የመጣውን መሸከም ሲያቅተኝ ፣ ያልመጣው በስጋት ሲንጠኝ ፣ አፌ እያወራ ልቤ ሲፈራብኝ ፣ ቀኑ የድንጋይ ሸክም ሲሆንብኝ ፣ ዘመን እንደ ሰው ፊቱን ሲያጠቁርብኝ ፣ ንግግሬ ለወዳጆች እሬት ሲሆን ፣ የተናገርኩትን ክፉ ቃል ምነው በመለስኩት ብዬ ስመኝ ፣ ልቤ መሳፈሪያ አጥቶ ሲዋልልብኝ ፣ ባሕሩም መርከቡም ሁሉም ሲያስፈራኝ ፣ መሄድም መቀመጥም ሁለቱም አሳብ ሲያንገላታኝ… አማኑኤል አምላኬ ልብህ አይጽናብኝ!
ምሕረት የሌለው ዘመን ሲመጣ ፣ ሰው ከአውሬ ብሶ መሰሉን ሲበላ ፣ ያሳደጉት ልጅ ዕድሜ ሲቀጥፍ ፣ የሰፈሩለት ከአገር ሲነቅል ፣ ቀንበር በቀንበር ላይ ሲጫን ፣ ሁሉም ጎባጣ ሁኖ የአሽከር ኑሮ ሲገጥመው ፣ ቅንነት ጠፍቶ ትልቁ በትንሹ ሲመቀኝ ፣ ድሀው ቀኑ ጠሮበት መሸሸጊያ ሲያጣ ፣ የበላይ የበታቹን ሲያስጨንቅ ፣ መናናቅ በዝቶ ክብር አገር ለቆ ሲወጣ ፣ ሁሉም ሜዳ ሁኖ መደበቂያ ሲታጣ ፣ የሰው ገመና የሰው እንጀራ ሲሆን ፣ ፈሪው ሲያስፈራራ ፣ ታረቁ ባዩ ሲያጣላ ፣ ጎበዝ መቆም አቅቶት ሲወድቅ ፣ ፍቅርና ይቅርታ የሰውን ኑሮ ሲሰናበት … አማኑኤል አምላኬ ልብህ አይጽናብኝ !
የወደዱት ሲያቆስል ፣ የጠሉት ሲስም ፣ ልጅ ባላጋራ ሲሆን ፣ በሰላም መሞትም ሲናፍቅ ፣ የልብን የሚያወሩት የልብ ሰው ሲጠፋ ፣ ሐቀኛ እየተራበ ሌባው ሲፋፋ ፣ ሽበት ተደፍሮ የዕድሜ ድሀ ሲንሰራፋ ፣ ፍቅር በሽሽግ ኖሮ ጠብ በገሀድ ሲወጣ ፣ የገባው ልውጣ እያለ ያልገባ ለመግባት ሲጋፋ ፣ የውሸት መሳሳም እየበዛ ፣ ጠብም ልክ ሲያጣ ፣ አወዳሽ ተወዶ ሕመምን የሚነግር እንደ ጠላት ሲታይ ፣ ተሸካሚው ላይ ሌላ ሸክም ሲጫን ፣ ኃጢአት ከአሸዋ ሲበዛ ፣ ግፍ ገደቡን ስቶ ሲፈስስ ፣ የጠገበ የራበውን ማየት ሲሳነው… አማኑኤል አምላኬ ልብህ አይጽናብኝ!
የቀን እንጂ ያንተ አማኝ መሆን ሲሳነኝ ፣ ባልተጨበጠ ነገር መዝለል ሲቃጣኝ ፣ ብዙ ያወራሁለት ነገር እንደ በረዶ ሲሟሟብኝ ፣ ፍቅርን ስፈራ ጠብም ሲረብሸኝ ፣ ዛሬን ሳልኖራት ነገ ስታውከኝ ፣ ሰው እንደ እኔ መሆኑን ረስቼ ያሻኝን ስናገር ፣ ዕድሜ ለእገሌ ያልኩለት ወገን ዕድሜዬን ሲያሳጥር ፣ በማውቀው ነገር ውስጥ የማላውቀው ሲበዛብኝ ፣ የጠላሁትን ጥሉልኝ ብዬ አገር ካገር ስዞር ፣ የከበደኝን ሸክም ለሌላው ሳሸክም ፣ የእኔ የሆነውን ማንም አይመልከትብኝ ስል ፣ የሌላውን የእኔ እንደሆነ ሳስብ… አማኑኤል አምላኬ ልብህ አይጽናብኝ !
በመጣው በረከት ማመስገን ሲሳነኝ ፣ ያልመጣውን ክፉ ነገር ገምቼ ስታወክ ፣ አንተን ትቼ ቀኑን ስፈራ ፣ የሚያስፈራኝን ባንተ መርታት ሲያቅተኝ ፣ ቀን እያለኝ ቀን ስጠብቅ ፣ ለጽድቅ ቀጠሮ ለኃጢአት አሁንን ስመድብ ፣ ማን ነኝ ከማለት ማነው ማለት ሲቀናኝ ፣ ቀንና ሌሊት በሰው ኑሮ ውስጥ ስውል ሳድር ፣ ስጠግብ ሁሉ የጠገበ ሲመስለኝ ፣ ሳገኝ ቤትህን ስረሳ ፣ ጤነኛ ስሆን ስዘል ፣ ስታመም ስፈልግህ ፣ ስእለቴን ስረሳ ፣ በልቼ ሳኮርፍ … አማኑኤል አምላኬ ልብህ አይጽናብኝ !
አገሬ አገሬ ላይ ስትናፍቀኝ ፣ ወገን እያለኝ እንደ ሌለኝ ሲሰማኝ ፣ ሁሉ እያለኝ ሁሉ እንደሌለኝ ስሆን ፣ ማሩ እየመረረኝ ፣ ላኖረኝ ፍቅርህ ምስጋና ሲያጥረኝ ፣ ያላንተ የኖርኩበትን ዘመን ስቃዩን ስረሳ ፣ ማገልገልን ትንሽ ድርሻ አድርጌ ስመለከት ፣ መኖሬን ረስቼ ስለ መኖሪያው ሳማርር ፣ በሌለህበት ስፍራ ስፈልግህ ፣ ባለህበት ቦታ ስሸሽህ… አማኑኤል አምላኬ ሆይ ልብህ አይጽናብኝ ። መንገዱን በጠዋት ጀምሬ እስከ ምሽት አልደረስኩም አማኑኤል ሆይ በተላላነት ከመቅረት እባክህ አድነኝ ።
አሜን !
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሐምሌ 30 ቀን 2018 ዓ.ም.