ሙላ ወንዜ
ተው ቦርከና ሙላ ፣ ላንተም ይሻልሃል ፤
ያልሞላህ እንደሆን ሁሉም ይረግጥሃል ።
ቦርከና ወንዝ በደሴና በኮምቦልቻ የሚገኝ ወደ አዋሽ የሚገባ ነው ። ወንዝ የሞላ እንደሆነ ማንም አይደፍረውም ። ዋናተኛም ይሰጋዋል ። የጎደለ እንደሆነ ወለሉ ይታያል ። ገመናው ይጋለጣል ። ሕፃን ሽማግሌው ፣ ምሁር ያልተማረው ሁሉም በድፍረት ይረግጠዋል ። “ውኃ ሲጎድል ተሻገር ፣ ዳኛ ሲገኝ ተናገር” ይባላል ። ያልጎደለ ውኃን የሚረግጠው ፣ የሚያቋርጠው ፣ የሚደፍረው ማንም የለም ። የውኃ ግርማው ሙላቱ ነው ። ወንዝ የሚጎድልበት ጊዜ አለ ። ምንጮቹ ሲደርቁ ይጎድላል ፣ ክረምት ሲከዳ ግርማውን ያጣል ። በየመንገዱ ሲጠለፍ ፣ ቅርብ አዳሪ ሲሆን ወንዝ ወለሉን ያሳያል ። አገር የሚያቋርጠው ሰፈር ላይ ይቀራል ። ወንዝ ሲሞላ ይታፈራል ። ነዳጁን ሞልቶ ሩቅ አገር ይጓዛል ። “ወንዙ ሞልቷል አሉ ፣ እንዳትዳፈሩት” ይባልለታል ። የጎደለ እንደሆነ ሁሉም ይረግጠዋል ። ተመልሶ አይመጣም ብሎ የዳስ ቤት ይሠራበታል ። የአሸዋውን ግርጣት ፣ የድንጋዮቹን ዓይናማነት እያየ ሰው ሁሉ መሳቂያ ያደርገዋል ። የገበያ ስፍራ ፣ የሸቀጥ ማራገፊያ ይሆናል ። ራሱን ያስከብር ብሎ ደምብ አስከባሪውም ስለ ወንዙ መወረር አይደንቀውም ።
ሰውም የሚከብረው የሞላ እንደሆነ ነው ። ጉድለቱን ለእግዚአብሔር ፣ ሙላቱን ለሰው ቢገልጥ መልካም ነው ። የሰው ዓይን ሙሉ ነገር ይፈልጋል ፣ የእግዚአብሔር ዓይን ግን ጎዶሎውን ሊሞላ ያስሳል ። የሰው ልጅ የሚጎድልበት ቀን አለው ። ምንጮቹ እየነጠፉ ሲመጡ ይጎድላል ። ጸሎቱ ሲቀዘቅዝ ኃጢአት ይጫጫነዋል ። ወዳጆቹ እያለቁ ሲመጡ ብሶተኛ ይሆናል ። መካሪዎቹ እልፍ ሲሉ ብስጩና ተበቃይ ይሆናል ። እቴጌ ምንትዋብ ሲሞቱ ዐፄ ቴዎድሮስ ከቍጣ የሚያበርዳቸው ፣ ከጭካኔ የሚያራራቸው አልተገኘም ። እንደ ጥንቱ አይሆንም ፤ ሁለተኛ ትዳር ቢይዙም ፣ አገር የተገዛላቸው ንጉሥ ቤታቸው ዐመፀባቸው ። ቢወልዱም የማያሳድጉትን ልጅ ወለዱ ። ቀን ጎድሏልና የንጉሥ ልጅ ስደተኛ ሆነ ። አልጋ ወራሹ አልጋ አጥቶ ፣ ባሕሉን ቋንቋውን በማያውቅ አገር ላይ ባይተዋር ሁኖ በልጅነቱ ገና በ18 ዓመት ዕድሜው ሞተ ። “መካሪ የሌለው ንጉሥ ያለ አንድ ዓመት አይነግሥ” እንዲሉ መካሪ ሲታጣ ዕድሜ እያጠረ ይመጣል ። ጉልበት ሲከዳ ሁሉም ይንሸራተታል ፣ የሥልጣን ፀሐይ ስታዘቀዝቅ ያከበረ ሁሉ ሊያዋርድ ይፈልጋል ።
ሙላት ቅድስና ነው ። እግዚአብሔር ከብረን እንድንኖር ትእዛዛቱን ሰጠን ። ትእዛዛቱ የቤተ መንግሥት ኑሮ እንድንኖር የሚያደርጉን ናቸው ። የቤተ መንገሥት ኑሮ ማለት ክብር ያለው ኑሮ ማለት ነው ። የራስን ክብር ማወቅና ክብር ለሚገባቸው ክብር መስጠት የእግዚአብሔር ቃል የሚያዝዘን ነው ። ምሥጢር አንድን ሰው ክቡር ፣ አንድን መንግሥት ጠንካራ የሚያደርገው ነው ። ምሥጢራችን አደባባይ ከተዘራ ክብር እያጣን እንመጣለን ። ምሥጢር ያላቸው አብያተ ክርስቲያናት የተከበሩ ናቸው ። ባልና ሚስት ምሥጢር ሲኖራቸው ልጆቻቸው ሳይቀር ያከብሩአቸዋል ። ሁሉም ነገር ለልጅ አይነገርም ። የቤተ ክርስቲያን ጉዞ ከምሥጢር ጋር የተያያዘ ነው ። ካህኑ ስለ ምእመኑ የሚያውቀውን ሁሉ ቢናገር አገር ይፈርሳል ። በማይሸፍኑን ፊት መራቆት ፣ ለማይሸከሙት ምሥጢራችንን መንገር ጎዶሎ ቀንን በራስ ላይ ማወጅ ነው ።
እግዚአብሔር የሰጠንን በረከት በአግባቡ አለመጠቀም ፣ በድግስና በስጦታ ማባከን የረሀብ ቀንን ያመጣል ። ሰዎች ምንም ባንሰጣቸው አለው መባልን ይወዳሉ ። ያለን የራሳችን ቢሆንም ፣ የሚጎድልብንም ለራሳችን ቢሆንም የሰዎች ጠባይ ግን ሲለዋወጥ በግልጽ እናያለን ። አለመጉደል ፣ አንሶ አለመገኘት ይገባል ። ስናጣ ራሳችንን ለመቀበል እንኳ እንቸገራለን ። የብዙዎችን በር አንኳኩተን የሚከፍትልን እንቸገራለን ። ዘመድ አዝማድን ተቀይመን አንጠግብም ። ዓለሙ ሁሉ ፊቱን ያዞረብን ስለሚመስለን ለሰው ያለን አመለካከት ክፉ ይሆናል ። ሰዎች ስለ እኛ ብዙ ሊያስቡና ሊናገሩ ይችላሉ ፣ ዋናው ይዞ መገኘት ነው ። ዘመድ አልባ የሆንነው ፣ የሚራራልን ያጣነው ራሳችንን ችለን እንድንቆም ነው ። የጎደልን ቀን ፣ የሰው ፊት ያየን ሰዓት ሁሉም ይረግጠናል ። ስሜታዊነት ፣ ዘመን ላመጣው ጨፋሪነት ፣ ትዳርን በአግባብ አለመያዝ ያጎድላል ፣ አጉል ባልንጀራ ፣ ውዳሴ ከንቱ መውደድ ያጎድላል !
ጤና የእግዚአብሔር በረከት ነው ። ለአንዳንድ አባቶች ደዌ ዘበጸጋ ይገጥማቸዋል ። ጤና ሳለ የሚናቅ ከሄደ በኋላ ግን በቀላሉ የማይገኝ ነው ። ሆዳችንን ስንወጠር መተንፈስ ይናፍቀናል ፣ አየር ማውጣት እንኳ ትልቅ ጸጋ መሆኑን እንረዳለን ። ቀላል በሚመስል በሆድ ድርቀት ሕመም የሚሰቃዩ ብዙዎች ናቸው ። ጤና ከገንዘብ በላይ ነው ። ልጅ ከጦረው ጤናው የጦረው ይሻላል ። ጤናችን የጎደለ ቀን በሰው እጅ እንወድቃለን ። ሁሉም አቅም አንሶት በግድ በሚኖርበት ዘመን ላይ ጤናንን መጠበቅ ተገቢ ነው ። በትክክል ኖረን ምንም ቢመጣ የሚቆጭ አይደለም ። ሁን ብለን ያወክነው ጤና ግን ያጸጽታል ። ጤና ሲጎድል ሁሉም ይረግጠናል ።
ሰው ደፍሮ የሚኖረው ፣ ተከብሮ የሚያድረው አዋቂ ሲሆን ነው ። አዋቂዎችን መንግሥታት ቢያጠፉአቸው እንኳ ስለ ፈሩአቸው ነው ። መሣሪያ ይዞ ከሸፈተው በላይ የአንድ ምሁር ብዕር አገርና መንግሥትን ያናውጣል ። የሚያስፈራው ጥይት መያዝ ሳይሆን ባለ አሳብ መሆን ነው ። በየዕለቱ በእውቀት ላይ እውቀት መጨመር ይገባል ። ከእውቀት የጎደልን ቀን ሁሉ ይንቀናል ። የላይ ጡንቻውን የሚያዳብረው ትውልድ ውስጣዊ አቅሙን በእውቀት ማጠናከር አለበት ። መረጃን እንደ እውቀት የሚያይ ትውልድ ዘላቂ እውቀት የቱ ነው ብሎ ማሰስ አለበት ። በተቋማት ገብቶ የሚማረው የእንጀራ እውቀትን ሲሆን የሕይወት እውቀትን ከኖሩት ሰዎች ለመማር ትውልድ ዝቅ ማለት አለበት ።
ልብ አድርጉ ጎድሎ የሚወደድ ሕፃን ብቻ ነው ። ሲሳሳት ይቅርታ የሚደረግለት ፣ ሲወድቅ ብራቮ/ጎበዝ ተነሣ ተብሎ የሚጨበጨብለት ሕፃን ብቻ ነው ። ድሮ በጉድለትን የሚወዱህ ዛሬ ግን ጉድለትህን የዜና ሽያጭ ያደርጉታልና ጎድለህ አትገኝ ። አንድ ጊዜ ለመናገር ሁለት ጊዜ አስብ ። እንደ ነደደህ መልስ አትስጥ ። ከሚንቁህ ጋር ጊዜህን አታጥፋ ። የሚቀኑብን ፈጥነህ ራቅ ። ስምህን ለሚያጠፉት ጆሮ አትስጥ ። ብቻ ሊረግጡህ ለሚፈልጉህ ጎድለህ አትገኝ ። ለነገ አትጨነቅ ፣ ዛሬን በትክክል ከኖርህ ለነገ ይተርፋል !
ጥቅምት 7 ቀን 2019 ዓ.ም.