የትምህርቱ ርዕስ | እንባ አባሹ

እንቆቆም ጠጣሁ ፣ ግራዋም ጠጣሁ ፣
እንደ መጠቃት የሚመር አጣሁ ።

መጠቃት ያማል ፣ ሰው ሰብአዊና መንፈሳዊ ክብር ያለው ፍጡር ነው ። ይህ ዓለምም የእኩል ቤት ነው ። የእኩል ቤትነቱ ከመሰሉ ሰው ጋር ብቻ ሳይሆን ከእንስሳትና ከአራዊት ጋርም የጋራ ቤቱ ነው ። የተጠቃ ሰው ጥቃቱን መመለስ ባለመቻሉ ከጥቃቱ በላይ እየተጎዳ ይመጣል ። መቼም ተጎድተን ካልጠበቅነው የሚጎዳን የለም ። እኔ ብቸኛ ነኝ ፣ ቀን የጣለኝ ሰው ነኝ ፣ ሁሉም ነገር በወገን ሆኗል እኔ ግን ዘመድ የለኝም በሚል ስሜት ውስጥ ያለ ሰው በትንሽ መነካት በጣም ያመዋል ። አስቀድሞ በተጎዳ ስሜት ስላለ ሁሉም ነገር ያቆስለዋል ። ነገር ግን እውነተኛው አባታችን እግዚአብሔር ነው ፣ ያለነው በአባታችን ርስት ነው ። እውነተኛ ዘመዶቻችንም በእግዚአብሔር የሚያምኑ ፣ ደግሞም ቅዱሳን መላእክትና ጻድቃን ናቸው ። እኛ ብቸኛ አይደለንም ። ጥቃታችንን የሚመልስ የበቀል አምላክ አለን ። እግዚአብሔር ለሁሉ ዋጋውን ይከፍለዋል ። ሕፃን ልጅ ተነባብረው ሲያጠቁት መልስ አይሰጥም ። እያለቀሰ ወደ አባቱ ይሄዳል ፣ አባቱም በቀሉን ይመልስለታል ። እኛም በቀልና ፍርድ የእርሱ ወደሆነው አምላክ መገስገስ አለብን ። ያጠቁንን ሰዎች በትልቁ ማጥቃት ሲያቅተን በጥላቻ ፣ ስም በማጥፋት ፣ በሐሜት ለመበቀል እንፈልጋለን ። ይህ አምላክን ፍርድ እንዲዘገይ ማድረግ ነው ። እግዚአብሔር የፍርድ ወንበሩ ላይ እስከ ተቀመጥን ድረስ አይፈርድልንም ። ዝም ስንል እርሱ ይናገራል ።

ዛፍ ድንጋይ ሲወረውሩበት ፍሬ ይሰጣል ። ልጅ ሳለን የሾላ ፍሬን ለማውረድ ድንጋይ እንወረውራለን ። እኛ ድንጋይ ስንወረውር ዛፉ ግን ፍሬ ይሰጣል ። ድንጋይ ለሚወረውሩብን ፍሬ መስጠት ይገባል ። ሰዎችን በትልቁ የምንበቀላቸው በመልካምነት ነው ። ቅዱስ እስጢፋኖስ በድንጋይ ለሚወግሩት ፍሬ ሰጣቸው ። “ተንበርክኮም፡- ጌታ ሆይ፥ ይህን ኃጢአት አትቍጠርባቸው ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ ። ይህንም ብሎ አንቀላፋ ። ሳውልም በእርሱ መገደል ተስማምቶ ነበር” (የሐዋ. 7 ፡ 60) ። ሳውል የኋላው ጳውሎስ ይህን ፍሬ ቃል ከሰማ ጀምሮ ምንም እንቅልፍ አልነበረውም ። ድንጋይ ለወረወሩበት ያ የጽደቅ ተክል እስጢፋኖስ ፍሬ ሰጠ ። እስጢፋኖስ ኃይለ ቃል ተናግሮ ፣ ዝቶ ቢሆን ኖሮ የሳውል ልብ ይበልጥ ይደነድን ነበር ። ጳውሎስ በእስጢፋኖስ ጸሎት የተወለደ ትልቅ ሐዋርያ ነው ። ጳውሎስ ብዙ መከራና ፈተና ተቀበለ ፣ በመጨረሻም በሰይፍ ተቀላ ። ምናልባት የፈጸመው ክፉ ድርጊት ስለ ነበር በብዙ መከራ ውስጥ አልፏል ። የዘሩትን ማጨድ አይቀርምና ። እግዚአብሔር ንስሐን ይቀበላል ፣ የዘሩትን ማጨድ ግን ሊቀጥል ይችላል ። ንስሐ በነፍስ ያድነናል ፣ በሥጋ ግን ዋጋ ልንከፍል እንችላለን ። በኃጢአት ምክንያት በበሽታ ብንወድቅ በንስሐ አማካይነት በነፍሳችን እንድናለን ፣ በሽታው ግን ሊቀጥል ይችላል ። ኃጢአት መዘዙ ብዙ ነው ።

እንኳን ኃጢአትን የደከመ ጽድቅን ማድረግ የለብንም ። የቀዘቀዘ አምልኮም ደመናን የማያልፍ ነው ። በዚህ ዓለም ላይ ሌላውን ሰው ለመጉዳት መኖር አይገባንም ። ደካማ ፣ ወገን የለሽ የመሰለን ሰው ብርቱ አምላክ አለው ፣ ቅዱሳን መላእክትም ወገኖቹ ናቸው ። ከኒውክለር በላይ የሚያሰጋ የድሀ እንባ ነው ። የድሀ እንባ ያለባቸው ተቅበዝባዥ ናቸው ። ደምና እንባ አንድ ናቸው ። ደም ቀይ ፣ እንባ ውኃ መሳይ ነው ። ሁለቱም ጥቂት ይመስላሉ ፣ ከውቅያኖስ በላይ ያሰጥማሉ ። የሰው ደምና እንባ ያለባቸው ሰዎች ያለ ሱስ መዋል ፣ ያለ መጠጥ መተኛት አይችሉም ። በሕይወታቸው እጅግ የተሰቃዩ ናቸው ። በራሳቸው ላይ የማይወስኑት ብዙ ጠላት አለኝ ብለው ስለሚያስቡ ጠላቶቻቸው እንዳይደሰቱ ነው ። የሰው እንባ ያለበት ሰው ለልጁ ግፍ ያስቀምጣል ፣ የሚወዳቸው ነገሮች ሲረግፉ ቁጭ ብሎ ያያል ። ሰውን ስንጎዳ ሕሊናውን ፣ አካሉን እንሰብራለን ። ማኅበራዊ ግንኙነቱን እናበላሻለን ። ያ ተበዳይ ሰውን ሁሉ በእኛ መልክ እያየ ሁሉን እንዲፈራና እንዲሸሽ እናደርገዋለን ። ደግ ከሆነ ክፉ ፣ ሰጪ ከሆነ ቢስ ይሆናል ። ክፉ ሰዎች ሁሉ ክፉ የነበሩ ሳይሆኑ እኛ ያከፋናቸው ሊሆኑ ይችላሉ ። ይህ ትልቅ ኃጢአት ነው ። እግዚአብሔርን ወዳጅ አሳጣነው ማለት ነው ።

ሕፃን ልጅ በደረሰበት ጥቃት እያለቀሰ ወደ አባቱ ይሄዳል ። በአባቱ እቅፍ ውስጥ ሁኖ ልቅሶውን ይጨርሳል ፣ እንባውን በአባቱ ልብስ ያብሳል ፣ በአባቱም ፍቅር የደረሰበትን ይረሳል ። አባቱ እንዲበቀልለት ይፈልጋል ። “ቆይ አባቴ ይምጣ ለአባቴ ነው የምነግርልህ” ይላል ። በእውነት የእኛ አባት ይመጣል ። በአደባባይ ተጋብቶ በአደባባይ መዘላለፍ ሊከብደን ይገባል ። አባቴ ይመጣል ብለን መተው ይገባል ። “የጨዋ ልጅ ሲፋታ የሚጋባ ይመስላል” እንዲሉ ። ስንለያይ ደግ ደጉን ብቻ ማውራት ይገባል ፣ አልቆአልና ። አልቃሾችን በእቅፉ የሚሰውር ፣ በልብሱም እንባቸውን የሚያብስ አምላክ አለ ። “በዙፋኑ መካከል ያለው በጉ እረኛቸው ይሆናልና ፥ ወደ ሕይወትም ውኃ ምንጭ ይመራቸዋልና ፤ እግዚአብሔርም እንባዎችን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል።” (ራእ. 7 ፡ 17) ።

አሜን !

ይቀጥላል
መስከረም 29 ቀን 2019 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ