መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » የሕፃናት ልብ » የሁልጊዜ ተማሪ

የትምህርቱ ርዕስ | የሁልጊዜ ተማሪ

ሕፃናት መጠየቅ ይወዳሉ ። የሚጠይቅ ትሑት ነው ። መጠየቅ አላውቅም አስረዱኝ ማለት ነው ። ሕፃናት ትሑታን ናቸው ፣ ስለዚህ ይጠይቃሉ ። ከተወለድን ቀን ጀምሮ እስከ ዕለተ ሞታችን ድረስ ትምህርት ቤት ገብተን ብንማር እንኳ የማናውቀው ብዙ ነገር አለ ። እያንዳንዱን ቀን የማወቅ ዕድል አድርጎ የሰጠን እግዚአብሔር ነው ። በሁሉም ነገር ምሉዐን በሁሉም ነገር ጎዶሎዎች አይደለንም ። ራሳችንን ዋጋ የለኝም ማለት አይገባንም ፣ ሌሎችንም አይረቡም ብለን መናገርም ተገቢ አይደለም ። እግዚአብሔር ዋጋ የለሽና የማይረባ ነገርን አልፈጠረም ። እግዚአብሔር ሁሉን ያውቃል ፣ አንድ ነገርን ግን አያውቅም ። የፈጠረውን ትንሽ ሰው አያውቅም ። መጠየቅ አላውቅም ብሎ ማመን ነው ። ያላወቅነው ስላላወቅን ነው ። ያንን ሰው መጠየቅም ሰውዬውን ማክበር ነው ። ገንዘብ ከሌለን ገንዘብ የሚሰጠንን እንወዳለን ፣ እውቀቱ ከሌለን እውቀት የሚሰጠንን ሰው መውደድ አለብን ። በቤታችን አምፑል የሰቀልነው ከራሳችን የሆነ ብርሃን ስለሌለን ነው ። የማይቀበል ሰው የማይሰጥም ወገን የለም ። ወደዚህ ዓለም ስንመጣ በዕራቁትነት ጀምረናልና በወርቅ በካባ እንዳንኮራ ! ወደዚህ ዓለም ስንመጣ ባለ ማወቅ ጀምረናልና መጠየቅን እንዳንፈራ !

ሕፃናት ብዙ ጥያቄዎችን ይጠይቃሉ ። ከጥያቄአቸው አለማቆም የተነሣ ወላጅ እስኪደክመው ድረስ ይጠይቃሉ ። የመጀመሪያው ትምህርት ቤት ቤተሰብ ነውና ጊዜያቸውን ይጠቀማሉ ። መጠየቅ ከመጀመራቸው አስቀድሞ በነበረው አፍ ባልፈቱበት ዘመን በስሜት ሕዋሳቶቻቸው አማካይነት የአንድን ነገር ምንነት ይመረምራሉ ። ያያሉ ፣ ያዩትን ነገር ይዳስሳሉ ፣ የዳሰሱትን ነገር ያሸታሉ ፣ ያሸተቱትን ነገር በጆሮአቸው ያዳምጣሉ ፣ ያዳመጡትን ነገር ይቀምሳሉ ። ሰው ከተወለደ ቀን ጀምሮ ተማሪ ነው ። አንድ ሕፃን እንደ ተወለደ የእናቱን ድምፅ ሲሰማ ወደ እርስዋ ዘወር ይላል ። ይህን ድምፅ ገና በማኅፀን ሳለ ያውቀዋል ። ስለዚህ ሰው ከማኅፀን ጀምሮ የሚማር ፍጡር ነው ። መምህሩ ለማስተማር ቆሞ ከተማሪው የሚማርበት ጊዜ ብዙ ነው ። ሰው ተምሮ የሚያስተምር ፣ እያስተማረ የሚማር ፍጡር ነው ። የዛሬ ሃምሳ በፊት የነበረው እውቀት ዛሬ ላይ ዕድገት አሳይቷል ። ስለዚህ ሁልጊዜ መማር አስፈላጊ ነው ። ጥናት በጥናት ፣ ምርምር በምርምር ሊተካ ይችላል ። በተማርን ቍጥር አእምሮአችን ንቁና ከአዲስ ትውልድ ጋር የምንጓዝ እንሆናለን ። ለትውልድ ባይተዋር ላለ መሆን ሁልጊዜ መማር ያስፈልጋል ። የመርሳት በሽታንም ለመከላከል ሁልጊዜ አንባቢና ከሰዎች ጋር የምንነጋገር መሆን አስፈላጊ ነው ።

በአሜሪካ አገር የሚኖሩ የታወቁት የአለቃ የተሻወርቅ ልጅ በዘጠና አምስት ዓመታቸው 19ኛውን የቻይና ቋንቋ ያጠኑ ነበር ። እኒህ ሰው 18 ቋንቋዎችን ያውቃሉ ። በእርጅናቸው ዘመን ቻይናዎችን እርሳቸው ያሉበት ከተማ ማየት ሲጀምሩ በመንገድ ከእነርሱ ጋር ለማውራትና ለመጠየቅ ቻይንኛ መማር ጀመሩ ። በውጭ አገር የሚኖር አንድ ወዳጄ ዓመታዊ የሒሳብ ሪፖርቱን የሠራችለትን ሴት ታሪክ እየነገረኝ ነበር ። ይህች ሴት ዕድሜዋ 92 ዓመትዋ ነው ። ዕድሜ ከሥራ ፣ ከስፖርት ጡረታ መውጫ አይደለም ። ጡረታን ያመጣው አገር ካገር ለመዞር ወይም ደግሞ ለወጣቱ ትውልድ ቦታ ለመልቀቅ ነው ። እግዚአብሔር የዕድሜ ሰፈፍ ፣ የዕድሜ ገለባ አልሰጠንም ። እስክንሞት ድረስ ሥራ አለን ። እውቀት እንደ ውቅያኖስ ነው ፣ ከዚያ ውስጥ የአንድ ሊቅ እውቀት እንደ አንዲት ጠብታ ነው ። የተማረ ሰው ሁሉን የሚያውቅ ሳይሆን የእውቀትን ጣዕም የቀመሰ ነው ። የተማረ ሰው ገና ሊታወቅ የሚገባው ብዙ ነገር እንዳለ ይረዳል ። ኮሌጆችም እውቀትን የሚሰጡ ሳይሆኑ እውቀትን የምናስቀምጥበትን ፋይል ወይም ሥርዓት የሚያሰለጥኑ ናቸው ። መማር እውቀትን ሲጨምር መጠየቅ ግን የማወቅ ፍላጎትን እየጨመረ ይመጣል ። ፍላጎት ከሁሉ የበለጠ አቅም ነው ። ከኮሌጅ ልንሰናበት እንችላለን ፣ እውቀትን ግን መሰናበት አይገባንም ። እግዚአብሔር ሰፊውን ዓለም የማስተማሪያ ክፍሉ አድርጎ እኛን ያስተምርበታል ። ራሳችን ለራሳችን ትልቅ ጥናት ነን ። አዎ እናቶች እንደሚሉት ሙያ እስኪያረጁ ነው !

አንድ ዛፍ መጀመሪያ ሥሩን ይሰዳል ፣ ሰውም የጥበብ መጀመሪያ የሆነውን ፈሪሀ እግዚአብሔር መያዝ አለበት ። ከተማሪ እጅ ማስታወሻ እንደማይጠፋ ሁሉ ከአዋቂ ልብም ፈሪሀ እግዚአብሔር መጥፋት የለበትም ። አንድ ዛፍ በለጋነቱ ዘመን ቀጥ ብሎ ያድጋል ፣ ሲሸመግል ግን ቅርንጫፉን ወደ ጎን ያሰፋል ። እውቀትም በጥበብ ሲተካ ፣ ዕድሜም ወደ ብስለት ሲቃረብ እውቀታችን ከሰዎች ጋር ስለ መኖር እያስተማረን ፣ ጠቃሚዎች እያደረገን ይመጣል ። ወጣቶች ከሽማግሌዎች መማር ፣ ሽማግሌዎችም ከወጣቶች መማር አለባቸው ። እውቀት ዘመናትን ያጨባብጣል ። ዛሬ ከመምህራን ፣ ከመጻሕፍት እንማራለን ። ነገ ላይ ግን ከስህተቶቻችን ፣ ከውድቀቶቻችንና ከሰዎች ጉዳት እንማራለን ። ጥበብ ሲያድርብን ሁልጊዜ ለመማር እንኖራለን ።

በኬንያ ፕሪሲላ ሲቲንኤ የተባለች የ90 ዓመት አረጋዊት ሴት ትምህርት ቤት ገብታ ፊደል መማር ጀመረች ። የትምህርትዋ ዓላማ መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ ነበር ፣ ደግሞም ለ65 ዓመታት በባሕል ሕክምናና በልምድ አዋላጅነት ሠርታለችና ያንን እውቀትዋን በጽሑፍ ለማስቀመጥ ነው ። ዛሬ በወጣትነታቸው ሁሉም ነገር እንዳለቀ ለሚሰማቸው ሰዎች ትልቅ አርአያ የምትሆን እናት ናት ። ወዳጄ ኃጢአትን በሚመለከት አርጅቻለሁ በል ፣ ዓላማን በሚመለከት ራስህን አታስረጀው ። ጌታችን እንደ ሕፃናት ሁኑ ያለን አዲስ ነገር ለማወቅ ጉጉት ይኑራችሁ ፣ ጠይቁ ፣ ተማሩ ፣ የተማራችሁን ደግማችሁ ለሌሎች ተናገሩ ሲለን ነው ። ያነበብነውንና የሰማነውን ላለመርሳት ከፈለገን ለሌሎች መናገር ትልቁ ዘዴ ነው ።

ይቀጥላል

መስከረም 30 ቀን 2019 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ