የትምህርቱ ርዕስ | የሕፃናት ልብ

አንድ ሕፃን ልጅ አሻንጉሊቱ ተሰበረበት ። ጓደኞቹ ሁሉ መጠገን እንደማይችል ቢነግሩትን መስማት አልቻለም ። እየሮጠ ወደ አባቱ ዘንድ ይዞት ሄደ ። አባቱም አሻንጉሊቱን ጠግኖ ሰጠው ። ይህ ሕፃን ሦስት ነገሮችን በውስጡ ይዟል ። አይቻልም የሚሉትን ሰዎች መስማት አልፈለገም ። ሁለተኛ እርሱ መጠገን የማይችል ደካማ መሆኑን አምኗል ። ሦስተኛ አባቱ እንደሚችል እርግጠኛ ነው ። በሕይወታችን ውስጥ እንደ ሕፃናት መሆን ያስፈልገናል ። ስንወድቅ አይነሡም ፣ ስናጣ አያገኙም ፣ ስንሳሳት አይታረሙም የሚሉን ብዙዎች ሊሆኑ ይችላሉ ። አንድ ዕቅድ ይዘን ስንነሣ አይሳካም ፣ አብደሃል ወይ ? ሊሆን አይችልም ፣ ሁሉም ሰው ጠላት ሁኖ ይነሣብሃል እያሉ የሚያስፈራሩ ሰዎች ይኖራሉ ። ሰዎች ሊያስፈራሩ ይችላሉ ፣ የእኛ ድርሻ ግን አለመፍራት ብቻ ነው ።

ዛሬ የምንጠቀምባቸውን ጠቃሚ ግኝቶች የሠሩ ሰዎች መጀመሪያ ላይ ይህን የመሰለ ተቃውሞና የፍርሃት ድምፅ አስተናግደዋል ። አዳካሚዎችን ባለመስማት ግን ለዓለም ብርሃን ሆነዋል ። ሥልጣኔ ወደ አገራችን ሲገባ ፣ ዘመናዊ ግኝቶች ጥቅም ላይ ሲውሉ ብዙ ተቃውሞ ነበረ ። ስልክ ማውራት ከሰይጣን ጋር መነጋገር ነው ተብሎ ብዙ ተቃውሞ ገጥሞታል ። ዛሬ ላይ ግን ከመሰሰታችን የተነሣ ከአንድ በላይ ስልክ አለን ። ሊያበረታቱን የሚችሉ እነማን ናቸው ? ብለን መምረጥ ካልቻልን ራእያችን ከጅምሩ ይቀጫል ። ይልቁንም በብዙ ተቃውሞ ውስጥ አልፈው ትልቅ ደረጃ ላይ የደረሱትን ሰዎች ማማከር የተሻለ ነው ። ውድቀት ፣ ስብራትና አለመሳካት ዘላለማዊ ዕጣዎቻችን አይደሉም ፣ የታላቅ ትንሣኤ መነሻ ናቸው ።

የራስን ድካም ማመን ወሳኝ ነው ። እኔ አልችልም አምላኬ ግን ይችላል ብሎ መደላደል አስፈላጊ ነው ። ሰው ከነ ድካሙ የሚቀበለው አምላክ እንዳለው ማመን አለበት ። ሕፃን ልጅ ባለመቻሉ አይደነግጥም ፣ ወደሚችለው አባቱ ግን ይሮጣል ። ጌታችን ወደ እርሱ ለሚመጡ መስፈርት አውጥቶአል ። መስፈርቱም “እናንተ ደካሞች” የሚል ነው ። ደካማነት ወደ ክርስቶስ ለመቅረብ ትልቁ መስፈርት ነው ። ድካሙን ያላመነ ሰው ሊጸልይ አይችልም ። ልጆች ብዙ ጊዜ የሚጎዱት ራሴ እወጣዋለሁ ብለው ወላጆቻቸውን ሲደብቁ ነው ። በቀላሉ የሚድን ቍስል ድብቅ በመሆናቸው ምክንያት አደገኛ ሁኔታ ላይ ይደርሳል ። ያንን ልጅ የሚያስፈራውና የሚያስፈራራው አካል ለወላጅ በመንገር ብቻ በቶሎ መቆም ሲችል ያ ልጅ ራሴ እወጣዋለሁ በማለት አላስፈላጊ ጭንቀት ውስጥ ይገባል ። በክርስትናችን ውስጥ በራሳችን ከማንችላቸው ነገሮች አንዱ የኃጢአትን ስርየት ተቀብሎ የሕሊና ዕረፍት ማግኘት ነው ። ይቅር ብሎ ዕረፍትን የሚሰጠን እግዚአብሔር ብቻ ነው ። ወደ እርሱ ከነ ድካማችን መምጣት ይገባል ።

እግዚአብሔር ይችላል ብሎ ማመን ይገባል ። እርሱ እኛ የሰበርነውን ያለ ወቀሳ ይጠግንልናል ። እኛ ያበላሸነውን ያለ ቍጣ ያስተካክለዋል ። ጌታችን በናዝሬት ያደገ የናዝሬቱ ኢየሱስ ተብሎ የተጠራ ነው ። ናትናኤል ግን ይህን ሰምቶ፡- “ከናዝሬት መልካም ነገር ሊወጣ ይችላልን?” አለ (ዮሐ. 1፡47)። ይህ ንግግር ዛሬ ላይ ተነግሮ ቢሆን ብዙ ረብሻ ያስነሣ ነበር ። አንዱን ብሔር ለማሳነስ ተብሎ የተነገረ ነው በማለት ለፍርድ ይቅረብልን ይባል ነበር ። ጌታችን ግን ንግግሩን ሳይሆን የናትናኤልን ተንኮል የሌለበትን የሕፃን ልቡን አየ ። ናትናኤል በቍጣ ሲናገረው ጌታ በፍቅር ቀረበው ። በዚህ ምክንያት ከ12ቱ ደቀ መዛሙርት አንዱ ለመሆን በቃ ። እግዚአብሔር ድካማችንን ያውቀዋል ፣ ሊለውጠን ይተጋልናል ። ያየውን ሊሳይብን ፣ የሰማውን ሊያሰማብን አይሻም ። ሰው ሁሉ ለብሶ የሚወጣው እግዚአብሔር ከድኖለት ነው ። የተከደነለት ሰው ሌላውን ሲገልጥ እግዚአብሔር ይደነቃል ።

አምላካችን ይችላል ። ብዙ ሰባራ ነገሮች አሉብን ። የብዙዎቻችን ደስታ ከመንጋቱ ይመሽበታል ። ስኬታችንን አውርተን ሳንጨርስ ማሽቆልቆል ይጀምራል ። የሚጠሉንም አገኘነው ብለው እንደ ወደቀ ዛፍ ምሣር ያበዙብናል ። ጌታችን ግን ሳቃችንን ሊመልስ ፣ የተነጠቅነውን ደስታ እንደገና ሊሰጠን ፣ የሚጠሉንን ሊያሳፍር ይችላል ። የሰዎችን ማጣጣል ፣ የራሳችንን ፍርሃት ወዲያ ወርውረን ወደ ጥበበኛው ጌታ እንገስግስ ። እኛ ወፍ ዘራሽ አይደለንም ፣ የሥላሴ ዕቅድ ሆነን ወደ ምድር መጥተናል ። ርካሽና ተራ ሰው አይደለንም ፣ ቅዱሳን መላእክት የሚጠብቁን ፣ በጠባቂ የምንንቀሳቀስ ነን ። የእግዚአብሔር ውዶች ነንና ደስ ሊለን ይገባል ።

ይቀጥላል

መስከረም 25 ቀን 2019 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ