የጥንቱ የግሪክ ቋንቋ ፍቅርን ለመግለጥ አራት ቃላትን ይጠቀማል ። የእኛና የሌሎች ቋንቋዎች ፍቅርን ፍቅር በማለት ብቻ በውስንነት ሲገልጥ ግሪኩ ግን በተለያየ ቃላት ያብራራዋል ። እነዚህም አጋፔ ፣ ፊልዮ ፣ ስቶርጅ ፣ ኤሮስ ናቸው ። አጋፔ ጥቅምን ታሳቢ ያላደረገ ፣ በራሱ በአፍቃሪው ማንነት ላይ የተመሠረተ ፣ ይቅርታን የተሞላ ፍቅር ነው ። ይህ ለእግዚአብሔር ፍቅርና ለክርስቲያናዊ ፍቅር ይጠቀሳል ። ፊልዮ የወዳጅነት ፣ የጓደኝነት ፍቅር ነው ። የአሳብ አንድነት ያላቸው ፣ በደስታና በመከራ የማይለያዩ ወዳጆች ፊልዮ በሚል ፍቅር ይገለጣሉ ። ስቶርጅ የቤተሰብ ፍቅር ፣ ወላጅ ለልጅ ፣ ልጅ ለወላጅ ያለውን መዋደድ የሚገልጥ ነው ። ኤሮስ በወንድና በሴት ፣ በባልና በሚስት መካከል ያለው ስሜታዊ ፍቅር የሚገለጥበት ነው ።
አጋፔ የፍቅር ጉልላት ነው ። ከፍ ያለና ከፊልዮ ፣ ከስቶርጅ ፣ ከኤሮስ የተለየ ነው ። ይህ ፍቅር መለኮታዊ የሆነ ፣ ምክንያት የማይፈልግ ፣ ሁልጊዜ ወደሌሎች የሚፈስ ነው ። ይህ ፍቅር ምክንያት የማይፈልግ ተባለ እንጂ ምላሽ የማይፈልግ አልተባለም ። እግዚአብሔርን ዝም ብሎ የሚወደን ፣ ባንወደው የማይገርመው አምላክ አድርገን መሳል ትክክል አይደለም ። ፍቅር ፍቅር ይፈልጋል ። አጋፔ ብቸኛ ልጅን ለመውደድ የሚውል ቃል ሁኖ እናገኘዋለን ። እግዚአብሔር አንተን ሲወድህ ሌላ ፍጡር እንዳልፈጠረ አድርጎ ነው ፣ አንቺንም ሲወድሽ በምድር ላይ እንዳለች ብቸኛ ሴት አድርጎ ነው ። አጋፔ መለኮታዊ ፍቅር ነው ። ቀድሞ የሚወድ ፣ ምክንያት የማይሻ ፣ ምላሽ አላገኘሁም ብሎ የማይጠላ ፣ ሰዎች ይለወጣሉ ብሎ ተስፋ የሚያደርግ ነው ። እግዚአብሔር እኛን የወደደው በፊልዮ ፍቅር አይደለም ። የፊልዮ ፍቅር የእኩያነት ፍቅር በመሆኑ የጋራ መዋደድን ይፈልጋል ። እግዚአብሔር ግን ሳንወደው አስቀድሞ ወደደን ። የእግዚአብሔር ፍቅር የስቶርጅ ፍቅር አይደለም ። ሰዎች የእኔ የሚሉትን ልጃቸውን ይወዳሉ ። እግዚአብሔር ግን ሁሉን ይወዳል ። የእኔ ብቻ ይሁን ፣ የእኔ ብቻ ትሁን የሚለው ስግብግብነት ያለበት የኤሮስ ፍቅር የእግዚአብሔርን ፍቅር መግለጥ አይችልም ። አጋፔ የተለየ ፍቅር ነው ። በዚህ ፍቅር ክርስቲያኖች እርስ በርስ መዋደድ ይገባቸዋል ። በ1ቆሮ. 13 ላይ የተጠቀሰው ይህ የአጋፔ ፍቅር ነው ። በሁኔታዎች ላይ ያልተመሠረተው የእግዚአብሔር ፍቅር አጋፔ ተብሎ ይጠራል ። ይህ ፍቅር ለሌሎች ዋጋ የሚከፍሉበት የመሥዋዕትነት ፍቅር ነው ። ስለ ሌሎች እንደ ሻማ በመቅለጥ ደስ የሚለው እኔነትን የጣለ ፍቅር ነው ።
ለሌሎች መልካም ሲያደርግ የሚደሰት ፣ መንገድ የጠፋቸውን በትዕግሥት ለመምራት የሚኖረው ፍቅር አጋፔ ይባላል ። ሰዎችን የሚረዳው የእርሱ ወገን ስለሆኑ ሳይሆን እግዚአብሔር ስለፈጠራቸው ነው ። የአጋፔ ፍቅር ሲኖረን የአምላክ ሠራተኛ እንደሆንን ፣ ያለ ምክንያትም ወደ ምድር እንዳልመጣን እንረዳለን ። ድንገተኛ የሚመስል ደግነት አድርገን ስንውል እንረካለን ። ለማናውቀውና ደግመን ለማናገኘው ሰው ትሑትና አስደሳች ስንሆን ይህ ፍቅር ገዝቶናል ማለት ነው ። የአጋፔ ፍቅር በመስቀል ላይ በዋለው በክርስቶስ ተገልጧል (ዮሐ. 3፡16)። የዚህ ፍቅር ጀማሪዎች እኛ አይደለንም ፣ ይህን ፍቅር ለዓለም ማንጸባረቅ ግን ይጠበቅብናል ። መስፈርት በሌለው ፣ ውለታን ታሳቢ ባላደረገ ፍቅር መዋደድ ካልቻልን ዓለምን ማትረፍ አንችልም ። በዮሐ. 3፡16 ላይ እግዚአብሔር ዓለሙን እንዲሁ ወዷልና የሚለው በአጋፔ ፍቅር ወዷል ማለት ነው ።
በሰማይ የሚታወቀው የአጋፔ ፍቅር ብቻ ነው ። በምድር የሚታወቀው ደግሞ የኤሮስ ፍቅር ነው ። ዓለም ስለ ፍቅር ሲወራ ከተቃራኒ ጾታ ውጭ አታውቅም ። የእግዚአብሔር ፍቅር የሆነው የአጋፔ ፍቅር ለምድራውያን እንግዳና ለማመን የሚቸገሩበት ነው ። እግዚአብሔር የሰውን ዘር ሁሉ ይወዳል ፣ አማኝም በዚህ ፍቅር ሁሉን መውደድ አለበት ። ይህ ፍቅር ከእግዚአብሔር ጋር ልዩ ግንኙነት ያላቸው ሰዎች የሚረዱትና የሚለማመዱት ነው ። በዚህ ፍቅር ውስጥ መጠን የሌለው ደስታ አለ ። እውነተኛው ፍቅር ራሱን ለሌሎች አሳልፎ እስከ መስጠት የሚደርስ ነው ። በራስ ላይ ሳይሆን በሌሎች ላይ ያተኮረ ፍቅር ነው ፣ እኔ ባይ ፍቅር አይደለም ። በከፍታና በዝቅታ ውስጥም የማይዋዥቅ ፍቅር ነው ። አጋፔ ቀድሞ የሚወድ እንጂ እስኪወዱት የሚጠብቅ አይደለም ። በራስ ተነሣሽነት እንጂ በሰውዬው ማንነት ላይ ያልተመሠረተ ፍቅር ነው ። በፍልስፍና ፣ በሰውነት ውስጥ በሚካሄዱ የተፈጥሮ ለውጦች የተመሠረተ የኤሮስ ፍቅር ሳይሆን ቀድሞ እንቅስቃሴ የሚያደርግ ነው ። ከሌሎች የሚጠብቀውን ነገር ራሱ የሚያደርግ አጋፔ ነው ። አጋፔ ስሜት ላይ ሳይሆን ውሳኔ ላይ የተመሠረተ ነው ። እንደ ደራሽ ውኃ ወደድኩ አፈቀርኩ ፣ የእኔ ካልሆነ እሞታለሁ እገድላለሁ ባይ አይደለም ። እግዚአብሔር ወደደን እንጂ ለምን እንደወደደን አናውቅም ። በራሱ የፍቅር ጠባይ ወደደን ። አጋፔም ሰው መራጭ አይደለም ፣ ሁሉንም እንደ በረከቱ በመቍጠር ይወዳል ። በዚህ ዓለም ላይ የሚያሳርፈው መውደድ ነው ፣ ማንን ልውደድ ማለት ግን ዕረፍት ያሳጣል ።
ይህ ዓለም የተገኘበትና የዳነበት ፍቅር የአጋፔ ፍቅር ሲሆን ለሌሎች ፍቅሮች ሁሉ መሠረታቸው ነው ። ከዘመን ዘመን እንዲሁ የሚወዱን ሰዎች ካሉ የአጋፔ ፍቅር ሞልቶባቸው ነው ። አጋፔ ንጹሕ ፣ በሁኔታዎች ላይ ያልተመሠረተ ፣ መሥዋዕታዊ ፍቅር ነው ። ክርስቲያን ይህን ፍቅር መለማመድና ለዓለም ማንጸባረቅ አለበት ።
ይቀጥላል
መስከረም 18 ቀን 2019 ዓ.ም.