መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » ቅድስት ማርያም » ቅድስት ማርያም -7

የትምህርቱ ርዕስ | ቅድስት ማርያም -7

ወላዲተ አምላክ

ቅድስት ኤልሳቤጥ ድንግል ማርያምን ባየች ጊዜ፡- “የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል?” በማለት ደስታዋን ገለጠች (ሉቃ. 1 ፡ 43) ። ቅዱሳን ወደሚሄዱበት ሁሉ ደስታን ይዘው ይጓዛሉ ። የእግዚአብሔር ሰው ወደ ቤታችን ሲመጣ በረከት አብሮ ይገባል ። እግሮቻቸው ርጥብ መሆናቸውን መጽሐፍ ይናገራል ። “መልካሙን የምሥራች የሚያወሩ እግሮቻቸው እንዴት ያማሩ ናቸው” ይላል (ሮሜ. 10 ፡ 15) ። ውበት ፣ ማማር የሚለካው በፊት ገጽታ ነበር ፣ አሁን ግን እግሮቻቸው እንደሚያምሩ ይናገራል ። የእግዚአብሔር ሰው ደራሽ ነውና ማማሩ በእግሩ ይለካል ። ነቢዩ ኤልያስ ወደ ሰራፕታዋ መበለት ቤት ቢገባ የረሀቡን ዘመን በበረከት አለፈችው ፣ ነቢዩ ኤልሳዕ ወደ ሱነም ሴት ቤት ቢገባ ልጅ አገኘች ፣ ልጅዋም ቢሞት በተአምራት ተነሣ ። የእግዚአብሔር ሰዎች ቤታችንን እንዲረግጡት መመኘት ይገባል ። ቅድስት ማርያምም ኤልሳቤጥን ብትጎበኛት በኤልሳቤጥ መንፈስ ቅዱስ ሞላባት ። “ኤልሳቤጥም የማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ ፅንሱ በማኅፀንዋ ውስጥ ዘለለ፤ በኤልሳቤጥም መንፈስ ቅዱስ ሞላባት” ይላል ። (ሉቃ. 1 ፡ 41) ። በነቢዩ በኤልያስ ከተገኘው በረከት በቅድስት ማርያም የተገኘው በረከት በለጠ ። ነቢዩ ጸጋውን አካፈለ ፣ በቅድስት ማርያም ሰላምታ ግን መንፈስ ቅዱስ በኤልሳቤጥ ላይ ሞላባት ። ጸጋው ሳይሆን ባለጸጋው መጣ ።

ያቺ ቃልን የፀነሰች ድንግል ሰላምታዋ እንዴት ያለ የሰላም ወንዝ ያለበት እንደሆነ እንገነዘባለን ። ሰላም ያለው ሰላም ይሰጣል ። የእግዚአብሔር ሰዎች ወደ እኛ ሲመጡ እንረጋጋለን ። ዓለም በጥድፊያ ዕድሜአችንን ልትቀጭ ስታዋክበን ምን እየሆንሁ ነው ብለን እንድናስብ የሚያደርገን የእግዚአብሔር ሰዎችን ማግኘት ነው ።

ለቍጥር የሚያታክቱ አዋጆች ፣ ሕጎችና መመሪያዎች ይወጣሉ ። በምድር ላይ ያለው ሕግ ከሰው ቍጥር ሊበዛ ነው ። መንግሥታት ሕጎችን የሚያበዙት የሰውን አእምሮ ለመቆጣጠር ነው ። ሰው በእምነትና በፍርሃት መካከል የሚኖር ፍጡር ነው ። የየዕለት ተጋድሎአችንም ከዲያብሎስ ጋር በቀጥታ ሳይሆን ከፍርሃት ጋር የሚደረግ ገድል ነው ። የፋሽን ኢንዱስትሪዎች አእምሮአችንን በምኞት ሊቆጣጠሩት ይፈልጋሉ ። የቴሌቪዥኑ መስኮት ሁሉም ሰው እየሮጠ መሆኑን በማሳየት አንተ ብቻ ቀርተሃል ይለናል ። የሚፈበረኩ ጦርነቶች ፣ ዓለምን የተቆጣጠሩት ጥቂት ነጋዴዎች ፣ የኢኮኖሚው መወላወል እነዚህ ሁሉ ዕረፍት እየነሡን ልንቸገር እንችላለን ። በየሰዓቱ የሚመጡት የጤና መረጃዎች ከጥንቃቄ ይልቅ ለፍርሃት ይዳርጉናል ። በዚህ ውስጥ የምንረጋጋው የእግዚአብሔር ሰዎችን ስናገኝ ብቻ ነው ። የእግዚአብሔር መዓዛ ያረፈባቸው ሰዎች በመናገራቸው ሳይሆን በመገኘታቸው ብቻ ያረጋጋሉ ።

ቅድስት ማርያም ወላዲተ አምላክ ወደ ኤልሳቤጥ ቤት በመሄድዋ በዚያ ቤት በረከት ሆነ ። የሄደችው አምላክን ተሸክማ ነው ። ቅዱስ አግናጥዮስ ራሱን “ቲኦፎሮስ” እያለ ይጠራ ነበር ። በግሪክ ቋንቋ ሁለት ዓይነት ፍቺ አለው ፤ እግዚአብሔርን የተሸከመና እግዚአብሔር የተሸከመው ማለት ነው ። ጌታችን በማቴ. 18፡2-3 ጠርቶ የተሸከመው ሕፃን አግናጥዮስ እንደ ነበር የጥንትዋ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት ይነግረናል ። ስለዚህ አግናጥዮስ እግዚአብሔር የተሸከመው ይባላል ። እግዚአብሔርን የተሸከመ ሲባልም በአሳቡ በምኞቱ ሁሉ ጌታውን ይዞ የሚዞር ማለት ነው ። እመቤታችን ከአግናጥዮስ ይልቅ መናገር ትችላለች ። ምክንያቱም አምላክን ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በጠባብ ማኅፀን ተሸክማለችና ።

ቅድስት ኤልሳቤጥ እግዚአብሔርን የምታመልክ ሴት እንደ ነበረች ተመስክሮላታል ። ይህች ቅድስት “የጌታዬ እናት” ብላ ቅድስት ማርያምን ስትጠራ የኤልሳቤጥ ጌታ እግዚአብሔር መሆኑን እናውቃለን ። ስለዚህ እመ እግዚአብሔር ጸባዖት – የአሸናፊው የእግዚአብሔር እናት ብላ እየጠራቻት ነው ። ከድንግል ማርያም የተወለደው እግዚአብሔር ነው ። ጌታ የሚለው አጠራር በግሪክ “ኪርዮስ” በዕብራይስጥ “አዶኒ” የሚል ሲሆን ይህ ስያሜ በቀጥታ የሚሰጠው ለአምላክ ብቻ ነው ። ስለዚህ የጌታዬ እናት ማለት የአምላኬ እናት ማለት ነው ። ኤልሳቤጥም በራስዋ እውቀት ሳይሆን በሞላባት መንፈስ ቅዱስ የጌታዬ እናት ለማለት በቅታለች ። በሥጋዊ ዝምድና በዕድሜ የምትበልጥ ቢሆንም አሁን ግን ቅድስት ማርያም እንደምትበልጣት አወቀች ።

ጌታ ሲወለድ የወጣለት ስም አማኑኤል የተሰኘ ነው ። አማኑኤል ማለት እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ማለት ነው ። ሥጋ የለበሰው እግዚአብሔር ባይሆን ኖሮ አማኑኤል አይባልም ነበር ። ደግሞም እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ነኝ ብሎ ሲናገር በብዛት እናነባለን ። አማኑኤልን ልዩ የሚያደርገው ከሥጋችን ሥጋ ከነፍሳችን ነፍስ ነሥቶ የእኛ ዘመድ መሆኑ ነው ። ለቅድስት ማርያም ከተሰጡ ስያሜዎች አንዱ “ወላዲተ አምላክ” የሚለው ነው ። አምላክን የወለደች ማለት ነው ። ወላዲተ አምላክ ብለን እርስዋን ስንጠራ ኢየሱስ ጌታችንን አምላክ መሆኑን እየመሰከርን ነው ። ወላዲተ አምላክ ብለን ቅድስት ማርያምን መጥራት የክርስቶስን ክብር ማጉላት ነው። ወላዲተ አምላክ የሚለው የነገረ መለኮት ትምህርት ፣ የታሪክም ምስክርነት ያለው ነው ። በግሪኩ ቴኦቶኮስ በግእዙ ወላዲተ አምላክ ተብላ ትጠራለች ፣ አምላክን የተሸከመች ማለት ነው ። በ431 ዓ.ም. በኤፌሶን የተደረገው ጉባዔ ወላዲተ ሰብእ – የሰው እናት ነች ብሎ ለተናገረው ለንስጥሮስ ወላዲተ አምላክ መሆኑንዋን መስክሮአል ። በዚህም ሊቁ ቅዱስ ቄርሎስ ሲታወስ ይኖራል ።

የወላዲተ አምላክ በረከት ከሁላችን ጋር ይሁን !

ይቀጥላል

ነሐሴ 15 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ