እንኳን ከ2018 ዓ.ም. ዘመነ ማርቆስ ወደ 2019 ዓ.ም. ዘመነ ሉቃስ በሰላም አሸጋገራችሁ!
ከቤቴ እንደ ተመላለስህ አውቃለሁ ፣ በገዛ ቤትህ በር ዘግቼብህ ብዙ ጊዜ መልሼሃለሁ ። ተንከባካቢ ካህን ፣ አሳዳጊ አባት ፣ መካሪ መምህር ብትሰጠኝ ኩራቴን ከፍ አድርጌአለሁ ። እግዚአብሔር ያስፈልገኛል ከማለት ለእግዚአብሔር አስፈልገዋለሁ ወደሚል እቡይነት አድጌአለሁ ። ሳኮርፍ የሚያባብሉኝ ፣ ስሸሽ የሚከተሉኝ ፣ ስጠፋ የሚፈልጉኝ ፣ በነጻ የሚወዱኝን እንደ ላክልኝ አውቃለሁ ። ሁልጊዜ ፀሐይ ፣ ሁልጊዜ ወዳጅ አይኖርምና ይህን ምሥጢር አጥቼዋለሁ ። የዕውር ሽፍታ ሆኜ ጓሮ ስደበቅ ፣ የበዳይ አኩራፊ ሆኜ ያዙኝ ልቀቁኝ ስል ፣ እንደ ጅራፍ ገርፌ መልሼ ስጮህ ሳትታዘብ ና ወደ እኔ እንዳልከኝ አውቃለሁ ። አገር ምድሩን ፣ ዘመድ ወዳጁን እንዳደከምሁ ፣ ምነው መሐን በሆንኩ እስኪሉ ወላጆቼን እንዳስመረርኩ ፣ አገልጋዮችን ተስፋ እንዳስቆረጥሁ አውቃለሁ ። አሳቤን አጽድቅልኝ እንጂ አሳብህ ይግዛኝ እንደማልል ፣ ዓይቼ መርገጥ አቅቶኝ ረግጬ እንደማይ ፣ ሁልጊዜ የእንባ ኑሮን ከምርጫዬ እንደምቀበል አውቃለሁ ። ለኃጢአት እየሳቅሁ ለጽድቅ የማለቅስ ፣ ሰው ሲጠራኝ ፈጥኜ መልስ የምሰጥ ፣ አንተ ስትጠራኝ ደግሜ የማስብ እንደሆንሁ አውቃለሁ ። ለአገልግሎት ደጋግሜ የማስበውን ለኃጢአት ባስብ ኖሮ የጸዳ ሕይወት በኖረኝ ነበር !
ለምድራዊ እንጀራ ብዙ ዓመታት የተማርሁ ፣ ለዘላለም ሕይወቴ ግን እውቀትን የጠላሁ ፣ ሥነ ምግባሬን አፍርሼ ቤት መሥራት የሚያምረኝ ፣ ጥላቻ ዘርቼ ያደገች አገር የምፈልግ እንደሆንሁ አውቃለሁ ። እባክህን ይህችን ዓመት ተወኝ ። ስለ እኔ ከእኔ መስማት ፣ ከሰው ማሰስ አያስፈልግህም ። ታውቀኛለህ ፣ ልቤም ሥራዬን ያውቀዋል ። ባንተ ምድር ተተክዬ ፍሬ አልባ ነኝ ። ያምናውን ስህተት ዘንድሮም እደግማለሁ ፣ የምርጫዬ ውጤት ዕድሜን ቢበላውም አሁንም በጽናት እሳሳታለሁ ። ደፋር መሃይም ነኝ ፣ ሽቅብ ሊቅ የማርም ፣ አባት የምሰድብ ነኝ ። ቢሆንም እባክህን ይህችን ዓመት ተወኝ ። ይህችን ዓመት ተወዉ እያሉ ስለ እኔ ብዙ ዘመን የለመኑህ አሉ ። ለሚመጣው ዓመት ግን እኔ ልለምንህ ፣ እባክህን ይህችን ዓመት ተወኝ ። ከእኔ በጎ አላገኘህምና እንደ አሳብህንም አልሆንሁምና የኪሣራ በጀት ያዝልኝ ።
የተስተካከለ አገር እንዲኖረኝ እፈልጋለሁ ፣ የተስተካከለ ሕይወት ግን የለኝም ። አገር ማለት የእኔና የወንድሜ ድምር መሆኑን አላውቅም ። ቤተ ክርስቲያን እኔ መሆኔን ዘንግቼ ቤተ ክርስቲያን እንድትዋብ እሻለሁ ። ያማረ ቤት እንዲኖረኝ እፈልጋለሁ በቤት ውስጥ የሚያረጋጋኝን ሰላም ግን ጥያለሁ ። የተቀደሱ ልጆችን እፈልጋለሁ ፣ የእኔን አርአያ እንደሚከተሉ ግን ረስቻለሁ ። የተሳከርኩ ልጅህ ነኝ ፣ እባክህን ይችን ዓመት ተወኝ ። ቁረጠው ብለህ ቀሳፊ መልአክን አትስደድብኝ ፣ አይጠቅምም ብለህ ተስፋ አትቍረጥብኝ ። በልቤ ጸድቄ እንደ ጨረስኩ በእግሬ ግን ገና እንዳልጀመርሁ ታውቀው የለ ። አሳብ ከውለታ የማይቆጠረው በሰው ዓለም ነውና እባክህን ይችን ዓመት ተወኝ ። ሰው እንዳይለየኝ ብዙ ማባበያ አለኝ ፣ የሚጠሉኝ ላይ እልህ ይዞኝ እከታተላለሁ ። መንፈስህን አታርቅብኝ ብዬ መለመን ግን ዘንግቻለሁ ። አንተን ማጣት አያስፈራኝምና እፈራለሁ ። እባክህን ይችን ዓመት ተወኝ ።
ባልተገረዘ ልብ የተቀበሉት ዓመት ሸለፈታም ነው ። ያለ ዘር የተቀበሉት ዓመት ፍሬ የለውም ። በንዴት የተቀበሉት ዓመት ነጎድጓዳማ ነው ። ልቤን የአሳብ ሥርዓት ስጠው ። ሕግህ መረንነቴን ያርቀው ። ነፍሴ መንግሥት እንደሌለባት ከተማ ታውካለች ፣ እባክህን ይርጋ በላት ። በነጻ ተሰጥቶኝ የሄደውን በዋጋ ፈልጌ አጣዋለሁ ። ስለ ዝናብ ለማመስገን ፣ ስለ ፀሐይ መውጣት ለመደነቅ ገና በሳል አይደለሁም ። በነጻ ስለምምገው አየር ውዳሴ ለማቅረብ ዛሬም አላደኩኝም ። ከማን ጋር እንደ ማማህ ፣ በአረማውያን ኑሮ እንደምቀና ፣ የሞቱት ታድለዋል እንደምልህ ታውቀዋለህ ። የተሰጠኝን ትቼ ያልተሰጠኝን እንደምፈልግ ፣ ሁሉን ለእኔ እያልኩ እንደማታክትህ ታውቀዋለህ ። ለልቤ ልብ ከሰጠኸው ይችን ዓመት ተወኝ ። ቅዱሳንን እያከበርሁ ቅዱስ መሆን አልፈልግም ፣ በሰማዕታት እየተደነቅሁ ለሆዴ አድራለሁ ። ፍቅር የሚለው ቃል ከምላሴ ጫፍ ላይ ጠፍቶ አያውቅም ፣ ፍቅር ግን የለኝም ። እንደገና አፍርሰህ ከሠራኸኝ እባክህን ይችን ዓመት ተወኝ ።
ከማኅፀን ጀምሮ የጥይት ድምፅ ስሰማ ነበረ ። ይህች ናት አገሬ ብዬ ለመኩራት ሳስብ ታሪክዋና የዛሬው ሁናቴዋ ይዘባረቅብኛል ። የቅዱሳን አገር እኔን የመሰለ ጃርት አብቅላለች ። የሰላም መሣሪያ ከመሆን የእልቂት አዋጅ ነጋሪ ሆኛለሁ ። እራሴን እየዋሸሁት የእኔ ንጹሕ ዘር ይህ ነው እላለሁ ። ሰማይ በማያደርስ ቋንቋ እናቆራለሁ ። እንኳን ቋንቋው ምላሴም አንድ ቀን እንደሚታሰር እዘነጋለሁ ። የወዳጆች ውለታን ረስቻለሁ ፣ ቂምን ግን አልረሳሁም ። በጎ ላደረጉልኝ በጎ ሳልመልስ ፣ ክፉ ለዋሉብኝ በቀል ለመመለስ እባጅታለሁ ። ማደጌ ሌላውን ለመርገጥ ፣ ከፍ ማለቴም ለጭካኔ ሆነብኝ ፤ አውራ እንደ ሌለው ንብ አሳቤ ይነጉዳል ፣ አዛዥ እንደሌለው ሠራዊት አካሌ ይሸፍታል ። ፍርሃቴን ፣ የገዛ አገሬን መስጋቴን ወደ ኋላ አስቀረውና አሻግረኝ ። አሳቤ አሳብ ብቻ ሆኖ እንዳይቀር ፣ የተመኘሁትን መልካም እንዳይ ፣ ለዋለልኝ እጅህ እንድኖር እባክህን ይችን ዓመት ተወኝ !
መስከረም 1 ቀን 2019 ዓ.ም.