቤም ይሄ የቤተ ክህነቱ ዘረኝነት አበሳ ባሕር ማዶም ተሻግሮ እንዴት ዕረፍት ነሥቷቸው እንደነበረና በዘመኑ የነበረውን ይሄንኑ አሳፋሪ እውነታ የሚያስረግጥ ነው፡፡ ለነገሩ በዛው ዘመን በምኒሊክ ቤተ መንግሥት የምኒሊክ የጤና ጉዳይ አሳሳቢ እየሆነ በመጣበት ወቅት ሥልጣን ከሸዋ እንዳይወጣ በሚፈልጉ በሸዌዮችና የጣይቱ ደጋፊ በነበሩ ጎንደሬዎች መካከል የነበረው ፍጥጫ፤ ዘረኝነት፣ ወንዘኝነትና ጎጠኝነት በሀገሪቱ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ምን ያህል ሥር የሰደደና አሳፋሪ እንደነበረ አንድ ማሳያ ነው፡፡
ዛሬም አንዳንዶች በክርስትናው ጥላ ሥር በመሆን የራሳቸውን ወገንና በቋንቋ የሚዛመዳቸውን የወንዛቸውን ሰው ብቻ በማሰባሰብ ከወንጌል እውነት ውጭ በማፈንገጥ ለእኩይ ዓላማቸው የወንጌልን እውነት ሆን ብለው ሲያጣምሙ እያየን ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ፡- ‹‹ማንንም ሰው ከክርስቶስ ውጭ እንደሆነ አላውቅም፡፡›› ብሎ ነበር የተናገረው፡፡ የዛሬዎቹ አንዳንድ ከእውነት ጋር የተፋቱ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይና አባቶች ነን ባዮች ግን ሰዎችን በክርስቶስ የመስቀል ፍቅር ሳይሆን የሚያውቋቸው በመጡበት ዘር፣ ጎሳና ማንነት፣ በሚናገሩት ቋንቋ መሆኑን እያየን ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያንም በዘረኝነትና በጎጠኝነት ምክንያት የቆሸሸውን የልጆቿን ልብ የምታጸዳበትን የይቅርታ እና የንስሐ ውኃንና ሳሙናን ለሕዝቡ ከመስጠት ይልቅ በተቃራኒው የዚሁ ሰለባ ሆና መገኘቷ፣ በነገሩ ልባቸው ያዘነባቸው ብዙዎች እውነተኛ አባቶቻችንና የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች እንዲሁም ሕዝበ ክርስቲያኑ፡- ‹‹ታዲያ መድረሻችንና ፍጻሜያችን ምን ሊሆን ነው?›› የሚለውን አሳሳቢ ጥያቄ እንዲጠይቁ እየተገደዱ ነው፡፡
በመሠረቱ ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ ኢየሱስ እንጂ የማንም አይደለችም፣ ሕዝቦቿም ከተለያዩ ቋንቋዎች፣ ነገዶች፣ ሕዝቦች፣ ወገንና ነገድ በክርስቶስ ኢየሱስ ክቡርና ቅዱስ ደም ልብሳቸውን ያጠሩ ሰማያውያን ዜጎች የተሰባሰቡባት እንጂ ሰዎች ስለመጡበት ዘር፣ ጎሳ፣ ወገን፣ ነገድ እና ቋንቋ ልዕልና የሚሰብኩባት አደባባይ ልትሆን አይገባትም፡፡ በዚህ ክፉ አስተሳሰብ ውስጥ ያሉ ሁሉ የብዙዎችን ልብ ላቆሰሉበት መርዘኛ ትምህርታቸውና የጥፋት መልእክታቸው የንስሐና የይቅርታ ልብ እንዲሆንላቸው ጊዜው ሳይረፍድ የምሕረትን አምላክ ይማጸኑ ዘንድ ይገባቸዋል፡፡ በክርስቶስ ኢየሱስ በአምላካችን እና በመድኃኒታችን መንግሥት፡- ዘር፣ ጎሳ፣ ቋንቋ፣ ወገንና ነገድ የሚባል ነገር የለም፣ ሁሉም ሰው በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ነው፡፡ ዘራችን ከማይጠፋው ከከበረው ከክርስቶስ ኢየሱስ ዘር፣ ዜግነታችን ሰማያዊ፣ ቋንቋችንም ሰማያዊ፣ ርስታችንም በሰማይ የሆነ የእግዚአብሔር ሕዝቦች!!!
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደው በሰውና በሰው መካከል የተገነባውን የዘረኝነት ግንብ ለማፍረስና እርሱ የሚመራትን አንዲት አዲስ ዓለም ወይም ቤተ ክርስቲያንን ለመመሥረት ነው፡፡ ከእንግዲህ ወዲህ ሰዎችን በክርስቶስ ብቻ እንጂ በዘራቸውና በቋንቋቸው ላለማወቅ ለእግዚአብሔር ቃል ልንገባ ያስፈልገናል፡፡ ክርስቶስ በመወለዱና በሞቱ ያፈረሰውን የዘረኝነት ግንብ ደግመን እንዳንገነባ ልንጠነቀቅ ይገባል፡፡
                    ወይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ አበዊነ!    
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ

አዳዲስ መጻሕፍት

ትርጉሙ:- ቀይ ዕንቈ

ለምድራችንና ለአገልግሎታችን በረከት የሆነ መጽሐፍ
የመጀመሪያ እትም ጥቅምት 2016 ዓ.ም

1ኛ ጢሞቴዎስ ትርጓሜ – ክፍል አንድ

የመጀመሪያ እትም ሐምሌ 2013 ዓ.ም

ምክር አዘል መጽሐፍ

የመጀመሪያ እትም