ሕፃን ልጅ የሚፈልገውን ይናገራል ። የሚፈልገውን እንደሚያገኝ እርግጠኛ ነው ። ብዙ ጊዜ ግን ፍላጎቱ ይጎዳዋልና ወላጆች ይከለክሉታል ። ሕፃኑ የአሁን ስሜቱን ሲያይ ወላጆቹ ግን ቋሚውን እውነትና የሚመጣውን ዘላቂ ችግር በማሰብ አይሆንም ይሉታል ። ሕፃኑም በመከልከሉ ለጊዜው ይከፋዋል ። ከልክለውኛል ብሎ ግን ቤቱን ለቆ አይወጣም ፣ ወላጅ ልቀይር ብሎም አያስብም ። የተከለከለውን ረስቶ ሌላ ይጠይቃል ። ልጅነት አስደሳች ጥገኝነት ያለው ሲሆን ወላጆችም በደስታ የሚሰጡት ፣ በማሰብም የሚከለክሉት ነው ። ጥገኛችን ነው ብለው ወላጆች አይንቁትም ፣ ለማኝ ነኝ ብሎም ልጅ አይሳቀቅም ። ያለመነው ትልቅ ነገር ገና ይሰጠዋል ። ያለፋበትን ቤት ይወርሳል ። ልጅ በድካሙ ሳይሆን በጸጋ ወራሽ ይሆናል ። ቢሆንም ከውርስ ሊነቀል የሚችልበትን ስህተት ሊፈጽም ይችላል ። የጠፋውን ልጅ ታሪክ የማያውቅ አማኒ የለም ፣ ራሱ የጠፋ መሆኑን የሚቀበል ግን የለም ። በሉቃስ 15 ላይ የምናገኘው የጠፋው ልጅ አባቱ ሳይሞት ውርስን ጠየቀ ፣ ይህ ልጅ የአባቱ መቆየት ሸክም ሆኖበት ነበር ። ፍላጎቱም ይሉኝታ አሳጣውና አባቴ ሆይ የሚደርሰኝን ስጠኝ ፣ ያንተ ሞት በጣም ዘገየብኝ ያለ ይመስላል ። ከአባቱ ፍቅር የንብረት ፍቅር በለጠበት። ውጤቱ ግን ያማረ አልነበረም ። የሆዳም መጨረሻ ሁሉን ከስሮ ባዶ እጅ መቅረት ነው ። እንዲህ ያሉ ልጆች ከርስት ሊነቀሉ ይችላሉ ።
ጸሎት ወደ አባት የሚቀርብ ጥያቄ ነው ። የጸሎት ዓላማው ልመና ብቻ ሳይሆን ኅብረት ነው ። ሕፃን ልጅ የሚለምነው ባይኖረውም አባቱን ያገኛል ፣ ማልዶ ይቀሰቅሰዋል ። ከአባቱ ጋር ብቻ መሆን ያረካዋል ። እውነተኛ አማኝም ጥያቄ ባይኖረውም ይጸልያል ፣ ጸሎት የአባትና የልጅ ኅብረት ነውና ። እግዚአብሔርን ስለ ራሱ መፈለግ ይገባል ። ልጅ ስለ ወረሰ ልጅ አይሆንም ፣ ልጅ ስለሆነ ግን ወራሽ ነው ። በአንዳንድ አገር ላይ በጥሩ ያስታመሙ ነርሶችና ሐኪሞች ውርስ ያገኛሉ ። ስለ ወረሱ ግን ልጅ አይደሉም ። የሚቀድመው የእግዚአብሔር ልጅ መሆን ነው ። እግዚአብሔር አባታችን ከሆነ የእርሱ የሆነ ሁሉ የእኛ ነው ። ችግር ካልገጠማቸው በቀር እግዚአብሔር ትዝ የማይላቸው ፣ አገልጋዮችን የማይፈልጉ ፣ ቤተ ክርስቲያንን ማየት የማይሹ ብዙ ምስኪኖችን እናውቃለን ። ጸሎት ለእነርሱ የእሳት አደጋ ስልክ ቍጥር ነው ። የእሳት አደጋ ካልተነሣ በቀር ወደዚህ ቍጥር መደወልን ማንም አያስብም ። እግዚአብሔር ግን አፍቃሪ አባታችን እንጂ የአደጋ ጊዜ ሠራተኛችን አይደለም ። ባገለገልንበት ዘመን የተረዳነው ነገር ቢኖር የሰው ልጅ ጥቂት ፍላጎቱ ሲሞላ ለእግዚአብሔር ጀርባውን ይሰጣል ። ያገለገሉትን አባቶች እንደ ጠላቱ ያያል ። “የክፉ ቀን ወዳጅ ያን ክፉ ቀን መስሎ ይታያል” የሚባለው ለዚህ ነው ። ቀላል ሰው የክፉ ቀን ወዳጁን በደግ ቀን ይረሳል ። በእኛ አገር አልፎ ያዋርዳል ። በዚህ ዘመን ባገለገለው ደቀ መዝሙር ያልተቀጣ መምህር የለም ።
ለእግዚአብሔር ሁሉን መንገር ተገቢ ነው ። ሁሉን ለሚሠራው መንገርን ትተን ምንም ለማይሠሩት ሁሉን መናገር ተገቢ አይደለም ። እግዚአብሔር ሰምቶ የማይመልሰው ጥያቄ ፣ አይቶ የማይሸፍነው ዕርቃን የለም ። ሁሉን ለእርሱ መንገር ብቻውን መልስ ነው ። እግዚአብሔር ባይሰጠን እንኳ ስላዳመጠን ዕረፍትን እናገኛለን ። የሚጠቅመንን የማይከለክለን አምላክ ፣ የሚጎዳንን አይሆንም ሲለን ደስ ሊለን ይገባል ። “አህያ ተማልላ ጅብ አወረደች” እንዲሉ እየተቀጣን ያለነው ካልሰጠኸኝ ብለን ችክ ባልንበት ነገር ነው ። የተዘጋ በር ሁሉ ያጣነው በረከት ሳይሆን ከአደጋ የሚጠብቀን ነው ። እግዚአብሔር የለመነውን እየከለከለ ያለመነውን የሚሰጠን ጊዜ ብዙ ነው ። የዮሴፍን ወደ ግብጽ መሸጥ እግዚአብሔር ለመልካም አደረገው ። ሙሴ ወደ ተስፋይቱ ምድር ባለ መግባቱ ኢያሱን የመሰለ መሪ አወጣ ። እነ ጳውሎስ እንዳይሄዱ የተከለከሉበት አገራት ነበሩ ። አንድ በር ተዘጋ ማለት ሁሉም በሮች ተዘጉ ማለት አይደለም ። እግዚአብሔር በረከቱን እያበሰለ ፣ አሊያም እኛን ለበረከቱ ብቁ እስክንሆን እየጠበቀ ነው ። አይሆንም የተባልነው ለዘላለም አይሆንም ነው ። ጠብቁ የተባልነውን በትዕግሥት መጠበቅ ተገቢ ነው ። ጸሎቴ አልሰመረም ብሎ እግዚአብሔርን መካድ ተገቢ አይደለም ። የሰማዕታትን በዓል እናከብራለን ። ሕይወታቸውን ሳይቀር ያጡትን የምስክሮች በዓል የምናከብረው ለእግዚአብሔር ነፍሳችንን ሳይቀር መተው እንዳለብን ለመማር ነው ።
እግዚአብሔር የሌለበት በረከት በረከት አይደለም ። ይሁዳ ጌታን በገንዘብ ለወጠ ። ነገር ግን ገንዘቡን በተነ ፣ ታንቆ ሞተ ። ያለ ጌታ ገንዘብ ዕድሜን ያሳጥራል ። ምግብን አትርፎ ነፍስን ማጣት ከንቱ እንደሆነ ዓለሙን አትርፎ እግዚአብሔርን ማጣትም ከባድ ኪሣራ ነው ። ስጦታው ሰጪውን ካስረሳ ትልቅ መቃወስ ነው ። ብዙዎች የሚፈልጉትን ነገር ካገኙ በኋላ ጌታ ሆይ ያንተ ድርሻ እስከዚህ ነው ፣ በቃ ተወን ይሉታል ። ልቅሶአቸውን ከእግዚአብሔር ጋር ፣ ሳቃቸውን ከዓለም ጋር ማድረግ ይፈልጋሉ ። እውነተኛው ችግር የሚጀምረው አሁን ነው ። የጠፋው ልጅ ከአባቱ ፍቅር የገንዘብ ፍቅር በለጠበት ። ጤናውን ፣ ክብሩን ፣ ሰላሙን ፣ በረከቱን አጥቶ ተመለሰ ። ዓለም በማታለል ወጥመድዋ ይዛ ያሳተችን ዛሬ እንመለስ ። ትላንትን የሚክስ ፍቅር በሰማይ አለ ። ንስሐም ዕድል ነውና ሊወሰድ ይችላል ። ለመምሸቱ እርግጠኛ ባልሆነ ቀን ላይ ሆነን ሌላውን ሰው ማሳዘን ተገቢ አይደለም ። እኮ እንመለስ !
ይቀጥላል
ጥቅምት 6 ቀን 2019 ዓ.ም.