መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » ፍቅር » እግዚአብሔር ፍቅር ነው

የትምህርቱ ርዕስ | እግዚአብሔር ፍቅር ነው

እግዚአብሔር ምሉዕ አካል አለው ፣ ፍቅርም ስሜት አይደለም ። እግዚአብሔር ዘላለማዊ ነው ፣ ፍቅርም ከሁኔታ በላይ ነው ። እግዚአብሔር የቦታ ዳርቻ የለበትም ፣ ፍቅርም ሁሉን ይወዳል ። እግዚአብሔር ብርሃን ነው ፣ ፍቅርም በእውነት ላይ ይመሠረታል ። ዓለም “ፍቅር ዕውር ነው” ይላል ፣ ይህ ቃል ለእውነተኛው ፍቅር ገላጭ አይደለም ፣ ለስሜት ስካር የሚነገር ነው ። እግዚአብሔር ትሑት ነው ፣ ፍቅርም ዋጋ ይከፍላል ። የሰው ፍቅር ተወዳጁ ባለው ነገር ላይ ይመሠረታል ። በመልኩ ቅላትና ጠይምነት ፣ በቁመቱ መርዘምና ማጠር ፣ በገንዘቡ ብዛትና በአነጋገሩ ማራኪነት ላይ ይመሠረታል ። ከእነዚህ ነገሮች አንዱ ሲጎድል የወደድነውን መጥላት እንጀምራለን ። እግዚአብሔር ግን የሚወደው እኛነታችንን ነው ። እርሱ የነፍሳችን ወዳጅ ነው ። እነዚህ ሁሉ መስፈርቶች የፍቅር መሠረት መሆን አይችሉም ። የእግዚአብሔር ፍቅር በራሱ በእግዚአብሔር ላይ ይመሠረታል ። የሚወደድ ሰው ቀርቶ የሚወደድ ማንነት የለንም ። ሰውንም ራሳችንንም የምንቀበለው በእግዚአብሔር ነው ። እግዚአብሔር በራሱ የፍቅር ባሕርይ ላይ ተመሥርቶ ያለ መስፈርት ይወደናል ። ይህ ፍቅር በማግኘት በማጣት አይለወጥም ።

እግዚአብሔር እንዲወደን ብለን የምናደርገው ጥረት የለም ። እግዚአብሔር ፍቅር ስለሆነ ይወደናል ። የወደደን ስለወደድነው አይደለም ፣ እንኳን እግዚአብሔር ወላጆቻችን እንኳ የወደዱን ስለወደድናቸው አይደለም ። እግዚአብሔር ስለ ወደደን እንወደዋለን ። እኛ ጠላቶች ሳለን አፍቅሮናል ። የፍቅር መነሻው ፣ በመውደድ ቀዳሚው እግዚአብሔር ነው ። ይህ ፍቅር በእርሱ ዘንድ በምልአት ይኖራል ፣ በእኛ ዘንድ ግን በከፊል ይገኛል ። ፍቅር ጸጋ ነው ፣ ፍቅር ፍሬ ነው ፣ ፍቅር እምነት ነው ፣ ፍቅር ምግባር ነው ፣ ፍቅር መሥዋዕትነት ነው ። ፍቅር የጸጋዎች ጸጋ ፣ የስጦታዎች ራስ ነው ። “ወዶኛልና አዳነኝ” የሚለው ዝማሬ ወደነዋልና አዳነን ብለን ልንለውጠው አንችልም (መዝ. 17፡19) ። ፍቅርም ማዳንም የእርሱ ነው ። ልናድናቸው የምንፈልጋቸው ሰዎች ካሉ ካልወደድናቸው አናድናቸውም ። ፍቅር ሌላውን የመታደግ ጉልበት ይሰጠናል ። በዓለም ላይ ያለው የመጨረሻው ቍስል በፍቅር ይታከማል !

ፍቅር ቀጣይ ተግባሩ ማዳን ነው ። አንድን ሰው ስንወደው አለማወቁን ፣ ስንፍናውን ፣ ሙያ የለሽ መሆኑን ፣ ረሀቡን ፣ ብቸኝነቱን እናድናለን ። በእውነት ይህን ካላደረግን መኖር ያን ያህል ትርጉም የለውም ። እግዚአብሔር የወደደንን ያህል መውደድ ቀርቶ ምን ያህል እንደ ወደደን ካወቅን በቂ ነው ። ደካሞች ሳለን ወደደን ። ሁላችንም ደካማ ያሳዝነናል ፣ መውደድ (ዋጋ መክፈል) ግን እንቸገራለን ። እግዚአብሔር ግን የወደደን በርትተን አይደለም ። ቆፍጣናን ፣ ጀግናን እንወዳለን ። እግዚአብሔር ግን ገና ደካማ ሳለን ወደደን ይላል (ሮሜ. 5 ፡ 6) ። በደል አቁመን ሳይሆን አሁንም እያሳዘነው ወደደን ። ሲኦል የምንለው ከዚህ ፍቅር ተለይቶ መውደቅ ነው ። በራችንን ዘጋን ማለት ፀሐይ ጠለቀች ማለት አይደለም ። ሰው ራሱን ሲኦል ቢያገኘው እግዚአብሔር ጠላው ማለት አይደለም ። ደካማ ፣ ስንኩል ፣ ብላሽ ፣ እንኳን በጉዞአችን በወንበራችን የምንወድቅ ሳለን እግዚአብሔር ወደደን ።

የእስራኤል ታዋቂ መዝሙር አለ ። የአይሁዶች የማለዳ ፣ የበዓላት መዝሙራቸው “ምሕረቱ ለዘላለም ነውና” የሚለው ነው (መዝ. 135) ። ፍቅሩ ለዘላለም ነውና ማለት ነው ። የነጋው ምሕረቱ ለዘላለም ስለሆነ ነው ። ስናቆም ቢያቆም ኖሮ አይነጋም ነበር ። ዓመቱን ያሳለፍነው ምሕረቱ ለዘላለም ስለሆነ ነው ። ፍቅሩ ዕለታዊ ዝማሬአችን ነው ። ዓመት ሙሉ በትክክል ተናግራችሁ አንድ ቀን ቢያደናቅፋችሁ ሁሉም ይወርድባችኋል ፣ እግዚአብሔር ግን ዓመት ሙሉ ተደናቅፈን አንድ ቀን ወደ እርሱ ስንመጣ ዋጋ ይሰጠዋል !

ፍቅሩ ይማርከን !

ይቀጥላል

መስከረም 11 ቀን 2019 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ