መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » ከተማይቱን አይቶ አለቀሰላት » ከተማይቱን አይቶ አለቀሰላት -1

የትምህርቱ ርዕስ | ከተማይቱን አይቶ አለቀሰላት -1

“ከተማይቱን አይቶ አለቀሰላት” ሉቃ. 19፡41 ።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ኢየሩሳሌም የመጨረሻ ጉዞውን ሲያደርግ በአህያ ውርንጫ ተቀምጦ ነበር ። ይህም ሦስት ነገሮችን ይገልጣል ። የመጀመሪያው ንጉሠ ሰላም መሆኑን ነው ። ሰላም የእግዚአብሔር መለኮታዊ ገንዘብ ናት ። ሰው ከራሱ ፣ ከጎረቤቱና ከእግዚአብሔር ጋር ሰላም ሊኖረው ይገባል ። የሰላም መሠረቱ ከእግዚአብሔር ጋር ያለ ስምምነት ነው ። ከእግዚአብሔር ጋር ስንታረቅ ከራሳችንና ከጎረቤታችን ጋር እንታረቃለን ። ከራሱና ከጎረቤቱ ጋር የተጣላ ዓለም ተፈጥሮአል ። በውስጣቸው የሞቱ ሰዎች ሌሎችን ለመግደል አይሳሱም ። ጌታችን የመጣው በራስ ወዳድነት ፣ በስግብግብነት ፣ በፍቅረ ንዋይ ፣ በትዕቢትና በእኔነት አምልኮ የሄደውን ሰላም ሊመልስ ነው ። ሰዎች ለሰላማቸው የሚሆነውን አያውቁም ። ስለ ዕፅዋት ምርምር ፣ ስለ ህዋ ሳይንስ ፣ ስለ በረራ ቴክኖሎጂ ፣ ስለ ተለያዩ ማሽኖች እውቀት አግኝተው ለሰላማቸው የሚሆነውን ግን አላወቁም ። ሰላም በተቀጠረ ከተማ በመኖር ፣ ጥብቅ አጥር ባለው ቤት ውስጥ በማደር ፣ ገንዘብን ሳይሳሱ መበተን በመቻል አይገኝም ። ሰላምና ደስታ ዱርዬዎች አይደሉምና በየመሸታ ቤቱ መፈለግ ሊያበቃ ይገባዋል ። ጌታችን ለኢየሩሳሌም የመጨረሻ መልእክት እንዲሆን ንጉሠ ሰላም ሁኖ በአህያ ላይ ተቀምጦ መጣ ። ይህ ታሪካዊ ምልክት ፣ የተለመደ የትእምርታዊ ትምህርት ነው ። ሰላም መምጣቱን ለማብሰር የእስራኤል ነገሥታት በአህያ ተቀምጠው በሕዝቡ መካከል ይመላለሱ ነበር ። ጦርነት መኖሩን ለመግለጥ ደግሞ በፈረስ ላይ ተቀምጠው ይመላለሱ ነበር ።

ጌታችን ለሦስት ዓመታት በትምህርቱ የሰላምን መገኛ ተናገረ ። ስላልሰሙት በመጨረሻ በሚያውቁት ምልክት በአህያ ተቀምጦ መጣ ። አሁንም አልገባቸውምና አለቀሰላቸው ። “ለሰላምሽ የሚሆነውን በዚህ ቀን አንቺስ ስንኳ ብታውቂ ፤ አሁን ግን ከዓይንሽ ተሰውሮአል” አለ (ሉቃ. 19 ፡ 42) ። ለሰላምዋ የሚበጃት ክርስቶስ ነበረ ። ይህ ቀን የመጨረሻው ዕድል ነው ። የሚፈልጉት ዕቃ ፊት ለፊት እያለ ከዓይን እንደሚሰወር ፣ መነጽሩን አድርጎ መነጽሩን እንደሚፈልግ መምህር ክርስቶስ የተሰወራት ከተማ ነበረች ። በሩቅ ዘመን ትፈልገዋለች እርሱ ግን በቃና ሰርግ ፣ በአልዓዛር መቃብር የሚገኝ አባልዋ ሁኖ ነበር ። ዕድልና ዕድለኞች አልተገናኙም ። ካጣ ሰው ይልቅ እያለው ያላወቀበት በጣም ያሳዝናል ። ብዙ ሰዎች ደግ የሚሆኑት ለራሳቸው ክፉ ሆነው ነው ። ለእነርሱ ዝሙት ለቤተሰባቸው ጠቦት ያዛሉ ። ለእነርሱ የአልኮል መጠጥ ለልጆቻቸው ወተት ይገዛሉ ። ኢየሩሳሌም ለሌላው መልስ የሚሆን ብዙ ብሥራት ነበራት ፣ ለራስዋ ግን አላወቀችበትም ። ታላቁን የእግዚአብሔር በግ አርዳ ዓለም ሁሉ ሲጠግብበት እርስዋ ግን በመንፈሳዊ ረሀብ ትኖራለች ።

ጌታችን በአህያ ጀርባ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም መግባቱ የተናቁትን እንደሚያከብር ያሳያል ። ሰዎች የሚያገለግላቸውን አህያ ይንቃሉ ፣ የማያገለግላቸውን አንበሳ ያከብራሉ ። ሰዎች የምትሸከማቸውን አህያ ያቃልላሉ ፣ የሚሰብራቸውን አንበሳ ያከብራሉ ። ሰዎች ሲሄዱ ጭነቱን ሲመለሱ እነርሱን የምትሸከመውን አህያ የስድብ ድምፅ ያደርጓታል ፣ ቍጡውን አንበሳ ለጎበዞች ማበረታቻ ያደርጉታል ። የናቁትን “አህያ” ፣ ያከበሩትን “አንበሳ” ይሉታል ። ሰው አገልጋዩን አያከብርም ። ምግባችንን ሠርተው የሚሰጡን የቤት አገልጋዮች ናቸው ፣ የምናከብረው በጉቦ የሚያራቁቱ ሹሞችን ነው ። ሬሳችንን የሚሸከሙ ድሆች ናቸው ፣ የምንኖረው በሞታችን ቀን ለማይመጡት እኩያ ወዳጆች ነው ፤ የእኛን ቆሻሻ መጥተው ለሚያነሡ ክብር የለንም ፣ ራሳቸውን የሚያመጻድቁትን ግን በግድ ካልጋበዝን እንላለን ። የትዕቢት ስፖንሰር ነን ። እግዚአብሔር የተናቁትን ያከብራል ። አህያ በበለዓም ታሪክ ውስጥ ጎልታ ወጥታለች ። ከፊት ለፊት ያለውን አደጋ ነቢይ ነኝ የሚለው አልተገነዘበም ፣ አህያዋ ግን ታይቷታል (ዘኁ. 22)። የሚመጣውን አደጋ ከባለጠጎች ይልቅ ከሹሞችም በላይ ድሆችና የተናቁ ምሁራን ያውቃሉ ። የሚሰማ ግን የለም ። “ምክር ከድሀ ነበርሽ ፣ ማን ቢሰማሽ” ተብሏል ።

ጌታችን በአህያ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም መግባቱ ትሕትናውን ያሳያል ። ትሑት ማለት የተናገረውን የሚኖር ማለት ነው ። ጌታችን “የሚያለቅሱ ብፁዓን ናቸው” አለ ፣ ራሱ አለቀሰ ። እውነተኛ ትሑታን ስለ ጥፋታቸው የሚያዝኑ ናቸው ። ኢየሩሳሌም በጥፋትዋ ትስቃለች ፣ ጌታ ግን አለቀሰላት ። ኢየሩሳሌም በአሁን ደስታ ተይዛለች ። ትዕቢትና ጭፍንነት ሲመጣ የሚመጣውን ማየት ያቅታል ። የሚሠሩት ቤት ላይፈርስ የተሠራ ፣ የመጣው ሀብት ላይናድ የተከማቸ መስሎ ይታያል ። መጪውን ውድቀት እያሰቡ ትሑት መሆን ከትዝብትም ከኵነኔም ያድናል ። ጌታችን ለማታለቅሰዋ ከተማ አለቀሰላት ። ኖኅ የሚመጣውን ጥፋት እያሰበ ይጮኽ ፣ ይሰብክ ፣ ያዝን ነበረ ። ብዙዎች ግን ያላግጡበት ነበር ። ጌታችንም ለኢየሩሳሌም ጥፋት ሲያለቅስ ብዙዎች ይገረሙ ነበር ። እርሱ ግን “ሰማይና ምድር ያልፋል ቃሌ ግን አያልፍም” አለ ። ይህ አጽንኦታዊ ንግግር ስለ ኢየሩሳሌም የተናገርኩት በርግጥ ይሆናል ማለቱ ነው ። ትሕትና ስለ ሌሎች ውድቀትም ማዘን ነው ። ሳሙኤል ነቢይ ስለ ንጉሡ ሳኦል ያለቅስ እንደ ነበረ ዛሬም ከክብር ስለ ወደቁት ሰዎች መፍረድ ሳይሆን ማልቀስ ይገባል ። ኢካቦድ ክብር ከአገር ለቀቀ ብሎ ማልቀስም የደጉ ሰው ምልክትና የትሕትና መገለጫ ነው ።

ይቀጥላል
ነሐሴ 18 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ