መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » የሕፃናት ልብ » የሚመራኝን አውቀዋለሁ

የትምህርቱ ርዕስ | የሚመራኝን አውቀዋለሁ

ሕፃናት የሚወዱትን ሰው በሙሉ ልባቸው ይታመኑበታል ። የሚመጡትም ከነቆሻሻቸው እንጂ ጸድተውና ራሳቸውን ለመለወጥ ሙከራ አድርገው አይደለም ። የሚወዱት ወደ ላይ ቢወረውራቸውም እጆቹ ከሥር እንደሚጠብቁአቸው እርግጠኛ ናቸው ። ፍርሃታቸውን ፣ ውድቀታቸውን ፣ ፍላጎታቸውን ለመናገር አይሳቀቁም ። እግዚአብሔር በአባት መልክ ሲገለጥ እንደ ልጆች እንድንቀርበው ስለ ፈለገ ነው ። አዲስ ኪዳንን ልዩ የሚያደርገው ወደ እግዚአብሔር የሚያቀርበን ብቃታችን ሳይሆን በአባትነቱ የገለጠልን ፍቅር ነው ። በቤቱም እንደ እንግዳ ሳይሆን እንደ ልጆች እንታያለን ። በእርሱ የሚያምኑትን ወንድም እኅቶች ብለን ለመጥራት መንፈሳዊ መብት አግኝተናል ። እግዚአብሔርን በሙሉ ልብ ልንታመነው ይገባል ። አይተወኝም አይጥለኝም ብለን በእርሱ ላይ መደገፍ አለብን ። አምላካችን የሚያስመካ አምላክ ነው ። ያመኑትን ጥሎ የማያውቅ የሁልጊዜ አምላክ ነው ። ሕፃን ልጅ አባቱ እንደሚሰጠው እንጂ ከየት አምጥቶ እንደሚሰጠው ማሰብ እንኳ አይፈልግም ። አባቱ ለእርሱ ሁሉን ቻይ ሁኖ ይሰማዋል ። እንዲህ አድርጎ የሚያምናቸውን ልጅ መጣል ለደካሞቹ ወላጆች የማይቻል ነው ። ለልጃቸው ምንም ቢያደርጉ የማይረኩት ሁሉን ይሰጠኛል ብሎ ስላመነባቸው ነው ። መኪና ገዝተው ቢሰጡት የማይረኩት አባቴ አውሮፕላን ይገዛልኛል ብሎ ስለ ታመነባቸው ነው ።

በመንፈሳዊው ዓለም ስላመነው ሳይሆን ስለ ታመነ ያደረገልን ብዙ ነው ። በምድራዊ ግንኙነት ልጅ ከወላጅ የሚያገኘው የአቅማቸውን ያህል እንጂ እርሱ የታመነባቸውን ያህል አይደለም ። ልጅ በአባቱ ላይ ያለውን መታመን ያህል እንኳ እኛ ለእግዚአብሔር የለንም ። ሰው በሰው ላይ የታመነውን ያህል እኛ በእግዚአብሔር አለመታመናችን ያሳዝናል ። ሁኔታዎች ምቹ ላይሆኑ ይችላሉ ፣ የጠበቅነው ቀርቶ ያልጠበቅነው እየሆነ ነው ። ሰሜን እያየን ወደ ደቡብ እየተጓዝን ሊሆን ይችላል ። አሁንም በእግዚአብሔር መታመን አለብን ። እርሱ ከሦስት ነገሮች ውጭ ነው ። ከጊዜ ፣ ከቦታና ከሁኔታ ውጭ ነው ። የምንኖርበት ስፍራ ሰላም እያጣ ሊሆን ይችላል ። ውጤታማ የሆነ የሥራ አፈጻጸም ላይኖር ይችላል ። አብረውን ከሚኖሩት ጋር የአይጥና የድመት ግንኙነት ከጀመርን ሰንብተን ይሆናል ። የምንወደው እየራቀን የምንጠላው እየተጣበቀን ይሆናል ። ወደ ቤታችን ስንገባ ካልተሳካ ውሎ ጋር ፣ ከእንቅልፍ ስንነሣ ከድካም ጋር ሊሆን ይችላል ። የሰው ያለህ እያልን ሰው ተርበን ይሆናል ። ሰው አለ ሰው ግን የለም እያልን ለራሳችን ማውራት ከጀመርን ቆይተን ይሆናል ። የሚሰሙት ዜናዎች ጤናማ ላይሆኑ ፣ ዓለም ከመሪዎች ቁጥጥር ውጭ ልትወጣ እየታገለች ሊመስለን ይችላል ። ትርጉም የሌለው የመሪዎች ስብሰባ ተስፋ አስቆርጦን ፣ ዝናብ የሌለው ደመና ሁኖብን ይሆናል ። እግዚአብሔር ግን ከሁኔታው በላይ ነው ።

ብዙ ጥያቄዎች ወደ ሕይወታችን ቢመጡም መልሱን አላወቅን ይሆናል ። የሁሉም ነገር መልስ እግዚአብሔር ብቻ ነው ። “አልጋው ሲገኝ ባሉ አይገኝ” አለች ይባላል ። አንዱ ቀዳዳ ሲሞላ ዐሥሩ ይከፈታል ። አልሞላ እያለ የኑሮው እንስራ ይንቦጫቦጫል ። እግዚአብሔር ግን ለጥያቄዎቻችን መልስ የሚሰጥ ሳይሆን ራሱ መልስ ነው ። በማይለቁ እጆች እንደ ተያዝን ፣ በማይነጥፉ መዳፎች እንደ ተጻፍን ማሰብ ደስ ይላል ። እግዚአብሔር መልካም ፣ ጥበበኛና ታማኝ ነው ። ራሳችን በራሳችን በከፋንበት ዓለም ላይ እግዚአብሔር መልካም ነው ። እንዴት ይሠራዋል የማይባል ጥበበኛ ፣ ቀን አይቶ የማይከዳ ታማኝ ነው ። ሕይወታችንን ለእርሱ ማስረከብ የዕረፍታችን ምሥጢር ነው ። ሕፃን ልጅ መንገድ መሄድ ደስ ይለዋል ። ግን መራመድ አይችልም ። በአባቱ እቅፍ ፣ በእናቱ ጀርባ ላይ ሁኖ ፣ የመንገዱ ርቀት ሳያሳስበው ፣ ኪሎ ሜትሩን ሳይጠይቅ ይጓዛል ። ቤታችን እንዴት ይሆናል ብሎ ወደ ኋላ አይሰጋም ፣ ወላጆቹ ለእርሱ ቤቱ ናቸውና እነርሱ ያሉበትን ቦታ እንደ ግዛቱ ይመለከታል ።

ሴቶች የኖሩበት ዕድሜ እየረዘመባቸው ይቸገራሉ ፣ ወንዶች የሚኖሩበት ጊዜ እያጠረባቸው ይፈራሉ ። የመጡበትን መንገድ በማሰብ ዛሬም እንባ ቀለባቸው የሆነ ፣ የሚሄዱበትን መንገድ እየፈሩ እግር እያላቸው ታስረው የተቀመጡ ብዙዎች ናቸው ። የሕይወት ግብ በእግር ሳይሆን በተስፋ የሚደረስበት ነው ። ተስፋ ከሌለው እግረኛ ፣ ተስፋ ያለው እግር የለሽ እርሱ ግቡን ያሳካል ። መኖርን በአቅማችን ከለካነው ከባድ ነው ። እግዚአብሔርን ግዛታችን ካላደረግን ሁሉም ስፍራ እያስፈራን ይመጣል ። በልዑል መጠጊያ እንጂ በፎቅ መኖሪያ ለማደር ማሰብ የለብንም ። ያለ ጌታ ቤቱ ደጅ ነው ። አንድ ቀን ጥለነው እንሄዳለንና ለቤታችን ከልክ በላይ መጨነቅ አይገባም ። ዛሬ የምንሳሳለትን ንብረት ነገ ማንም እንደ ልቡ ይጠቀምበታል ። ጠላታችንም ገብቶ ሊወርሰን ይችላል ። ወዳጆቻችን የምንላቸው የሚጠሉንን በድብቅ ሲወዱ የነበረ ሲሆን ስንሞት በገሀድ ያደርጉታል ። ዛሬም ቢወስደን የዛሬ ስድሳ ዓመትም ቢወስደን ለዕለቱም ለዓመታቱም እርሱ ያስፈልገናል ። የልደት ቀናችንን ስላልወሰንን የሞት ቀናችንን መወሰን አንችልም ።

የነቢዩ ዳንኤል ጸሎቱ በአንበሳ ጉድጓድ ከመጣል አላዳነውም ፣ ከአንበሳ አፍ ግን አድኖታል ። ያለ ችግር የሚኖር አማኝ የለም ። አብርሃም የተጓዘው ወደማያውቀው ምድር ነው ። መንገዱ ባይታየንም በእግዚአብሔር ታምነን መጓዝ አለብን ። አንድ ሾፌር ጉዞ የሚጀምረው የሚሄድበት መንገድ ሁሉ ታይቶት አይደለም ፣ አንዱን ምዕራፍ ሲጨርስ ሁለተኛው እየታየው ነው ። መንገድ የሚታየው በተጓዙ ቍጥር ነውና እንጓዝ ። ከዚህ በፊት ሄደንበት የማናውቀውን መንገድ ሾፌሩን ፣ ካፒቴኑን አምነን እንጓዛለን ፣ እንዲህ በማመናችን ተጎድተን አናውቅም ። ነገም በእግዚአብሔር እውቀት ውስጥ ናትና በርቱ !

መንገዱን አላወቅሁትም ፣ የሚመራኝን አምላክ ግን አውቀዋለሁ !

ይቀጥላል

ጥቅምት 4 ቀን 2019 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ