የትምህርቱ ርዕስ | ስቶርጅ

የቤተሰብ ፍቅር ማለት ነው ። ግሪኮች ከፊልዮ ወይም ከወዳጅነት ፍቅር የተለየ መሆኑን ለመግለጥ ቤተሰባዊ ፍቅርን ስቶርጅ በማለት ይጠሩታል ። ቤተሰባዊ ፍቅር ከጓደኝነት ፍቅር የሚለየው ጓደኛን እኛ ስመርጠው ቤተሰብ ግን የተመረጠልን ነው ። ጓደኝነት የሚቆምበት ምዕራፍ ብዙ ነው ፣ ቤተሰብ ግን እስከ ሞት ድረስ የመዝለቅ ጠባይ አለው ። ጓደኝነትን መቁረጥና ማብቃት ይቻላል ፣ ቤተሰብን መቁረጥና ማቆም ግን አይቻልም ። በሰላም ቀን የተራራቀ የሚመስለው ቤተሰብ ኀዘን በመጣ ጊዜ አለሁ ብሎ ይወጣል ። ስቶርጅ የወላጅና የልጆችን ፍቅር ፣ የልጆችንና የወላጆችን መዋደድ የሚገልጥ ነው ። በዚያው አያትን ፣ አክስትን ፣ አጎትን ፣ የቅርብ የሥጋ ዘመዶችን ይነካል ። ቤተሰባዊ ፍቅር ከአንድ ወገን በመወለድ ፣ አብሮ በማደግ ፣ ሊገለጥ በማይችል ስሜት በመተሳሰብ የሚመጣ ነው ።

ወላጆች ለልጆቻቸው ዘመን ያልፈተነው ፍቅር አላቸው ። ልጆቻቸውን የጣሉ ወላጆች ቢኖሩ እንኳ ከቍጥር የሚገቡ አይደሉም ። በመጨረሻው ዘመን ፍቅር እየቀዘቀዘ ቢሆንም የወላጅና የልጅ ፍቅር ግን አሁንም እንደ ሞቀ ነው ። ወላጆች አባትነትና እናትነትን በጸጋ ከእግዚአብሔር ይቀበላሉ ። እውነተኛው አባታችንና እናታችን እግዚአብሔር ነው ። እነዚህ ምድራውያን ወላጆች ይሞታሉ ፣ እርሱ ግን የማይሞት ነው ። ወላጆች ለልጆቻቸው ያላቸው ፍቅር የአብራካቸው ክፋይ በመሆናቸው ስሜታዊ ትስስት አለው ። ሁሉም ሰው ሊወልድ አይችልም ። ሚሊየን ሕፃናትን ያሳደጉና ከሞት የታደጉ ሰዎች ያልወለዱ ናቸው ። ይህ የመንፈስ አባትነትና እናትነት ነው ። ራሱ እግዚአብሔር አባታችን የተባለው በሥጋ ልደት ሳይሆን በመንፈስ ወልዶን ነው ። በመንፈስ መውለድ በሥጋ ከመውለድ የበለጠ ነው ። ወላጆች ለልጆቻቸው ያላቸው ፍቅር እወድሃለሁ በማለት የሚያበቃ ሳይሆን ተግባራዊ ነው ። የልጃቸውን የሥጋውን ፍላጎት ምግብ በመስጠት ፣ የነፍሱን ፍላጎት መምህር ዘንድ በመስደድ ፣ የመንፈሱን ፍላጎት ሃይማኖትን በመስጠት ያሟላሉ ። ፍቅር ተግባራዊ ሁኖ የሚታየው ወላጆች ዘንድ ነው ።

ልጅ አግብቶ ከቤት ቢወጣም ከወላጅ ልብ ውስጥ ግን አሁንም አለ ። እርሱ ወልዶ “ልጄ” ቢል እንኳ ለወላጁ ግን አሁንም ልጅ ነው ። ወላጅ ያደገውንና ትልቅ ስም ያለውን ልጅ ሳይሆን እርዳታ ይፈልግ የነበረውን ያንን ትንሹን ሕፃን ያስባል ። ልጅ የሚያድገው ለራሱ ነው ፣ ለወላጅ ግን ሁሌም ልጅ ነው ። በዚህ ዓለም ላይ መልስ ያላገኘ ፍቅር የወላጅ ፍቅር ነው ። ልጅ አንገት የለውምና መለስ ብሎ ወላጆቹ የሰጡትን ፍቅር መመለስ አይችልም ። የተሾሙ ወጣቶችን ሁሉም ሰው ይፈልጋቸዋል ፣ እስር ቤት ሲገቡ የሚጠይቃቸው ግን የወለደ ብቻ ነው ። ሲሳካላትም ሲወድቅም ልጁን የማይጥል ወላጅ ነው ። በርግጥ የወላጅ ፍቅር ፍጹም ነው ማለት አይደለም ። ሰው ጥላውን ይዞ እንደሚዞር ልጅም የወላጅ ፍቅር ሲከተለው ይኖራል ። ወጥቶ ለመግባት ፣ ከነደደው እሳት ለመውጣት የወላጅ ጸሎት ወሳኝ ነው ። እርምጃ የሚለማመዱ ሕፃናት እነርሱ በራሳቸው እየሄዱ ይመስላቸዋል ፣ አሊያም ብወድቅስ የሚል ፍርሃት ይንጣቸዋል ። ከኋላ ግን የተሰወረ የአባት እጅ ይጠብቃቸዋል ። በእቅፍ ሙቀት እናት ልጅን ስትንከባከብ ፣ እርምጃን በማለማመድ ደግሞ አባት ልጁን ጠንካራ ያደርገዋል ። የቆሙ ሁሉ ፣ የሚራመዱ አእላፋት ስውር እጅ እንደ ደገፋቸው አያውቁም ።

ያደገ ልጅ እጁን ይለቁታል ፣ ልብ ግን አይለቀውምና ወላጅ አሁንም ጥበቃ ላይ ነው ። በርግጥ እምነት ከሌለን ልጆችን ማሳደግ ብርቱ ነው ። አምነን ስንተው እኛም እንተኛለን ፣ ልጆችም እግዚአብሔርን ይዘው ወደፊት ይራመዳሉ ። ቅዱስ ጭካኔ ልጅን ከፍርሃት ያድነዋል ። የወዳጅ በር እንደ አደጋ መውጫ በር ነው ፤ ከወጡ በኋላ መመለሻ የለውም ። የወላጅ በር ግን ሁልጊዜ ክፍት ነው ። ቢረሳ ቢረሳ የወላጅ እጅ ሊረሳ አይገባውም ። ወላጅ የልጁን ፊት ሲያስታውስ ይኖራል ፣ ልጅ ደግሞ የወላጅን እጅ ሲረሳ ይኖራል ። ወላጅ በልጁ ችግር ሁሉ መድረስ አይችልም ፣ በችግር ሁሉ የሚደርሰውን ጌታ ማስተዋወቅ ግን ይገባዋል ። ወላጅ ለልጅ ሕይወቱን ፣ ዕድሜውንና ውበቱን ያባክናል ። ትዝታውም ምግብ ሁኖት ይኖራል ። በሕይወት ውስጥ የሚያስደስተውና “ኖሬአለሁ ተመስገን” የሚያሰኘው ለሌሎች መቆረስ ነውና ።

ልጆች በልጅነታቸው ወላጅን ከቤት አናስወጣም ብለው ማኅበራዊ ኑሮን አሰርዘዋል ። ልጅ የማይታይ ገመድ ነው ። ገመድን በስለት ይቆርጡታል ። እየጠላ የሚወደድ ቢኖር ልጅ ነው ። ልጅ አድጎ እንዲያ የወደዱትን ወላጆች ስልካቸውን እንኳ አላነሣም ሲል ያሳዝናል ። ወላጆችም ጠንካራ መሆን ፣ ሁልጊዜ ልጅን ልምራ ብሎ መውጣት አይገባቸውም ። እግዚአብሔር የጻፈላቸውን እንዲሆኑ ልጆችን መልቀቅ ያስፈልጋል ። አሊያ የራስን ጤና ፣ የልጅን ሕይወት መክሰር ይመጣል ። የቤተሰብ ፍቅር ካለፉት ሃምሳ ዓመታት ወዲህ በአገራችን ተመትቷል ። በአብዮተኞች አደፋፋሪነት አባት ልጁን ፣ ልጅ አባቱን አሳልፎ ሰጥቷል ፣ አብዮት ልጅዋን በላች በሚል መፈክር ወንድምና ወንድም ፣ የትግል አጋር ጭምር በመበላላታቸው የቤተሰብ ፍቅር ተጎድቷል ። እንክርዳድ በሆነውና በትውልዱ ላይ በበቀለው ዘረኝነት የቤተሰብ ፍቅር ተጎድቷል ። አባት ልጁን እናትህ ከዚህ ዘር የተወለደች ናት ፣ በላት እንዳለ በቅርብ እንሰማለን ። የቤተሰብ ፍቅር በውርስ ክርክሮች በጣም እየተጎዳ ነው ። በየፍርድ ቤቱ የሞላው ፋይል የቤተሰብ ክስ ነው ። የቤተሰብ ፍቅር ሲናጋ የአገር ፍቅር እየተናጋ ይመጣል ። ቤተሰብ በቁም የማይረዳዳ የልቅሶ ቀን የኀዘን ባንድ ሆኖ የሚመጣ መሆኑ ያሳዝናል ።

ይቀጥላል

መስከረም 22 ቀን 2019 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ