“እናንተ የምድር ጨው ናችሁ፤”
(ማቴ. 5 ፡ 13 ) ።
በታሪክ እንደምናነበው ጨው በዘመናት አብዮት ያስነሣ ነው ። በ1789 እአአ በፈረንሳይ በጨው ምክንያት የተጣለው ግብር ከፍተኛ ዓመፅ አስነሥቷል ። የጨው ግብሩ በአንዳንድ ከተሞች ላይ የተለያየ ሲሆን መኳንንቱንና የቤተ ክህነት ሰዎችን አይመለከትም ነበር ። ይህ ጫና ሙሉ በሙሉ ድሆች ላይ በመውደቁ የፈረንሳይ አብዮት እንዲነሣ አንዱ ምክንያት ሆኗል ። በሕንድ በ1930 እአአ በቅኝ የያዙት እንግሊዞች የጨው ግብር ጣሉ ። ይህንንም በመቃወም ፊት መሪ የሆነው ማሃትማ ጋንዲ የግብሩን ሕግ በግልጽ ተላለፈ ። በዚህ ምክንያት የተቀጣጠለው አብዮት ሕንድ በ1947 እአአ ነጻነትዋን እንድታገኝ ምክንያት ሆነ ። ትንሽ የሚመስለው ጨው ለትልቅ አብዮት መቀስቀሻ ሆኗል ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ክርስቲያኖችን “እናንተ የምድር ጨው ናችሁ” ሲላቸው እንደ ትንሽ ብትታዩም በዓለም ላይ የሞራል አብዮት ታስነሣላችሁ ማለቱ ነው ። ክርስቲያን ምድርን ቢንቅ ሰማይን አይቶ ነው ። መገፋቱን በደስታ ቢቀበል የሚፈርድለት አምላክ ስላለው ነው ። ፍቅርን በነጻ ቢሰጥ ፍቅርን ስለ ተቀበለ ነው ። ያለኝ ይበቃኛል የሚለውን መርሕ የሚከተለው የኑሮ ምሥጢር ገብቶት ነው ። ክርስቲያን እንደ ትንሽ ቢታይም ተጽእኖ የሚያመጣ ነው ።
ክርስትና ለምድር ባለ ውለታ ነው ። በኢትዮጵያ ያለችውን ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ብናይ ባለ ውለታ ናት ። ጎብኚዎች ወደ አገር የሚመጡት የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን ታሪካዊነት ለማየት ነው ። ቤተ ክርስቲያን እየተጠላች እንኳ የአገር እንጀራ ናት ። ታሪክ የሌለው ሕዝብ የልብ ሙላት የለውም ። ታሪክ የሌላቸው ታላላቅ አገራት ታሪካዊ ቦታዎችንና እሴቶችን የሚያፈርሱት የበታችነት ስሜት ስለሚያሰቃያቸው ነው ። አገራችን ባለ ታሪክ የሆነችው በታሪክ ማኅደር በቤተ ክርስቲያን ነው ። ጥቅጥቅ ያለ ዛፍና ደን ከታየ ወይ ደብር ነው አሊያም ገዳም ነው ። ዛፎች እንደ ጠላት ሲጨፈጨፉ ቅጠል እንኳ አልበጥስም ብላ አየር ንብረቱን የምትጠብቅ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ናት ። ገዳማት ትልልቅ ዩንቨርሲቲዎች ናቸው ። በእኛ አገር ብቻ ሳይሆን በሌላው ዓለም ገዳማት የእውቀት ደሴት ናቸው ፤ የፓሪስ ዩኒቨርሲቲ ፣ ኦክስፎርድ ፣ ካምብሪጅ መነሻቸው ቤተ ክርስቲያን ናት ። በምድር ላይ የምናየው ኪነ ሕንፃ ፣ ኪነ ጥበብ ፣ ሥዕላት የክርስቲያኖች ውጤት ናቸው ። በሐዋርያው ጳውሎስ የተጀመረው የእርዳታ ድርጅት እስከ ዘመናችን ደርሶአል ፤ ቀይ መስቀልን ያቋቋመ የክርስትና እርሾ ነው ። እናንተ የምድር ጨው ናችሁ ያለው የጌታችን ቃል ደርሶአል ።
ጨው ትንሽ መስሎ ትልቅ አብዮት ሲያመጣ በታሪክ አይተናል ። አሥራ ሁለቱ የጌታችን ደቀ መዛሙርት ትንሽ ቢመስሉም መላውን ዓለም በዕርፈ መስቀል/በክርስቶስ ፍቅር እያረሱ ፣ የወንጌልን ዘር ዘርተውበታል ። በምድር ላይ ለ2ሺህ ዓመታት የጸናች ማኅበር ቤተ ክርስቲያን ናት ። ጨው ርካሽ መስሎ ውድ ዋጋ ያስገኛል ፣ ደቀ መዛሙርቱም ሲታዩ የገሊላ ገበሬዎች ናቸው ። ዓሣ አጥማጅ ልፋተኛ ፣ ጠረኑ ደስ የማይል ነው ። ጌታ ግን በትንሹ የታመኑትን ወደ ትልቅ አደራ ጠራቸው ። የክርስቲያን የከፍታው ምሥጢር እግዚአብሔር ነው ። ላዩ ጎስቋላ ቢመስልም ውስጡ ግን ጠንካራ ነው ። ጽኑ ቁመና የሞተን መንፈስ መሸከም አይችልም ። የጸና መንፈስ ግን የደከመውን አካል መሸከም ይችላል ። ሰው የሚደርሰው እግር ስላለው ሳይሆን ተስፋ ስላለው ነው ። ተስፋ ውስጣዊ መብራት ነው ። ክርስቲያን ውስጡ ጽኑ ነው ። አሁን ካለው ክብር የሚመጣው ስለሚበልጥ ፍርሃትን ያሸንፋል ።
ጨው መገበያያ ገንዘብ ሁኖ አገልግሏል ። ባሮች ደመወዛቸውን በጨው መልክ ይቀበሉ ነበር ። ጨው በጥንቱ ዓለም ንብረትን የመቍጠሪያ ሰነድ ሁኖ አገልግሏል ። መቶ ብር የምንለው ወረቀት ነው ፣ መቶ ብር አይደለም ። የሰዎች ስምምነትና የመንግሥት ሥልጣን መቶ ብር አድርጎታል ። ንብረትንም በሰነድ ለመያዝ ገንዘብ አስፈላጊ ሆኗል ። ይህን ተግባር የቀደሙት ሰዎች በጨው ገንዘብነት ይጠቀሙበት ነበር ። ጨው ሀብት እንደሆነ ክርስቲያኖችም የምድር በረከት ናቸው ። አንድ ክርስቲያን በሞተ ቍጥር ምድር የሚጸልይላትን ሰው ታጣለች ። አንድ ካህን በሞተ ቍጥር ማኅበራዊ ጫና እየጨመረ ይመጣል ። የአንድ ሰባኪ ሞትም የአንድ ቤተ መጻሕፍት መቃጠል ነው ።
“እንዴት ካህን ይሙት ካህን ይቀበር ፣
መፀንፀኛው የወርቅ መቋሚያው የብር ፤
ተብሏል ።
እንግዲህ መቃብር ጠንክረህ ተማር ፣
ድጓ ተሸክሞ መጣልህ መምህር ፤
የተባለውም ለዚህ ነው !
ክርስቲያኖች የምድር ሀብት ናቸው ። በምድር ላይ ክርስትና ባይኖር ኖሮ በስብከት ቀርቶ በሰይፍ የሚያሳምን አካል ይገዛ ነበር ። በአሁን ሰዓት የምድር ኃያላን የሚባሉት የክርስቲያን መንግሥታት ናቸው ። ኃይል በሌሎች እጅ ቢወድቅ ኖሮ እኛን ካልመሰልህ ተብሎ ማለቅና መደምሰስ ይኖር ነበር ። ክርስቲያን የሌላውን ነጻነት ያከብራል ።
“እናንተ የምድር ጨው ናችሁ” ተብለናል ። ጨውነታችን የሚሠራው ለምድር እንጂ ለሰማይ አይደለም ። የምድር ቆይታችን ዘላለማችንን የሚወስን ነው ። ሕይወትንም ሽልማትንም የምናገኘው በምድር ላይ ባሳየነው እምነት ነው ። ዋጋችንን ማወቅ ፣ ያለ ዓላማ አልተፈጠርኩም ብለን ለሥራ መነሣት ይገባናል ። ጣፍጠን ለማጣፈጥ ቀኑ ዛሬ ነው ።
ይቀጥላል
ጥቅምት 24 ቀን 2019 ዓ.ም.