ጣልያን ከወጣ ጊዜ አንሥቶ የገዛ ልጆቻችንን ፣ አዋቂዎቻችንን መብላት ሥራችን ሆኗል ። የ1953 ዓ.ም. መፈንቅለ መንግሥት ጣሊያንን ያባረሩ ጀግኖችን በሙሉ የጨረሰ ነው ። የ1966 ዓ.ም. አብዮት ከስድሳ በላይ የሚሆኑ ዓለም አቀፍ ምሁራንን ፣ አገር ወዳዶችን ፣ የጦር ሳይንቲስቶችን የገደልንበት ነው ። ለ17 ዓመታት የተካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት ትውልድን የፈጀ ነው ። እስከዚህች ሰዓት ድረስ ምድሪቱ የደም ዕዳን እያከማቸች ነው ። ዝቅ የሚል ወገን ካልተገኘ ሁላችንም የገደል እራት ነን ። ጠንክረን ተዋግተን አይደለም ጠንክረን ሠርተንም ሕዝባችንን ከረሀብ ካዳንን ዕድለኞች ነን ። ኢትዮጵያ ዘመድ ያገኘች እንደሆነ የሚያለቅስላት እንዲህ ብሎ ነው፡-
“የገደለው ባልሽ ፣ የሞተው ወንድምሽ ፤
ኀዘንሽ ቅጥ አጣ ከቤትሽ አልወጣ ።
ዝቅ ማለት ያሻግራል ፣ እልህ ግን ሞትን ይጋብዛል ። እንዴት ቀኝ እጅ ከግራ እጅ ተጣልቶ የገላጋይ ያለ ይላል ?
ቤተ ክርስቲያን በጠባብ ድልድይ ላይ ነች ። የቀደሙት በረሀብ ፣ ከውሻ ጋር ታግለው የጠበቅዋት ቤት ዛሬ በጀት በተገኘበት ዘመን እየፈረሰች ነው ። ከቤተ ክርስቲያን እየበላ ወደ ዓለም የሚውጥ ፣ የሰይጣን የውስጥ ካድሬ እየሆነ ወንጌለ መንግሥትን የሚያደናቅፍ በዝቷል ። መወጋገዝና መነቃቀፍ እንጂ የእርቅ ምሳሌነት ከቤተ ክርስቲያን እየራቀ ነው ። ቤተ ክርስቲያንን ያወከው ራሱ ሰውዬው “አይ የእኛ ቤት” እያለ ያማርራል ፣ የሰው ልቅሶ ይቀማል ። ከክርስቶስ ጋር ሞቻለሁ ብሎ በመሐላ የጀመረ መነኮስ እንደገና ነቅቶ ጎሣና ነገድ አለኝ ካለ የሁሉ አባት መሆን ይሳነዋል ። ቤተ ክርስቲያንን ዝቅ በማለት ካልሆነ አሁን ባለው መፈራረድ አናድናትም ። የኑቢያ/የሱዳን ቤተ ክርስቲያን እስከ 1100 ዓ.ም ድረስ ሕያው ነበረች ። የሱዳን ቤተ ክርስቲያን ዛሬ የለችም ። በጊዜያዊ ጥቅም ስንባላና ከጠላት ጋር ወግነን ወንድምን ስናጠፋ መጨረሻችን መጨረሻቸው እንዳላማረ አብያተ ክርስቲያናት መሆኑ አይቀርም ። እንዲህ ያለ ቀን እንደሚመጣ ከልጅነታችን ጀምሮ የተቀደሱ አባቶች ሲናገሩ እንሰማ ነበረ ። በእኛው ዘመን የሚደርስ አልመስል ብሎን ቀኑ እንደ ደራሽ ውኃ መጣብን ። ቤተ ክርስቲያንን ለማትረፍ መፋጠጥ ፣ አንዱ ያንዱን የውስጥ ልብስ መግለጥ መፍትሔ አይደለም ። ዝቅ ብሎ መሸነፍ ፣ ለመፍትሔ መገናኘት ግድ ነው ።
እኔ ቀድሜ ወጥቻለሁ መንገዱን ልቀቅልኝ ቢል ፣ አንተ ማነህ የምለቅልህ ብሎ ሁለተኛው በኩራት ቢመልስ ኖሮ ሁለቱም ፍየሎች ገደል ገብተው ያልቁ ነበር ። አንዱ ዝቅ ብሎ ሌላውን መሸከም ፣ የሌላውን ጸጋና ሥልጣን ማክበር የምንተርፍበት ምሥጢር ነው ። ሁሉ ሊቅ ፣ ሁሉ ሹም የሆነበት አገር አይድንም ። እልህ ሁሉን ይገድላል ፣ ትሕትና ሁሉን ያሻግራል ። አንድ እርምጃ ወደ ኋላ መለስ ማለት ሁለት እርምጃ ወደፊት ለመራመድ ችሎታን ይሰጣል ። ድል ያለው ድጦ በማለፍ ሳይሆን ዘወር በማለትም ነው ። በትግሉ አሸንፎ ወንድምን ግን መክሰር የሕሊና ዕረፍት አይሰጥም ። ያኛውን ወገን ማሸማቀቅ ጥቁር ቀንን በራስ ላይ መጥራት ነው ። ማንም ራሱን ጋብዞ ወደዚህ ዓለም አልመጣም ። የእግዚአብሔርን እንግዳ ማሳቀቅ ፍርዱ ይግባኝ የሌለው ነው ። የሚገርመው እንዲህ ባተራመስነው ምድር ላይ ለመውለድ ያለን እቅድ ነው ፤ ነዋሪውን ከማምጣታችን በፊት መኖሪያውን መሥራት አለብን ። ችግርን በችግር ማሸነፍ ይቻላል ። በምድር ኃይል የመጣውን በሰማይ ኃይል መመለስ ሲቻል አይተናል ። ጥበበኛ ሰው ግን ችግርን ይፈታል እንጂ በበለጠ ችግር አያሸንፍም ። የተዳፈኑ እሳቶች የነገ ነበልባሎች ናቸው ። የመፍትሔ አካል መሆን ሞትን ሙሽርነት የሚያደርግ የሕሊና ዕረፍትን የሚያጎናጽፍ ነው ።
በዓለም ላይ የጠብ መነሻ እኔ እኔ ማለትና የእኔ የእኔ ማለት ነው ። ትክክል መሆናችንን በመተው ሰላምን ማምጣት አለብን ። ትክክለኛነታችንን በማረጋገጥና ልከኛነቴን እወቁልኝ በማለት ሰላም ላይመጣ ይችላል ። ዝቅ ለማለት ፣ ሌላውን ለመሸከም ፣ ወገንን ለማሻገር ማሰብ አለብን ። የሌሎች ሰላም የእኛ ሰላም ነው ። የሌሎች ማግኘትም የእኛ በረከት ነው ። የሌሎች መኖርም የእኛ ህልውና ነው ። ተፈጥሮ ተደጋግፎ የቆመ ነው ። አንዱ ሲጎድል ጣራው ማፍሰስ ፣ ቤቱ መፍረስ ይጀምራል ። በሁሉም ሃይማኖትና ባሕል አዳም የሰው ዘር አባት መሆኑ ይታመናል ። ከአንድ ምንጭ ተቀድተን እንደ ባዕድ መተያየት ፣ ድልድይን እያፈረሱ ግንብን መገንባት ፣ የሚያገናኘን ትልቅ ርእስ እያለ በሚያለያየን ትንሽ አሳብ መከፋፋት አለማስተዋል ነው ። ብቻ በአንድ መርከብ ላይ የተነሣ ማዕበል የሚመለከተው እገሌን ነው አይባልም ፣ ኢትዮጵያ የምትባል መርከብ ላይ የተሳፈርን መድረሳችንም መቅረታችንም የጋራ ነውና እንተዛዘን ።
ጥቅምት 21 ቀን 2019 ዓ.ም.