ሁለት ፍየሎች በጠባብ ድልድይ ላይ መሐል ላይ ተገናኙ ። ድልድዩ የተሠራው በጥልቅ ሸለቆ ላይ ነው ። ወደ ኋላ ለመመለስም ወደ ፊት ለመሄድም ያልቻሉት ፍየሎች ፊት ለፊት ተፋጠጡ ። እኔ ነኝ የማልፈው እኔ ነኝ ቢሉ ሲጋፉ ሁለቱም ወደ ገደል ይገባሉ ። ለምን እያየኸኝ መጣህ እስክሻገር አትጠብቅ ነበር ወይ ብለው ሙግት ቢገጥሙ መመለስ ከማይችሉበት ስፍራ ላይ ናቸው ። አንዳንድ ጉዳዮች የሚተዉ እንጂ የሚተነተኑ አይደሉም ። እኔ ነኝ የማልፈው ብለው በእልህ ፣ በትዕቢት ቢጋጠሙ ሁለቱም ወደ ሸለቆው ወድቀው የሚሞቱ ናቸው ። በዚያች ቀጭን ድልድይ ላይ ተፋጠው ቢውሉ በዝለት መውደቃቸው አይቀርም ። አንተ ዝቅ በል አንተ ለመባባልም ለመግደርደርም ጊዜ የላቸውም ። አንደኛው ፍየል ምንም ትንታኔ ሳያበዛ መሬት ላይ ለጥ ብሎ ተኛ ። አንደኛው ፍየልም በጀርባው ላይ ተራምዶ ተሻገረ ። ሁለቱም የሚሞቱበት ትዕቢት ስለ ወደቀ በትሕትና ሁለቱም ዳኑ ።
መሐል ላይ ከደረሱ በኋላ ብዙ ሰዎች ተፋጠዋል ። ንብረት ካፈሩ ፣ ልጆችን ከወለዱ በኋላ የተፋጠጡ ብዙ ባለ ትዳሮች አሉ ። ወደ ኋላ ቢመለሱ የሚያስጠጋ ዘመድ የለም ፣ ወደፊት እንዳይገሰግሱ ትዕቢት ይታገላቸዋል ። “እየዬ ሲዳላ ነው” እንዲሉ ብዙዎች ጉዳታቸው የሚሰማቸው ሲደላደሉ ነው ። በክፉ ቀን የተቻቻሉ ባልና ሚስት በበረከትና በዕረፍት ቀን ይለያያሉ ። የንብረት መደርጀት ፣ የልጆች ማደግ የምስጋና እንጂ የብሶት ርእስ መሆን አልነበረበትም ። የፉክክር ቤት ሳይዘጋ ያድራል እንዲሉ በምን ቸገረኝ ፣ የቤቱ መሪ እኔ ነኝ በሚል ትግል ብዙ ሕይወትና ንብረት እየባከነ ነው ። ሁለት ሰዎች አንድ መሪ ከጨበጡ ያለ ጥርጥር መኪናው ይገለበጣል ። ከገዛ ቤቱ የሸሸ ፣ የገዛ ኑሮውን መቀበል ያቃተው ብዙ ወገን አለ ። የታወከ ቤተሰብ የታወከች ቤተ ክርስቲያንንና አገርን ይወልዳል ። ቤተሰብ ሥጋዊና መንፈሳዊ ጥቅም ያለው ትልቅ ተቋም ነው ። ሰው ወደ ትዳር ከመግባቱ በፊት የሚያገባውን ወገን በሁለት ዓይኖቹ እንዲያይ ይፈቀዳል ፣ ካገባ በኋላ ግን አንዱን መጨፈን አለበት ። የሚገርመው ከመጋባታቸው በፊት ሁለት ዓይናቸውን የጨፈኑ ሰዎች ካገቡ በኋላ ሁለት ዓይናቸውን ይገልጣሉ ። አንዳንዴም በአጉሊ መነጽር መተያየት ይጀምራሉ ። ሰው እንኳን ፈልገንበት ፣ እንኳን ተከታትለነው እንዲሁም በግልጥ የሚወድቅ ነው ። ሰላምን ከሚነኩ ነገሮች የመጀመሪያው ሰዎችን መከታተል ነው ።
ብዙ መቶ ዓመታት በአንድነት የኖሩ ሕዝቦች ድንገተኛ መፋጠጥ ውስጥ ሲገቡ እናያለን ። መቼም ታሪክ በሌላው አገር ሻይ ቡና እየጠጡ የሚተርኩትና የሚያደምጡት የቅንጦት ወሬ ነው ። በእኛ አገር ግን የህልውና ጉዳይ እየሆነ ነው ። በዛሬው ስህተቱ የሚዳኝ ሰው የለም ፣ በትላንት ታሪክ ግን ዋጋ ከፋይ የሆነ ብዙ ሰው አለ ። ባልነበርንበት ዘመን በታሪክ መጣላት ተገቢ አይደለም ። በአያቱ ባለጠጋ ያልነበረ ድሀ የለም ፣ በአያቱም ድሀ ያልነበረ ሀብታም የለም ። ዓለም ተለዋዋጭ ነው ። የዛሬውን ጥያቄ ለመመለስ አቅም ካገኘንም በጣም ጎበዝ ነን ። ትላንት ላይ ኑቢያ የኢትዮጵያ አካል ነበረች ፣ የመን እነ ዐፄ ካሌብ ነጻ ያወጡአት ፣ ኢትዮጵያውያን የገዙአት ነበረች ። ግን ነበር ለታሪክ እንጂ ለመብል አይሆንም ። ይልቁንም ረጅም ጉዞ አብሮ የተጓዘ ሕዝብ እንጂ ባለፉት ሃምሳና መቶ ዓመታት የመጣ አዲስ ሕዝብ የለንም ። “ልጅ ደረሰ ቤት ፈረሰ” እንዲሉ ዘመናዊ ትምህርትን የቀመሰና የደረሰው ትውልድ አገርን አፈረሰው ! የኢትዮጵያውያን ውበት እንደ ነብር ዥንጉርጉርነት ነው ። ይህን የተለያየ ቋንቋና መልክ በረከታችን እንጂ መርገማችን አይደለም ። ኢትዮጵያዊ ሁኖ ከሁለትና ከአራት ጎሣ ያልተወለደ ማግኘት በጣም ከባድ ነው ። እንደ እኛ የተቀያየጠ ሕዝብ የለም ። ጥፋታችንም ልማታችንም የጋራ ነው ። ዛሬ ላይ በጠባብ ድልድይ ላይ ተፋጠናል ። በከፋፍለህ ግዛ መርሕ መጥተው የነበሩትን ቅኝ ገዥዎች አባረን አሳባቸውን ተግባራዊ አድርገነዋል ። የሰጡንን ካርታ ተቀብለነዋል ።
ኢትዮጵያውያን እምብዛም ዘመናዊ መሣሪያ በሌለበት በአድዋ ጦርነት ያሸነፉት አንድ ስለ ነበሩ ነው ። መሣሪያ በነበረበት በማይጨው ጦርነት የተሸነፉት መለያየት ስለ መጣ ነው ። ከተለያየን ደካማውም ያሸንፈናል ፣ አንድ ከሆንን የሚያሸንፈን ኃይል የለም ። ሰርገኛ ጤፍን ነጩንና ጥቁሩን ለቅሞ ለብቻው የሚያስቀምጥ ጎበዝ የለም ። የአገራችን ሰው ሰርገኛ ጤፍ ነው ፣ ይህን ወገን መለያየት ከባድ ነው ። እኛ ኢትዮጵያውያን አብረን ካልኖርን አብረን የምንጠፋ ነን ። አንድነታችን አማራጭ ሳይሆን ግዳጅ ነው ። የራሳችን የሆነ ማንነትና ቆራጥነት ያለን ሕዝቦች በመሆናችን በዙሪያችንና በመላው ዓለም ብዙ ጠላት አትርፈናል ። በኢትዮጵያ ያለው ክርስትናውም እስልምናውም የራሱ የሆነ ማንነት ያለው በመሆኑ ለጥፋት ዒላማ ከተደረገ ቆይቷል ። አሁን ያለንበት ሁኔታ በሸለቆው ላይ በተዘረጋው ጠባብ ድልድይ ላይ መሐል ላይ ተፋጠናል ። በመገፋፋት ፣ በትዕቢት ፣ በእልህ ሁላችንም እንሞታለን ፣ የሌሎችም ቅርጫ እንሆናለን ።
ይቀጥላል
ጥቅምት 20 ቀን 2019 ዓ.ም.