መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » የሕፃናት ልብ » ከትቢያ ያነሣል

የትምህርቱ ርዕስ | ከትቢያ ያነሣል

በምድር ላይ እንደ ሕፃን ልጅ ፍጹም ድሀ የለም ፣ ነገር ግን ምንም አይጎድልበትም ። የተወለደው ዕራቁቱን ነው ፣ የሚጠብቁት ግን ብዙ አልባሾች ናቸው ። ወደማያውቀው አገር ሲመጣ ስጋት የለበትም ። እውቀት የለውም ፣ አቅም የለውም ። እንደውም ሲወለድ ሕፃን ተወለደ ተባለ እንጂ እገሌ ብሔር ተወለደ አልተባለም ። ሰው የሚጀምረው በሰውነት ነው ። የሚፈጽመውም በሰውነት ነው ። ሲወለድ ሕፃን ፣ ሲሞት ሬሣ ይባላል ። ሕፃን ምንም የሌለው ፣ የብሔር ስምም የሌለው ቢሆንም አንድም ነገር አይጎድልበትም ። ገንዘብ ሳይዝ ምግብ ይለምናል ፣ በነጻ ያገኛል ። ምግቡን አዘገያችሁ ብሎ ያለቅሳል ፣ ያለ መብት አስከባሪ መብቱ በሙሉነት ይከበርለታል ። ከሚነቃበት የሚተኛበት ጊዜ ብዙ ነው ፣ ዓይኖች ግን ተተክለው ይጠብቁታል ። አባወራው እየጮኸ የሚሰማው የለም ፣ ሕፃኑ ግን ትንሽ ድምፅ ሲያሰማ ፣ በሕልሙም ሲያወራ ቶሎ ይደመጣል ። እጆች አሉት ሥራ አይሠሩም ፣ እግሮች አሉት አይራመዱም ። ፍቅር ነው ይሉታል ፣ ይስሙታል እንጂ ገና መሳም እንኳ አለመደም ። እኔ ላንተ ስል ነው የምኖረው ይሉታል ፣ ሕፃኑ ከመጣ ወራት ሆነውታል ፣ ወላጁ ግን ሠላሳ ዓመት ያለ ሕፃኑ ኖሯል ።

ይህን ዓለም በድህነት ጀምረነዋል ፣ ዕራቁታችንን ተወልደናል ። “ዕራቁቱን ለተወለደ ቁምጣ መች አነሰው” ይባላል ። መጨነቃችን ሁሉ ከንቱ መሆኑን ለመግለጥ ነው ። ምንም ይዘን አልመጣንምና ምንም ይዘን አንሄድም ። እንደውም ጥለነው የምንሄደው ነገር በረከቱ ሳይቀር የጥል ፣ የክርክር ፣ የመገዳደያ ርእስ ይሆናል ። እንኳን ስርቆታችን በረከታችንም ጠብ ያመጣል ። ስጡ የተባልነው ሞተንም አንድነትን እንዳንለያይ ነው ። በጠባብ ማኅፀን ተረግዘን ፣ በጠባብ መቃብር እናድራለን ። ያቺ ከማኅፀን ስንወጣ እኛን የተቀበሉባት ጨርቅ አብራን ትኖራለች ። ያቺ ነጭ ጨርቅ ከእኛ ጋር እያደገች በመጨረሻ ከፈን ትሆናለች ። ይዘነው የምንሄደው ሀብትና ዝና ፣ ሥልጣንና ከበሬታ የለምና መመካት አይገባም ። የሞታችን ቀን የሚነገርልንን ጽድቅ ለመስማት ዕድል እንኳ የለንም ። በእኛ ስም የተደገሰውን መቅመስ እንኳ አንችልም ። ሰዎች በሞታችን ላይ የሚያሳዩንን ፍቅር በቁማችን ቢያሳዩን ኖሮ ዕድሜአችን ምናልባት ይጨምር ነበር ። ግን ከዚህች ውሸታም ዓለም ሞት የተባለው ሠረገላ ይገላግለናል ። በቁማችን እኛን ያንገበገቡን ሰዎች ከሞትን በኋላ በእኛ ሞት እንደ ተንገበገቡ ያወራሉ ። በቁማችን ያልሰሙን ሰዎች ከሞትን በኋላ “እንዲህ ይል ነበር” እያሉ ቡና ይጠጡብናል ። ብቻ ምንም ይዘን አልመጣንም ፣ ምንም ሀብት ይዘን አንሄድም ። ለመስጠትም መኖር ያስፈልጋል ።

የሰው ልጅ ዕራቁቱን መጥቶ ዕራቁቱን ሲሄድ ትቶት የሚሄደው ሥራው ግን ሲታወስበት ይኖራል ፣ ሥራውም ቀድሞት በሰማይ ያሸልመዋል ። ሕፃን ልጅ ምንም ድሀ ቢሆን አይጎድልበትም ። እኛም ባለጠጋ አባት አለን ። ወደ ዓለም ያመጣን ወደ ሌላ ዓለም የሚወስደን አባት አለን ። በምድር ያለ አባት ልጁን አገር ካገር ሊያዞረው ይችላል ። ዓለማትን እያፈራረቀ የሚያሳይ ግን እግዚአብሔር ብቻ ነው ። ትንሽ መሬት እንናፍቃለን ፣ ዓለም የሚያወርስ አባት አለን ። ዕራቁቱን የተወለደውን ሕፃን ጨርቅ ይዘው ይጠብቁታል ፣ በእግዚአብሔር ቤት የምንኖረው ተሸፍኖልን ነው ፣ የገባንበት መስፈርቱም ተጋርዷል የሚል ነው ። ወደማናውቀው ነገ እየተጓዝን ቢሆንም የሕይወታችን ፊታውራሪ እግዚአብሔር አለልን  ። ራሱን መከላከል የማይችለው ሕፃን ልዩ ጥበቃ አለው ። በታላላቅ አደጋዎች እንኳ የመትረፍ ዕድል ያለው ሕፃን ልጅ ነው ። አቅም ለሌላቸው እግዚአብሔር አቅም ነው ። ብዙ ስጋቶች አሉብን ። የጦርነት ፣ የረሀብ ፣ የመለያየት ፣ የዝርፊያ ፣ የበሽታ ፣ የኢኮኖሚ ፣ የአስተዳደር ጽኑነት ስጋቶች ያናውጡናል ። እግዚአብሔር ግን ካስፈሩን ነገሮች በላይ ነው ። ከማመን ውጭ ለመኖር ዋስትና የሚሰጥ ምንም ነገር የለም ። ወደማላውቀው ምድር ያመጣኝ ፣ ወደማላውቀው ነገ የሚመራኝ ፣ ራሱን ተማምኖ የፈጠረኝ አምላክ አለኝ ብለን መደላደል አለብን ።

“ከሕዝቡ መኳንንት ጋር ያስቀምጣቸው ዘንድ፥ የክብርንም ዙፋን ያወርሳቸው ዘንድ፥ ችግረኛውን ከመሬት ያስነሣል፥ ምስኪኑንም ከጉድፍ ያስነሣል” (1ሳሙ. 2፡8) ።

ሊቀ ጳጳሱ ሲናገሩ፡- “ለእምዬ አዲስ አበባ እልል በሉላት” ብለዋል ። “በተወለደበት መንደር ፊደል ያልቆጠረው ፕሮፌሰር የተባለባት ፣ የሣር ክዳን ቤት ያልነበረው የብዙ ሕንፃ ባለቤት የሆነባት ፣ ለእግሩ ጫማ ያልነበረው ጫማ የለበሰባት ፣ … ለዚህች ለእምዬ አዲስ አበባ እልል በሉላት” ብለዋል ። ንግግራቸው ሁለት ይዘት አለው ። የመጀመሪያው እግዚአብሔር ከመሬት ያነሣል የሚል ነው ፤ ሁለተኛው ከመሬት የተነሣችሁ የመጣችሁበትን አትርሱ የሚለው ጥብቅ መልእክት ነው ። እግዚአብሔር ከመሬት ያነሣል ። ዮሴፍን በስደቱ ፣ በመሸጡ ፣ በወንድሞቹ በመጠላቱ ፣ በሐሰት በመከሰሱ ያልተወው ጌታ የግብጽ ጠቅላይ ሚኒስትር አደረገው ። ወንድሞቹ ቢንከባከቡት ኖሮ ጎበዝ እረኛ ሁኖ ይቀር ነበር ። ቢገፉት የአገር መሪ አደረጉት ። ገፊዎች የሚገፉን ቦታህ እዚህ አይደለም ፣ ከእኛ ጋር ጭቃ አታላቁጥ ብለው ነው ። የገፉት ጧሪ ሆነላቸው ። ለካ የገፋነው በረከታችንን ነበር አሉ ። ዳዊትም ወንድሞቹ የተዉት ፣ የማይፈለግ ፣ አባትና እናት የጣለው ነበር ። እግዚአብሔር በምድረ በዳም ያነጋግራል ። ዳዊት በዱር እያደረ በቤተ መንግሥት ሁኖ ይቃዥ የነበረውን ሳኦልን ያረጋጋ ነበር ። በመጨረሻም የእስራኤል ሁለተኛ ንጉሥ ሆነ ። እግዚአብሔር ከትቢያ ያነሣል ።

ይቀጥላል
ጥምቅት 2 ቀን 2019 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ